ሕዝቅኤል 19:1-14

  • ስለ እስራኤል አለቆች የተነገረ ሙሾ (1-14)

19  “ስለ እስራኤል አለቆች ሙሾ አውጣ፤*  እንዲህም በል፦‘እናትህ ምን ነበረች? በአንበሶች መካከል ያለች እንስት አንበሳ ነበረች። በብርቱ ደቦል አንበሶች መሃል ተኛች፤ ግልገሎቿንም በዚያ አሳደገች።   ከግልገሎቿ መካከል አንዱን ተንከባክባ አሳደገችው፤ እሱም ብርቱ ደቦል አንበሳ ሆነ።+ አድኖ መብላት ተማረ፤ሰዎችንም እንኳ ሳይቀር በላ።   ብሔራት ስለ እሱ ሰሙ፤ ጉድጓዳቸው ውስጥ ገብቶም ያዙት፤በስናግም እየጎተቱ ወደ ግብፅ ምድር አመጡት።+   እሷም በትዕግሥት ስትጠባበቅ ከቆየች በኋላ የመመለስ ተስፋ እንደሌለው ተገነዘበች። በመሆኑም ከግልገሎቿ መካከል ሌላውን ወስዳ እንደ ብርቱ ደቦል አንበሳ አድርጋ ላከችው።   እሱም በአንበሶች መካከል ይጎማለል ጀመር፤ ብርቱ ደቦል አንበሳም ሆነ። አድኖ መብላት ተማረ፤ ሰዎችንም እንኳ ሳይቀር በላ።+   በማይደፈሩት ማማዎቻቸው መካከል አደባ፤ ከተሞቻቸውንም አወደመ፤ከዚህም የተነሳ ግሳቱ ወና በሆነችው ምድር ላይ አስተጋባ።+   በዙሪያው ባሉ ግዛቶች ያሉ ብሔራት መረባቸውን በእሱ ላይ ለመዘርጋት ተነሱበት፤እሱም ጉድጓዳቸው ውስጥ ገብቶ ተያዘ።   በስናግ ጎትተው በእንስሳት ጎጆ ውስጥ በመክተት ወደ ባቢሎን ንጉሥ አመጡት። ከዚያ በኋላ ድምፁ በእስራኤል ተራሮች ላይ እንዳይሰማ በዚያ አሰሩት። 10  እናትህ በውኃዎች አጠገብ እንደተተከለ፣ በደምህ ውስጥ ያለ የወይን ተክል* ነበረች።+ ከውኃው ብዛት የተነሳ ፍሬ አፈራች፤ ብዙ ቅርንጫፎችም ነበሯት። 11  ለገዢዎች በትረ መንግሥት የሚሆኑ ጠንካራ ቅርንጫፎች* አወጣች። አድጋ ከሌሎች ዛፎች ይበልጥ ረጅም ሆነች፤ደግሞም ከርዝመቷና ከቅጠሎቿ ብዛት የተነሳ ጎልታ ታየች። 12  ሆኖም በቁጣ ተነቀለች፤+ ወደ ምድርም ተጣለች፤የምሥራቅም ነፋስ ፍሬዋን አደረቀው። ጠንካራ ቅርንጫፎቿ ተሰብረው ደረቁ፤+ እሳትም በላቸው።+ 13  በዚህ ጊዜ በምድረ በዳ፣ውኃ በሌለበት ደረቅ ምድር ተተከለች።+ 14  እሳት ከቅርንጫፎቿ* ወጥቶ ቀንበጦቿንና ፍሬዋን በላ፤በእሷም ላይ አንድም ጠንካራ ቅርንጫፍ፣ ለገዢዎችም የሚሆን በትረ መንግሥት አልተረፈም።+ “‘ይህ ሙሾ ነው፤ ሙሾ ሆኖም ያገለግላል።’”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “የሐዘን እንጉርጉሮ አሰማ።”
“በወይን እርሻህ ውስጥ እንዳለ የወይን ተክል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ዘንጎች።”
ወይም “እሳት ከዘንጎቿ።”