1 ቆሮንቶስ 5:1-13
5 በመካከላችሁ ዝሙት እንደተፈጸመ ይወራል፤ እንዲህ ዓይነቱ ዝሙት ደግሞ በአሕዛብ መካከል እንኳ ታይቶ አይታወቅም፤ ከአባቱ ሚስት ጋር የሚኖር ሰው አለ ተብሏል።
2 ታዲያ በዚህ ድርጊት ማዘንና ድርጊቱን የፈጸመውን ሰው ከመካከላችሁ ማስወጣት ሲገባችሁ በዚህ ትኩራራላችሁ?
3 ምንም እንኳ እኔ በአካል ከእናንተ ጋር ባልሆንም በመንፈስ ከእናንተ ጋር ስለሆንኩ እንዲህ ያለ ድርጊት በፈጸመው ሰው ላይ አብሬያችሁ ያለሁ ያህል ሆኜ ፈርጄበታለሁ፤
4 የእኔም መንፈስ በጌታችን በኢየሱስ ኃይል ከእናንተ ጋር ሆኖ አንድ ላይ በምትሰበሰቡበት ጊዜ በጌታችን በኢየሱስ ስም
5 እንዲህ ያለውን ሰው ለሰይጣን አሳልፋችሁ ስጡት፤ ይህም እሱ በጉባኤው ላይ ያሳደረው ሥጋዊ ተጽዕኖ እንዲወገድና* የጉባኤው መንፈስ በጌታ ቀን ተጠብቆ እንዲቆይ ነው።
6 የምትመኩበት ነገር መልካም አይደለም። ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ እንደሚያቦካው አታውቁም?
7 አሁን እንደሆናችሁት ሁሉ ያልቦካ አዲስ ሊጥ እንድትሆኑ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ። ምክንያቱም ፋሲካችን ክርስቶስ ተሠውቷል።
8 ስለዚህ በዓሉን በአሮጌ እርሾ እንዲሁም በክፋትና በኃጢአተኝነት እርሾ ሳይሆን እርሾ በሌለበት በቅንነትና በእውነት ቂጣ እናክብር።
9 ከሴሰኞች ጋር መግጠማችሁን እንድትተዉ በደብዳቤዬ ላይ ጽፌላችሁ ነበር፤
10 እንዲህ ስል ግን በአጠቃላይ ከዚህ ዓለም ሴሰኞች ወይም ስግብግብ ሰዎችና ቀማኞች ወይም ደግሞ ጣዖት አምላኪዎች ጋር አትገናኙ ማለቴ አይደለም። እንዲህ ቢሆንማ ኖሮ ጨርሶ ከዓለም መውጣት ያስፈልጋችሁ ነበር።
11 አሁን ግን እየጻፍኩላችሁ ያለሁት ወንድም ተብሎ እየተጠራ ሴሰኛ ወይም ስግብግብ ወይም ጣዖት አምላኪ ወይም ተሳዳቢ ወይም ሰካራም ወይም ቀማኛ ከሆነ ማንኛውም ሰው ጋር መግጠማችሁን እንድትተዉ አልፎ ተርፎም እንዲህ ካለው ሰው ጋር ምግብ እንኳ እንዳትበሉ ነው።
12 በውጭ ባሉ ሰዎች ላይ የምፈርደው እኔ ምን አግብቶኝ ነው? በውስጥ ባሉት ሰዎች ላይ እናንተ አትፈርዱም?
13 በውጭ ባሉት ላይ አምላክ ይፈርዳል። “ክፉውን ሰው ከመካከላችሁ አስወጡት።”