የሉቃስ ወንጌል 23:1-56

  • ኢየሱስ ጲላጦስና ሄሮድስ ፊት ቀረበ (1-25)

  • ኢየሱስና ሁለት ወንጀለኞች በእንጨት ላይ ተሰቀሉ (26-43)

    • “ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” (43)

  • ኢየሱስ ሞተ (44-49)

  • ኢየሱስ ተቀበረ (50-56)

23  ስለዚህ በዚያ ተሰብስበው የነበሩት ሰዎች በሙሉ ተነስተው ወደ ጲላጦስ ወሰዱት።+ 2  ከዚያም እንዲህ እያሉ ይከሱት ጀመር፦+ “ይህ ሰው ሕዝባችንን ሲያሳምፅ፣ ለቄሳር ግብር እንዳይከፈል ሲከለክልና+ ‘እኔ ክርስቶስ ንጉሥ ነኝ’+ ሲል አግኝተነዋል።” 3  በዚህ ጊዜ ጲላጦስ “አንተ የአይሁዳውያን ንጉሥ ነህ?” ሲል ጠየቀው። እሱም መልሶ “አንተው ራስህ እኮ እየተናገርከው ነው” አለው።+ 4  ከዚያም ጲላጦስ ለካህናት አለቆቹና ለሕዝቡ “በዚህ ሰው ላይ ምንም ወንጀል አላገኘሁበትም” አለ።+ 5  እነሱ ግን “በመላው ይሁዳ፣ ከገሊላ አንስቶ እስከዚህ ድረስ እያስተማረ ሕዝቡን ይቀሰቅሳል” በማለት አጥብቀው ተናገሩ። 6  ጲላጦስ ይህን ሲሰማ ሰውየው የገሊላ ሰው መሆኑን ለማረጋገጥ ጠየቀ። 7  ከሄሮድስ+ ግዛት የመጣ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ በዚያን ጊዜ በኢየሩሳሌም ወደነበረው ወደ ሄሮድስ ላከው። 8  ሄሮድስ ኢየሱስን ሲያየው በጣም ደስ አለው። ስለ እሱ ብዙ ነገር ሰምቶ ስለነበር+ ለረጅም ጊዜ እሱን ለማየት ይፈልግ ነበር፤ አንዳንድ ተአምራት ሲፈጽም ለማየትም ተስፋ ያደርግ ነበር። 9  በመሆኑም ብዙ ጥያቄ ይጠይቀው ጀመር፤ እሱ ግን ምንም መልስ አልሰጠውም።+ 10  ይሁን እንጂ የካህናት አለቆቹና ጸሐፍት በተደጋጋሚ እየተነሱ አጥብቀው ይከሱት ነበር። 11  ከዚያም ሄሮድስ ከወታደሮቹ ጋር ሆኖ አቃለለው፤+ እንዲሁም ያማረ ልብስ አልብሶ ካፌዘበት+ በኋላ መልሶ ወደ ጲላጦስ ላከው። 12  በዚያን ዕለት ሄሮድስና ጲላጦስ ወዳጆች ሆኑ፤ ከዚያ በፊት በመካከላቸው ጠላትነት ነበር። 13  ከዚያም ጲላጦስ የካህናት አለቆቹን፣ ገዢዎቹንና ሕዝቡን በአንድነት ጠርቶ 14  እንዲህ አላቸው፦ “ይህን ሰው ወደ እኔ ያመጣችሁት ሕዝቡን ለዓመፅ ያነሳሳል ብላችሁ ነበር። ይኸው በፊታችሁ መረመርኩት፤ ሆኖም በእሱ ላይ ያቀረባችሁትን ክስ የሚደግፍ ምንም ነገር አላገኘሁም።+ 15  ሄሮድስም ቢሆን ምንም ጥፋት ስላላገኘበት ወደ እኛ መልሶ ልኮታል፤ በመሆኑም ለሞት የሚያበቃ ምንም ነገር አልፈጸመም። 16  ስለዚህ ቀጥቼ+ እፈታዋለሁ።” 17  *—— 18  ሕዝቡ ሁሉ ግን “ይህን ሰው ግደለው፤* በርባንን ግን ፍታልን!” እያሉ ጮኹ።+ 19  (ይህ ሰው በከተማው ውስጥ በተከሰተ የሕዝብ ዓመፅና በነፍስ ግድያ የታሰረ ነበር።) 20  ጲላጦስ ኢየሱስን ሊፈታው ስለፈለገ ድምፁን ከፍ አድርጎ እንደገና ለሕዝቡ ተናገረ።