ሕዝቅኤል 24:1-27

  • እንደዛገ ድስት የሆነችው ኢየሩሳሌም (1-14)

  • የሕዝቅኤል ሚስት ሞት እንደ ምልክት ሆኖ ያገለግላል (15-27)

24  የይሖዋ ቃል በዘጠነኛው ዓመት፣ በአሥረኛው ወር፣ ከወሩም በአሥረኛው ቀን እንዲህ ሲል ዳግመኛ ወደ እኔ መጣ፦  “የሰው ልጅ ሆይ፣ ይህን ቀን፣* አዎ ይህንኑ ቀን መዝግብ። የባቢሎን ንጉሥ በዚሁ ቀን በኢየሩሳሌም ላይ ጥቃት መሰንዘር ጀምሯል።+  ዓመፀኛውን ቤት አስመልክቶ ምሳሌ* ተናገር፤ ስለ እነሱም እንዲህ በል፦ “‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ድስቱን* ጣደው፤ እሳት ላይ ጣደው፤ ውኃም ጨምርበት።+   ጭኑንና ወርቹን ጨምሮ ጥሩ ጥሩ የሆነውን ሙዳ ሥጋ ሁሉ ሰብስበህ ጨምርበት፤+ምርጥ የሆኑ አጥንቶችንም ሙላበት።   ከመንጋው ምርጥ የሆነውን በግ ውሰድ፤+ በድስቱም ሥር ዙሪያውን ማገዶ ጨምር። ሥጋውን ቀቅለው፤ በውስጡ ያለውንም አጥንት አብስለው።”’  “ስለዚህ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘የዛገ ድስት ለሆነችውና ዝገቷ ላለቀቀው እንዲሁም ደም አፍሳሽ ለሆነችው ከተማ ወዮላት!+ ሥጋውን አንድ በአንድ አውጣ፤+ ዕጣ መጣል አያስፈልግህም።   ያፈሰሰችው ደም በውስጧ ይገኛልና፤+ በገላጣ ዓለት ላይ አፍስሳዋለች። በአፈር እንዲሸፈን መሬት ላይ አላፈሰሰችውም።+   ቁጣዬ ተነሳስቶ እበቀላት ዘንድያፈሰሰችው ደም እንዳይሸፈንደሙን በሚያንጸባርቅ ገላጣ ዓለት ላይ አደረግኩት።’+   “ስለዚህ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ደም አፍሳሽ ለሆነችው ከተማ ወዮላት!+ ማገዶውን እቆልለዋለሁ። 10  እንጨቱን ከምር፤ እሳቱን አቀጣጥል፤ሥጋውን በደንብ ቀቅል፤ መረቁን አፍስ፤ አጥንቶቹም ይረሩ። 11  ባዶውን ድስት እንዲግል ፍሙ ላይ ጣደው፤መዳቡም በጣም ይግላል። ቆሻሻው በውስጡ ይቀልጣል፤+ ዝገቱንም እሳት ይበላዋል። 12  ድስቱ በጣም ከመዛጉ የተነሳ ስለማይለቅ ከንቱ ልፋት ነው፤ደግሞም እንዲሁ ድካም ብቻ ነው።+ ከነዝገቱ እሳት ውስጥ ጣለው!’ 13  “‘በጸያፍ ምግባርሽ የተነሳ ረክሰሻል።+ ላነጻሽ ሞክሬ ነበር፤ አንቺ ግን ከርኩሰትሽ ንጹሕ ልትሆኚ አትችዪም። በአንቺ ላይ ያደረብኝ ቁጣ እስኪበርድ ድረስ ንጹሕ አትሆኚም።+ 14  እኔ ይሖዋ ራሴ ይህን ተናግሬአለሁ። በእርግጥ ይፈጸማል። ምንም ሳላቅማማ፣ ያላንዳች ሐዘንና ጸጸት እርምጃ እወስዳለሁ።+ እንደ መንገድሽና እንደ ሥራሽ ይፈርዱብሻል’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ።” 15  የይሖዋም ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦ 16  “የሰው ልጅ ሆይ፣ በፊትህ ተወዳጅ የሆነውን በአንድ ምት ልወስድብህ ነው።+ አንተም ዋይታ አታሰማ* ወይም አታልቅስ ወይም ደግሞ እንባህን አታፍስ። 17  ሐዘንህን በውስጥህ አምቀህ ያዝ፤ ለሞተው በወጉ መሠረት ሐዘንህን አትግለጽ።+ ጥምጥምህን እሰር፤+ ጫማህንም አድርግ።+ ሪዝህን* አትሸፍን፤+ ