የሉቃስ ወንጌል 13:1-35

  • ‘ንስሐ ካልገባችሁ ትጠፋላችሁ’ (1-5)

  • ፍሬ አልባ የሆነችው የበለስ ዛፍ ምሳሌ (6-9)

  • የአካል ጉዳተኛ የሆነች ሴት በሰንበት ተፈወሰች (10-17)

  • የሰናፍጭ ዘሯ ምሳሌና የእርሾው ምሳሌ (18-21)

  • በጠባቡ በር ለመግባት መጋደል ያስፈልጋል (22-30)

  • ሄሮድስ፣ ‘ያ ቀበሮ’ (31-33)

  • ኢየሱስ ስለ ኢየሩሳሌም የተሰማውን ሐዘን ገለጸ (34, 35)

13  በወቅቱ፣ በዚያ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ጲላጦስ ደማቸውን ከመሥዋዕታቸው ጋር ስለደባለቀው ስለ ገሊላ ሰዎች ለኢየሱስ አወሩለት። 2  እሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “እነዚህ የገሊላ ሰዎች ይህ ስለደረሰባቸው ከሌሎቹ የገሊላ ሰዎች ይበልጥ ኃጢአተኞች እንደሆኑ አድርጋችሁ ታስባላችሁ? 3  በፍጹም፤ ነገር ግን ንስሐ ካልገባችሁ ሁላችሁም እንደ እነሱ ትጠፋላችሁ።+ 4  ወይም ደግሞ የሰሊሆም ግንብ ተንዶባቸው የሞቱት 18 ሰዎች በኢየሩሳሌም ከሚኖሩት ሰዎች ሁሉ ይበልጥ በደለኞች የነበሩ ይመስላችኋል? 5  በፍጹም፤ ነገር ግን ንስሐ ካልገባችሁ ሁላችሁም ልክ እንደ እነሱ ትጠፋላችሁ።” 6  ከዚያም እንዲህ ሲል ይህን ምሳሌ ተናገረ፦ “አንድ ሰው በወይን እርሻው ውስጥ የተተከለች አንዲት የበለስ ዛፍ ነበረችው፤ እሱም ከዛፏ ፍሬ ሊለቅም መጣ፤ ሆኖም ምንም አላገኘባትም።+ 7  በዚህ ጊዜ የወይን አትክልት ሠራተኛውን ‘ከዚህች የበለስ ዛፍ ፍሬ ለማግኘት ሦስት ዓመት ሙሉ ተመላለስኩ፤ ሆኖም ምንም አላገኘሁባትም። ስለዚህ ቁረጣት! ለምን በከንቱ ቦታ ትይዛለች?’ አለው። 8  እሱም መልሶ እንዲህ አለው፦ ‘ጌታዬ፣ ዙሪያዋን ቆፍሬ ፍግ ላድርግባትና እስቲ ለአንድ ዓመት ደግሞ እንያት። 9  ወደፊት ፍሬ ካፈራች ጥሩ፤ ካልሆነ ግን ትቆርጣታለህ።’”+ 10  ኢየሱስ በሰንበት ቀን አንድ ምኩራብ ውስጥ እያስተማረ ነበር። 11  በዚያም ባደረባት ክፉ መንፈስ የተነሳ ለ18 ዓመት በበሽታ ስትማቅቅ የኖረች* አንዲት ሴት ነበረች፤ በጣም ከመጉበጧም የተነሳ ፈጽሞ ቀና ማለት አትችልም ነበር። 12  ኢየሱስም ባያት ጊዜ ጠራትና “አንቺ ሴት፣ ከበሽታሽ ተገላግለሻል” አላት።+ 13  እጁንም ጫነባት፤ ወዲያውም ቀጥ አለች፤ አምላክንም ማመስገን ጀመረች። 14  የምኩራቡ አለቃ ግን ኢየሱስ በሰንበት ቀን በመፈወሱ ተቆጥቶ ሕዝቡን “ሥራ የሚሠራባቸው ስድስት ቀኖች አሉ፤+ ስለዚህ በእነዚያ ቀኖች እየመጣችሁ ተፈወሱ እንጂ በሰንበት ቀን አይደለም” አላቸው።+ 15  ይሁን እንጂ ጌታ እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “እናንተ ግብዞች፣+ እያንዳንዳችሁ በሰንበት ቀን በሬያችሁን ወይም አህያችሁን ከጋጣው ፈታችሁ ውኃ ለማጠጣት ትወስዱ የለም?+ 16  ታዲያ የአብርሃም ልጅ የሆነችውና 18 ዓመት ሙሉ በሰይጣን ታስራ የኖረችው ይህች ሴት በሰንበት ቀን ከዚህ እስራቷ መፈታት አይገባትም?” 17  ኢየሱስ ይህን በተናገረ ጊዜ ተቃዋሚዎቹ ሁሉ በኀፍረት ተሸማቀቁ፤ ሕዝቡ በሙሉ ግን እሱ ባደረጋቸው አስደናቂ ነገሮች+ ሁሉ ይደሰቱ ጀመር። 