ሆሴዕ 1:1-11

  • የሆሴዕ ሚስትና የወለደቻቸው ልጆች (1-9)

    • ኢይዝራኤል (4)፣ ሎሩሃማ (6) እና ሎአሚ (9)

  • አንድ እንደሚሆኑ የተነገረ ተስፋ (10, 11)

1  በይሁዳ ነገሥታት+ በዖዝያ፣+ በኢዮዓታም፣+ በአካዝና+ በሕዝቅያስ+ እንዲሁም በእስራኤል ንጉሥ በዮአስ+ ልጅ በኢዮርብዓም+ ዘመን ወደ ቤኤሪ ልጅ ወደ ሆሴዕ* የመጣው የይሖዋ ቃል።  ይሖዋ በሆሴዕ አማካኝነት ቃሉን መናገር ሲጀምር ይሖዋ ሆሴዕን እንዲህ አለው፦ “ሄደህ ዝሙት አዳሪ ሴት* አግባ፤ እሷ በምትፈጽመውም ምንዝር* ልጆች ይወለዱልሃል፤ ምክንያቱም በምንዝር የተነሳ* ምድሪቱ ይሖዋን ከመከተል ሙሉ በሙሉ ርቃለች።”+  ስለዚህ ሄዶ የዲብላይምን ልጅ ጎሜርን አገባ፤ እሷም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደችለት።  ከዚያም ይሖዋ እንዲህ አለው፦ “ልጁን ኢይዝራኤል* ብለህ ጥራው፤ በኢይዝራኤል* ለፈሰሰው ደም የኢዩን ቤት በቅርቡ ተጠያቂ አደርጋለሁና፤+ የእስራኤል ቤት ንጉሣዊ አገዛዝም እንዲያከትም አደርጋለሁ።+  በዚያ ቀን የእስራኤልን ቀስት በኢይዝራኤል ሸለቆ* እሰብራለሁ።”  እሷም ዳግመኛ ፀነሰች፤ ሴት ልጅም ወለደች። አምላክም እንዲህ አለው፦ “ልጅቷን ሎሩሃማ* ብለህ ጥራት፤ ምክንያቱም ከእንግዲህ ለእስራኤል ቤት ምሕረት አላሳይም፤+ በእርግጥ አስወግዳቸዋለሁ።+  ለይሁዳ ቤት ግን ምሕረት አደርጋለሁ፤+ በቀስት፣ በሰይፍ፣ በጦርነት፣ በፈረሶች ወይም በፈረሰኞች ሳይሆን በአምላካቸው በይሖዋ አድናቸዋለሁ።”+  ጎሜር፣ ሎሩሃማን ጡት ካስጣለች በኋላ ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች።  ከዚያም አምላክ እንዲህ አለው፦ “ልጁን ሎአሚ* ብለህ ጥራው፤ ምክንያቱም እናንተ ሕዝቤ አይደላችሁም፤ እኔም አምላካችሁ አይደለሁም። 10  “የእስራኤልም ሕዝብ* ብዛት ሊሰፈር ወይም ሊቆጠር እንደማይችል እንደ ባሕር አሸዋ ይሆናል።+ ‘ሕዝቤ አይደላችሁም’+ ተብሎ በተነገራቸው ስፍራም ‘የሕያው አምላክ ልጆች’ ይባላሉ።+ 11  የይሁዳና የእስራኤል ሕዝብ ተሰብስበው አንድ ይሆናሉ፤+ ለራሳቸውም አንድ መሪ ይሾማሉ፤ ከምድሪቱም ይወጣሉ፤ የኢይዝራኤል ቀን ታላቅ ይሆናልና።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ሆሻያህ የሚለው ስም አጭር መጠሪያ ሲሆን “ያህ አዳነው፤ ያህ አድኗል” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “ነውረኛ ሴት፤ ሴሰኛ ሴት።”
ወይም “ነውር፤ ሴሰኝነት።”
ወይም “በነውር የተነሳ፤ በሴሰኝነት የተነሳ።”
“አምላክ ዘር ይዘራል” የሚል ትርጉም አለው።
ዋና ከተማዋ ሰማርያ ብትሆንም ኢይዝራኤል የሰሜናዊ እስራኤል ነገሥታት መቀመጫ ነበረች። 1ነገ 21:1ን ተመልከት።
ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”
“ምሕረት አልተደረገላትም” የሚል ትርጉም አለው።
“ሕዝቤ አይደሉም” የሚል ትርጉም አለው።
ቃል በቃል “ወንዶች ልጆች።”