የሉቃስ ወንጌል 15:1-32

  • የጠፋችው በግ ምሳሌ (1-7)

  • የጠፋው ሳንቲም ምሳሌ (8-10)

  • የአባካኙ ልጅ ምሳሌ (11-32)

15  አንድ ቀን ቀራጮችና ኃጢአተኞች ሁሉ ኢየሱስን ለመስማት በዙሪያው ተሰበሰቡ።+ 2  ፈሪሳውያንና ጸሐፍትም “ይህ ሰው ኃጢአተኞችን ይቀበላል፤ ከእነሱም ጋር ይበላል” እያሉ አጉረመረሙ። 3  በዚህ ጊዜ የሚከተለውን ምሳሌ ነገራቸው፦ 4  “ከእናንተ መካከል 100 በጎች ያሉት ሰው አንዷ ብትጠፋበት 99ኙን በምድረ በዳ ትቶ የጠፋችውን እስኪያገኝ ድረስ አይፈልግም?+ 5  በሚያገኛትም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ላይ ይሸከማታል። 6  ቤት ሲደርስም ጓደኞቹንና ጎረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ ‘የጠፋችውን በጌን ስላገኘኋት የደስታዬ ተካፋዮች ሁኑ’ ይላቸዋል።+ 7  እላችኋለሁ፣ ልክ እንደዚሁ ንስሐ መግባት ከማያስፈልጋቸው 99 ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ አንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ታላቅ ደስታ ይሆናል።+ 8  “ወይም ደግሞ አሥር ድራክማ ሳንቲሞች* ያሏት አንዲት ሴት አንዱ ድራክማ* ቢጠፋባት መብራት አብርታ ቤቷን በመጥረግ እስክታገኘው ድረስ በደንብ አትፈልገውም? 9  ሳንቲሙን ባገኘችው ጊዜም ጓደኞቿንና ጎረቤቶቿን* በአንድነት ጠርታ ‘የጠፋብኝን ድራክማ ሳንቲም* ስላገኘሁት የደስታዬ ተካፋዮች ሁኑ’ ትላቸዋለች። 10  እላችኋለሁ፣ ልክ እንደዚሁ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በአምላክ መላእክት ዘንድ ደስታ ይሆናል።”+ 11  ከዚያም እንዲህ አለ፦ “አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት። 12  ታናሽየውም ልጅ አባቱን ‘አባቴ ሆይ፣ ከንብረትህ ድርሻዬን ስጠኝ’ አለው። በመሆኑም አባትየው ንብረቱን ለልጆቹ አካፈላቸው። 13  ከጥቂት ቀንም በኋላ ታናሽየው ልጅ ያለውን ነገር ሁሉ ሰብስቦ ወደ ሩቅ አገር ተጓዘ፤ በዚያም ልቅ የሆነ* ሕይወት በመኖር ንብረቱን አባከነ። 14  ያለውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ በዚያ አገር በሙሉ ከባድ ረሃብ ተከሰተ፤ በዚህ ጊዜ ችግር ላይ ወደቀ። 15  ከችግሩም የተነሳ ከዚያ አገር ሰዎች ወደ አንዱ ሄዶ የሙጥኝ አለ፤ ሰውየውም አሳማ+ እንዲጠብቅለት ወደ ሜዳ ላከው። 16  እሱም አሳማዎቹ የሚመገቡትን ምግብ በልቶ ለመጥገብ ይመኝ ነበር፤ ነገር ግን የሚሰጠው አልነበረም። 17  “ወደ ልቦናው ሲመለስ ግን እንዲህ አለ፦ ‘ስንቶቹ የአባቴ ቅጥር ሠራተኞች ምግብ ተርፏቸው እኔ እዚህ በረሃብ ልሞት ነው! 18  ተነስቼ ወደ አባቴ በመሄድ እንዲህ እለዋለሁ፦ “አባቴ ሆይ፣ በአምላክና* በአንተ ላይ በደል ፈጽሜአለሁ። 19  ከእንግዲህ ልጅህ ተብዬ ልጠራ አይገባኝም። ከቅጥር ሠራተኞችህ እንደ አንዱ አድርገኝ።”’ 20  ስለዚህ ተነስቶ ወደ አባቱ ሄደ። ገና ሩቅ ሳለም አባቱ አየው፤ በዚህ ጊዜ አንጀቱ ተላወሰ፤ እየሮጠ ሄዶም አንገቱ ላይ ተጠምጥሞ ሳመው። 21  ከዚያም ልጁ ‘አባቴ ሆይ፣ በአምላክና በአንተ ላይ በደል ፈጽሜአለሁ።+ ከእንግዲህ ልጅህ ተብዬ ልጠራ አይገባኝም’ አለው። 22  አባትየው ግን ባሪያዎቹን እንዲህ አላቸው፦ ‘ቶሎ በሉ! ምርጥ የሆነውን ልብስ አምጥታችሁ አልብሱት፤ ለእጁ ቀለበት፣ ለእግሩም ጫማ አድርጉለት። 23  የሰባውንም ጥጃ አምጥታችሁ እረዱ፤ እንብላ፤ እንደሰት። 24  ይህ ልጄ ሞቶ ነበርና፤ አሁን ግን ሕያው ሆኗል።+ ጠፍቶ ነበር፤ ተገኝቷል።’ ከዚያም ይደሰቱ ጀመር። 25  “በዚህ ጊዜ ታላቁ ልጅ በእርሻ ቦታ ነበር፤ ተመልሶ መጥቶ ወደ ቤት በተቃረበ ጊዜ የሙዚቃና የጭፈራ ድምፅ ሰማ። 26  ስለዚህ ከአገልጋዮቹ አንዱን ጠርቶ ነገሩ ምን እንደሆነ ጠየቀው። 27  አገልጋዩም ‘ወንድምህ መጥቷል፤ በደህና ስለመጣም አባትህ የሰባውን ጥጃ አርዶለታል’ አለው። 28  እሱ ግን ተቆጣ፤ ወደ ቤት ለመግባትም አሻፈረኝ አለ። ከዚያም አባቱ ወጥቶ ይለምነው ጀመር። 29  እሱም መልሶ አባቱን እንዲህ አለው፦ ‘እነሆ፣ እኔ ስንት ዓመት ሙሉ እንደ ባሪያ ሳገለግልህ ኖርኩ፤ መቼም ቢሆን ከትእዛዝህ ዝንፍ ብዬ አላውቅም፤ አንተ ግን ከጓደኞቼ ጋር እንድደሰት አንዲት የፍየል ጠቦት እንኳ ሰጥተኸኝ አታውቅም። 30  ሆኖም ሀብትህን ከዝሙት አዳሪዎች ጋር ያወደመው* ይህ ልጅህ ገና ከመምጣቱ የሰባውን ጥጃ አረድክለት።’ 31  በዚህ ጊዜ አባቱ እንዲህ አለው፦ ‘ልጄ፣ አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር ነህ፤ ደግሞም የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው። 32  ሆኖም ይህ ወንድምህ ሞቶ ነበር፤ አሁን ግን ሕያው ሆኗል፤ ጠፍቶ ነበር፤ ተገኝቷል። ስለዚህ ልንደሰትና ሐሴት ልናደርግ ይገባል።’”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ለ14ን ተመልከት።
ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ሴቶች ጓደኞቿንና ጎረቤቶቿን።”
ለ14ን ተመልከት።
ወይም “የንዝህላልነት።”
ቃል በቃል “በሰማይና።”
ቃል በቃል “የበላው።”