18  ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “የአምላክ መንግሥት ከምን ጋር ይመሳሰላል? ከምንስ ጋር ላነጻጽረው? 19  አንድ ሰው ወስዶ በአትክልት ቦታው ከዘራት የሰናፍጭ ዘር ጋር ይመሳሰላል፤ ይህች ዘር አድጋ ዛፍ ሆነች፤ የሰማይ ወፎችም በቅርንጫፎቿ ላይ ሰፈሩ።”+ 20  ደግሞም እንዲህ አለ፦ “የአምላክን መንግሥት ከምን ጋር ላነጻጽረው? 21  አንዲት ሴት ወስዳ ሊጡ በሙሉ እስኪቦካ ድረስ ከሦስት ትላልቅ መስፈሪያ* ዱቄት ጋር ከደባለቀችው እርሾ ጋር ይመሳሰላል።”+ 22  ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም እየተጓዘ ሳለ በየከተማውና በየመንደሩ እያስተማረ ያልፍ ነበር። 23  በዚህ ጊዜ አንድ ሰው “ጌታ ሆይ፣ የሚድኑት ጥቂቶች ናቸው?” ሲል ጠየቀው። እሱም እንዲህ አላቸው፦ 24  “በጠባቡ በር ለመግባት ከፍተኛ ተጋድሎ አድርጉ፤+ እላችኋለሁ፦ ብዙዎች ለመግባት ይፈልጋሉ፤ ነገር ግን አይችሉም። 25  የቤቱ ባለቤት ተነስቶ አንዴ በሩን ከዘጋው በኋላ ውጭ ቆማችሁ ‘ጌታ ሆይ፣ ክፈትልን’+ እያላችሁ በሩን ብታንኳኩ ‘ከየት እንደመጣችሁ አላውቅም’ ብሎ ይመልስላችኋል። 26  በዚህ ጊዜ ‘አብረንህ እኮ በልተናል፤ ደግሞም ጠጥተናል፤ በአውራ ጎዳናዎቻችንም አስተምረሃል’ ማለት ትጀምራላችሁ።+ 27  እሱ ግን ‘ከየት እንደመጣችሁ አላውቅም። እናንተ ክፉ አድራጊዎች ሁሉ፣ ከእኔ ራቁ!’ ይላችኋል። 28  አብርሃምን፣ ይስሐቅን፣ ያዕቆብንና ነቢያትን ሁሉ በአምላክ መንግሥት ውስጥ ስታዩና እናንተ ግን በውጭ ተጥላችሁ ስትቀሩ በዚያ ታለቅሳላችሁ፤ ጥርሳችሁንም ታፋጫላችሁ።+ 29  በተጨማሪም ሰዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ እንዲሁም ከሰሜንና ከደቡብ መጥተው በአምላክ መንግሥት በማዕድ ይቀመጣሉ። 30  ደግሞም ከኋለኞች መካከል ፊተኞች የሚሆኑ፣ ከፊተኞች መካከልም ኋለኞች የሚሆኑ አሉ።”+ 31  በዚያን ጊዜ አንዳንድ ፈሪሳውያን መጥተው “ሄሮድስ ሊገድልህ ስለሚፈልግ ከዚህ ውጣና ሂድ” አሉት። 32  እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ሄዳችሁ ያንን ቀበሮ ‘ዛሬና ነገ አጋንንትን አስወጣለሁ እንዲሁም ሰዎችን እፈውሳለሁ፤ በሦስተኛውም ቀን ሥራዬን አጠናቅቃለሁ’ በሉት። 33  ይሁንና ነቢይ ከኢየሩሳሌም ውጭ ሊገደል ስለማይችል* ዛሬና ነገ እንዲሁም ከነገ ወዲያ ጉዞዬን መቀጠል አለብኝ።+ 34  ኢየሩሳሌም፣ ኢየሩሳሌም፣ ነቢያትን የምትገድል፤ ወደ እሷ የተላኩትንም በድንጋይ የምትወግር፤+ ዶሮ ጫጩቶቿን በክንፎቿ ሥር እንደምትሰበስብ እኔም ልጆችሽን ለመሰብሰብ ስንት ጊዜ ፈለግኩ! እናንተ ግን አልፈለጋችሁም።+ 35  እነሆ፣ ቤታችሁ* ለእናንተ የተተወ ይሆናል።+ እላችኋለሁ፣ ‘በይሖዋ* ስም የሚመጣ የተባረከ ነው!’ እስክትሉ ድረስ ፈጽሞ አታዩኝም።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “በዚያም ለ18 ዓመት የሚያሽመደምድ መንፈስ ያደረባት።”
ቃል በቃል “የሲህ መስፈሪያ።” አንድ ሲህ 7.33 ሊትር ነው። ለ14ን ተመልከት።
ወይም “መገደሉ የማይታሰብ ነገር ስለሆነ።”
ቤተ መቅደሱን ያመለክታል።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።