+ 21  እነሱ ግን “ይሰቀል! ይሰቀል!”* እያሉ ይጮኹ ጀመር።+ 22  እሱም ለሦስተኛ ጊዜ “ለምን? ይህ ሰው ምን ያጠፋው ነገር አለ? ለሞት የሚያበቃ ምንም ነገር አላገኘሁበትም፤ ስለዚህ ቀጥቼ እፈታዋለሁ” አላቸው። 23  በዚህ ጊዜ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ኢየሱስ እንዲገደል* አጥብቀው ወተወቱት፤ ድምፃቸውም አየለ።+ 24  ስለዚህ ጲላጦስ የጠየቁት እንዲፈጸም ውሳኔ አስተላለፈ። 25  ሕዝብ በማሳመፅና በነፍስ ግድያ ታስሮ የነበረውንና እንዲፈታላቸው የጠየቁትን ሰው ለቀቀው፤ ኢየሱስን ግን የፈለጉትን እንዲያደርጉበት አሳልፎ ሰጣቸው። 26  ይዘውትም እየሄዱ ሳሉ ከገጠር እየመጣ የነበረውን ስምዖን የተባለ አንድ የቀሬና ሰው ያዙትና የመከራውን እንጨት* አሸክመው ከኢየሱስ ኋላ እንዲሄድ አደረጉት።+ 27  ብዙ ሕዝብም ይከተለው ነበር፤ ከእነሱም መካከል በሐዘን ደረታቸውን እየደቁ የሚያለቅሱለት ሴቶች ነበሩ። 28  ኢየሱስም ወደ ሴቶቹ ዞር ብሎ እንዲህ አለ፦ “እናንተ የኢየሩሳሌም ልጆች፣ ለእኔ አታልቅሱ። ይልቁንስ ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ፤+ 29  ሰዎች ‘መሃን የሆኑ ሴቶች፣ ያልወለዱ ማህፀኖችና ያላጠቡ ጡቶች ደስተኞች ናቸው!’+ የሚሉበት ቀን ይመጣልና። 30  በዚያን ጊዜ ተራሮችን ‘በላያችን ውደቁ!’ ኮረብቶችንም ‘ሸሽጉን!’ ይላሉ።+ 31  ዛፉ እርጥብ ሆኖ ሳለ እንዲህ ካደረጉ በደረቀ ጊዜማ ምን ይከሰት ይሆን?” 32  ወንጀለኞች የሆኑ ሌሎች ሁለት ሰዎችም ከእሱ ጋር ሊገደሉ እየተወሰዱ ነበር።+ 33  የራስ ቅል+ ወደተባለ ቦታ በደረሱ ጊዜ ኢየሱስን በዚያ ከወንጀለኞቹ ጋር በእንጨት ላይ ቸነከሩት፤ ወንጀለኞቹም አንዱ በቀኙ ሌላው ደግሞ በግራው ተሰቅለው ነበር።+ 34  ኢየሱስም “አባት ሆይ፣ የሚያደርጉትን ስለማያውቁ ይቅር በላቸው” ይል ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ልብሶቹን ለመከፋፈል ዕጣ ተጣጣሉ።+ 35  ሕዝቡም ቆሞ ይመለከት ነበር። የሃይማኖት መሪዎቹ ግን* “ሌሎችን አዳነ፤ የተመረጠው የአምላክ ክርስቶስ እሱ ከሆነ እስቲ ራሱን ያድን” እያሉ ያፌዙበት ነበር።+ 36  ወታደሮቹ እንኳ ሳይቀሩ ወደ እሱ ቀርበው የኮመጠጠ የወይን ጠጅ በመስጠት+ አፌዙበት፤ 37  እንዲሁም “አንተ የአይሁዳውያን ንጉሥ ከሆንክ ራስህን አድን” ይሉት ነበር። 38  በተጨማሪም ከበላዩ “ይህ የአይሁዳውያን ንጉሥ ነው” የሚል ጽሑፍ ነበር።+ 39  ከዚያም በዚያ ከተሰቀሉት ወንጀለኞች አንዱ “አንተ ክርስቶስ አይደለህም እንዴ? እስቲ ራስህንም እኛንም አድን!” እያለ ይዘልፈው+ ጀመር። 