የሉቃስ ወንጌል 21:1-38
21 ኢየሱስ ቀና ብሎ ሲመለከት ሀብታሞች በመዋጮ ሣጥኖቹ* ውስጥ መባቸውን ሲከቱ አየ።+
2 ከዚያም አንዲት ድሃ መበለት በጣም አነስተኛ ዋጋ ያላቸው ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች* ስትከት+ አይቶ
3 እንዲህ አለ፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከሁሉ የበለጠ የሰጠችው ይህች ድሃ መበለት ነች።+
4 ሁሉም መባ የሰጡት ከትርፋቸው ነውና፤ እሷ ግን በድሃ አቅሟ ያላትን መተዳደሪያ ሁሉ ሰጥታለች።”+
5 በኋላም አንዳንዶች ቤተ መቅደሱ ውብ በሆኑ ድንጋዮችና ለአምላክ በተሰጡ ስጦታዎች እንዴት እንዳጌጠ+ በተናገሩ ጊዜ
6 “ይህ የምታዩት ነገር ሁሉ የሚፈርስበት ጊዜ ይመጣል፤ እንዲህ ድንጋይ በድንጋይ ላይ እንደተነባበረ አይኖርም” አለ።+
7 እነሱም “መምህር፣ እነዚህ ነገሮች በእርግጥ የሚፈጸሙት መቼ ነው? እነዚህ ነገሮች የሚፈጸሙበትን ጊዜ የሚጠቁመው ምልክትስ ምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት።+
8 እሱም እንዲህ አለ፦ “እንዳያሳስቷችሁ ተጠንቀቁ፤+ ብዙዎች ‘እኔ እሱ ነኝ’ እንዲሁም ‘ጊዜው ቀርቧል’ እያሉ በስሜ ይመጣሉና። እነሱን አትከተሉ።+
9 በተጨማሪም ስለ ጦርነትና ብጥብጥ* ስትሰሙ አትሸበሩ። በመጀመሪያ እነዚህ ነገሮች መፈጸም አለባቸውና፤ ፍጻሜው ግን ወዲያው አይመጣም።”+
10 ከዚያም እንዲህ አላቸው፦ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣+ መንግሥትም በመንግሥት ላይ+ ይነሳል።
11 ታላላቅ የምድር ነውጦች ይከሰታሉ፤ በተለያየ ስፍራም የምግብ እጥረትና ቸነፈር ይሆናል፤+ ደግሞም የሚያስፈሩ ነገሮች እንዲሁም ከሰማይ ታላላቅ ምልክቶች ይታያሉ።
12 “እነዚህ ሁሉ ነገሮች ከመፈጸማቸው በፊት ግን ሰዎች ይይዟችኋል፤ ስደት ያደርሱባችኋል+ እንዲሁም ለምኩራብና ለወህኒ ቤት አሳልፈው ይሰጧችኋል። በስሜም ምክንያት በነገሥታትና በገዢዎች ፊት ያቀርቧችኋል።+
13 ይህም ለመመሥከር የሚያስችል አጋጣሚ ይከፍትላችኋል።
14 የምትሰጡትን መልስ አስቀድማችሁ መዘጋጀት እንደማያስፈልጋችሁ ልብ በሉ፤+
15 ተቃዋሚዎቻችሁ ሁሉ በአንድነት ሆነው ሊቋቋሙት ወይም ሊከራከሩት የማይችሉት አንደበትና ጥበብ እሰጣችኋለሁና።+
16 ከዚህም በተጨማሪ ወላጆቻችሁ፣ ወንድሞቻችሁ፣ ዘመዶቻችሁና ጓደኞቻችሁ እንኳ አሳልፈው ይሰጧችኋል፤* አንዳንዶቻችሁንም ይገድላሉ፤+
17 በስሜ የተነሳም ሰዎች ሁሉ ይጠሏችኋል።+
18 ይሁን እንጂ ከራሳችሁ ፀጉር አንዷ እንኳ አትጠፋም።+
19 ከጸናችሁ ሕይወታችሁን ታተርፋላችሁ።*+
20 “ይሁንና ኢየሩሳሌም በጦር ሠራዊት ተከባ ስታዩ+ መጥፊያዋ እንደቀረበ እወቁ።+
21 በዚህ ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፤+ በከተማዋ ውስጥ ያሉም ከዚያ ይውጡ፤ በገጠር ያሉም ወደ እሷ አይግቡ፤
