ሕዝቅኤል 10:1-22
10 እኔም እያየሁ ሳለ ከኪሩቦቹ ራስ በላይ ካለው ጠፈር በላይ እንደ ሰንፔር ድንጋይ ያለ ነገር ተገለጠ፤ መልኩም ዙፋን ይመስል ነበር።+
2 ከዚያም አምላክ በፍታ የለበሰውን ሰው+ “በኪሩቦቹ ሥር ወደሚገኙት የሚሽከረከሩ መንኮራኩሮች*+ መሃል ግባና በኪሩቦቹ መካከል ካለው ፍም+ በእጆችህ ዘግነህ በከተማዋ ላይ በትነው”+ አለው። እሱም እኔ እያየሁት ገባ።
3 ሰውየው ወደዚያ ሲገባ ኪሩቦቹ ከቤተ መቅደሱ በስተ ቀኝ ቆመው ነበር፤ ደመናውም የውስጠኛውን ግቢ ሞላው።
4 የይሖዋም ክብር+ ከኪሩቦቹ ላይ ተነስቶ ወደ ቤተ መቅደሱ በር ደጃፍ ሄደ፤ ቤተ መቅደሱም ቀስ በቀስ በደመናው ተሞላ፤+ ግቢውም በይሖዋ ክብር ብርሃን ተሞላ።
5 የኪሩቦቹም ክንፎች ድምፅ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ሲናገር እንደሚሰማው ድምፅ እስከ ውጨኛው ግቢ ድረስ ይሰማ ነበር።+
6 ከዚያም አምላክ፣ በፍታ የለበሰውን ሰው “ከሚሽከረከሩት መንኮራኩሮች መካከልና ከኪሩቦቹ መሃል እሳት ውሰድ” ብሎ አዘዘው፤ ሰውየውም ገብቶ ከመንኮራኩሩ አጠገብ ቆመ።
7 ከዚያም አንዱ ኪሩብ፣ በኪሩቦቹ መካከል ወዳለው እሳት+ እጁን ዘረጋ። የተወሰነ እሳት ወስዶ በፍታ በለበሰው ሰው+ እጆች ላይ አደረገ፤ እሱም እሳቱን ይዞ ወጣ።
8 ኪሩቦቹ ከክንፎቻቸው ሥር የሰው እጅ የሚመስል ነገር ነበራቸው።+
9 እኔም እያየሁ ሳለ በኪሩቦቹ አጠገብ አራት መንኮራኩሮች ተመለከትኩ፤ በእያንዳንዱ ኪሩብ አጠገብ አንድ መንኮራኩር ነበር፤ መንኮራኩሮቹም እንደ ክርስቲሎቤ ድንጋይ የሚያብረቀርቅ መልክ ነበራቸው።+
10 የአራቱም መልክ ይመሳሰል ነበር፤ በአንድ መንኮራኩር ውስጥ በጎን በኩል ሌላ መንኮራኩር የተሰካ ይመስል ነበር።
11 በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ መዞር ሳያስፈልጋቸው በአራቱም አቅጣጫ መሄድ ይችሉ ነበር፤ ምክንያቱም መዞር ሳያስፈልጋቸው ፊታቸው ወደሚያይበት* አቅጣጫ ሁሉ ይሄዱ ነበር።
12 ሰውነታቸው ሁሉ፣ ጀርባቸው፣ እጃቸው፣ ክንፋቸው እንዲሁም መንኮራኩሮቹ ይኸውም የአራቱም መንኮራኩሮች ሁለመና በዓይን የተሞላ ነበር።+
13 አንድ ድምፅ መንኮራኩሮቹን “ተሽከርካሪ መንኮራኩሮች!” ብሎ ሲጠራቸው ሰማሁ።
14 እያንዳንዳቸው* አራት አራት ፊት ነበራቸው። የመጀመሪያው ፊት የኪሩብ ፊት፣ ሁለተኛው ፊት የሰው ፊት፣ ሦስተኛውም የአንበሳ ፊት፣ አራተኛው ደግሞ የንስር ፊት ነበር።+
15 ኪሩቦቹም ወደ ላይ ተነሱ፤ በኬባር ወንዝ+ ያየኋቸው ሕያዋን ፍጥረታት እነዚሁ ነበሩ፤*
16 ኪሩቦቹ ሲንቀሳቀሱ፣ መንኮራኩሮቹም አጠገባቸው ሆነው ይንቀሳቀሱ ነበር፤ ኪሩቦቹ ከምድር በላይ ከፍ ከፍ ለማለት ክንፎቻቸውን ወደ ላይ ሲዘረጉ መንኮራኩሮቹ ከአጠገባቸው አይለዩም ወይም አይርቁም ነበር።+
17 እነሱ ሲቆሙ፣ መንኮራኩሮቹም ይቆማሉ፤ እነሱ ከፍ ከፍ ሲሉ መንኮራኩሮቹም አብረዋቸው ከፍ ከፍ ይሉ ነበር፤ በሕያዋን ፍጥረታቱ ላይ የሚሠራው መንፈስ* በውስጣቸው ነበርና።
18 ከዚያም የይሖዋ ክብር+ ከቤተ መቅደሱ በር ደጃፍ ተነስቶ በመሄድ ከኪሩቦቹ በላይ ቆመ።+
19 ኪሩቦቹ እኔ እያየኋቸው ክንፎቻቸውን ወደ ላይ ዘርግተው ከምድር ተነሱ። እነሱ ሲሄዱ መንኮራኩሮቹም አብረዋቸው ነበሩ። በይሖዋ ቤት በስተ ምሥራቅ በሚገኘው በር መግቢያም ላይ ቆሙ፤ የእስራኤል አምላክ ክብርም በላያቸው ነበር።+
20 እነዚህ በኬባር ወንዝ አቅራቢያ ከእስራኤል አምላክ በታች ያየኋቸው ሕያዋን ፍጥረታት ናቸው፤+ በመሆኑም ኪሩቦች መሆናቸውን አወቅኩ።
21 አራቱም፣ አራት አራት ፊትና አራት አራት ክንፍ ነበራቸው፤ ከክንፎቻቸውም ሥር የሰው እጆች የሚመስሉ ነገሮች ነበሯቸው።+
22 የፊታቸውም መልክ በኬባር ወንዝ አቅራቢያ እንዳየኋቸው ፊቶች ነበር።+ እያንዳንዳቸው ቀጥ ብለው ወደ ፊት ይሄዱ ነበር።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ የሠረገላ ተሽከርካሪ እግር።
^ ቃል በቃል “ራስ ወዳለበት።”
^ እያንዳንዱን ኪሩብ ያመለክታል።
^ ቃል በቃል “ያየሁት ሕያው ፍጡር ይኸው ነበር።”
^ ቃል በቃል “የሕያው ፍጡሩ መንፈስ።”