40  ሌላኛው ግን መልሶ እንዲህ ሲል ገሠጸው፦ “አንተ ራስህ ተመሳሳይ ፍርድ ተቀብለህ እያለ ትንሽ እንኳ አምላክን አትፈራም? 41  እኛስ ላደረግነው ነገር የሚገባንን ቅጣት በሙሉ እየተቀበልን ስለሆነ በእኛ ላይ የተፈጸመው ፍርድ ተገቢ ነው፤ ይህ ሰው ግን ምንም የሠራው ጥፋት የለም።” 42  ቀጥሎም “ኢየሱስ ሆይ፣ ወደ መንግሥትህ ስትመጣ አስበኝ” አለው።+ 43  እሱም “እውነት እልሃለሁ ዛሬ፣ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” አለው።+ 44  ጊዜው ስድስት ሰዓት ገደማ የነበረ ቢሆንም ምድሪቱ በሙሉ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በጨለማ ተሸፈነች፤+ 45  ይህም የሆነው የፀሐይ ብርሃን በመጥፋቱ ነው፤ ከዚያም የቤተ መቅደሱ መጋረጃ+ መሃል ለመሃል ተቀደደ።+ 46  ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ “አባት ሆይ፣ መንፈሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ”+ አለ። ይህን ካለ በኋላ ሞተ።*+ 47  መኮንኑም የተፈጸመውን ነገር በማየቱ “ይህ ሰው በእርግጥ ጻድቅ ነበር”+ በማለት ለአምላክ ክብር ይሰጥ ጀመር። 48  ይህን ለማየት በቦታው ተሰብስበው የነበሩ ሰዎች ሁሉ የተከሰቱትን ነገሮች ሲመለከቱ በሐዘን ደረታቸውን እየደቁ ወደ ቤታቸው ተመለሱ። 49  በቅርብ የሚያውቁትም ሁሉ በርቀት ቆመው ነበር። እንዲሁም ከገሊላ አንስቶ አብረውት የተጓዙት ሴቶች በዚያ ተገኝተው እነዚህን ነገሮች ይመለከቱ ነበር።+ 50  እነሆም፣ የሸንጎ* አባል የሆነ ዮሴፍ የሚባል አንድ ጥሩና ጻድቅ ሰው ነበረ።+ 51  (ይህ ሰው ሴራቸውንና ድርጊታቸውን በመደገፍ ድምፅ አልሰጠም ነበር።) እሱም የአይሁዳውያን ከተማ የሆነችው የአርማትያስ ሰው ሲሆን የአምላክን መንግሥት ይጠባበቅ ነበር። 52  ይህም ሰው ጲላጦስ ፊት ቀርቦ የኢየሱስ አስከሬን እንዲሰጠው ጠየቀ። 53   አስከሬኑንም አውርዶ+ በበፍታ ገነዘው፤ ከዚያም ማንም ሰው ተቀብሮበት በማያውቅ ከዓለት ተፈልፍሎ በተሠራ መቃብር ውስጥ አኖረው።+ 54  ዕለቱ የዝግጅት ቀን ነበር፤+ ሰንበት+ የሚጀምርበት ጊዜም ተቃርቦ ነበር። 55  ከገሊላ ከኢየሱስ ጋር አብረው የመጡት ሴቶች ግን ተከትለው በመሄድ መቃብሩን አዩ፤ አስከሬኑም እንዴት እንዳረፈ ተመለከቱ።+ 56  ጥሩ መዓዛ ያላቸው ቅመሞችና ዘይቶች ለማዘጋጀትም ተመልሰው ሄዱ። ሆኖም ሕጉ በሚያዘው መሠረት በሰንበት አረፉ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ3ን ተመልከት።
ቃል በቃል “ይህን አስወግደው።”
ወይም “እንጨት ላይ ይሰቀል! እንጨት ላይ ይሰቀል!”
ወይም “በእንጨት ላይ እንዲሰቀል።”
ቃል በቃል “ገዢዎቹ ግን።”
ወይም “እስትንፋሱ ቆመ።”
ወይም “የሳንሄድሪን።”