22 ምክንያቱም የተጻፈው ነገር ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይህ የፍትሕ እርምጃ የሚወሰድበት ጊዜ* ነው።
23 በእነዚያ ቀናት ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው!+ ምክንያቱም በምድሪቱ ላይ ታላቅ መከራ፣ በዚህ ሕዝብም ላይ ቁጣ ይመጣል።
24 በሰይፍ ስለትም ይወድቃሉ፤ ተማርከውም ወደየአገሩ ይወሰዳሉ፤+ የተወሰኑት የአሕዛብ* ዘመናት እስኪፈጸሙ ድረስም ኢየሩሳሌም በአሕዛብ* ትረገጣለች።+
25 “እንዲሁም በፀሐይ፣ በጨረቃና በከዋክብት ላይ ምልክቶች ይታያሉ፤+ በምድርም ላይ ሕዝቦች ከባሕሩ ድምፅና ነውጥ የተነሳ የሚያደርጉት ጠፍቷቸው ይጨነቃሉ።
26 የሰማያት ኃይላት ስለሚናወጡ ሰዎች ከፍርሃትና በዓለም ላይ የሚመጡትን ነገሮች ከመጠበቅ የተነሳ ይዝለፈለፋሉ።
27 ከዚያም የሰው ልጅ+ በኃይልና በታላቅ ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል።+
28 ሆኖም እነዚህ ነገሮች መከሰት ሲጀምሩ መዳናችሁ እየቀረበ ስለሆነ ቀጥ ብላችሁ ቁሙ፤ ራሳችሁንም ቀና አድርጉ።”
29 ከዚያም እንዲህ ሲል አንድ ምሳሌ ነገራቸው፦ “የበለስ ዛፍንና ሌሎች ዛፎችን ሁሉ ተመልከቱ።+
30 ዛፎቹ ሲያቆጠቁጡ ራሳችሁ አይታችሁ በጋ* እንደቀረበ ታውቃላችሁ።
31 በተመሳሳይ እናንተም እነዚህ ነገሮች ሲፈጸሙ ስታዩ የአምላክ መንግሥት እንደቀረበ እርግጠኞች ሁኑ።
32 እውነት እላችኋለሁ፣ እነዚህ ነገሮች ሁሉ እስኪፈጸሙ ድረስ ይህ ትውልድ ፈጽሞ አያልፍም።+
33 ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን ፈጽሞ አያልፍም።+
34 “ይሁንና ከልክ በላይ በመብላትና በመጠጣት+ እንዲሁም ስለ ኑሮ በመጨነቅ+ ልባችሁ ሸክም እንዳይበዛበት ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ አለዚያ ያ ቀን ድንገት ሳታስቡት
35 እንደ ወጥመድ+ ይመጣባችኋል። ይህ በመላው ምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ ይደርስባቸዋልና።
36 እንግዲያው መፈጸማቸው ከማይቀረው ከእነዚህ ሁሉ ነገሮች ማምለጥና በሰው ልጅ ፊት መቆም እንድትችሉ+ ሁልጊዜ ምልጃ እያቀረባችሁ+ ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ።”+
37 ኢየሱስ ቀን ቀን በቤተ መቅደስ ያስተምር ነበር፤ ሲመሽ ግን ወጥቶ ደብረ ዘይት በተባለው ተራራ ያድር ነበር።
38 ሕዝቡም ሁሉ በቤተ መቅደስ እሱን ለመስማት በማለዳ ወደ እሱ ይመጡ ነበር።
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “ዕቃዎቹ።”
^ ወይም “ረብሻ፤ ዓመፅ።”
^ ወይም “ይከዷችኋል።”
^ ወይም “ነፍሳችሁን ታገኛላችሁ።”
^ ወይም “የበቀል ቀን።”
^ ወይም “የብሔራት።”
^ ወይም “በብሔራት።”
^ በጳለስጢና ምድር ዕፀዋት የሚለመልሙት በበጋ ነው።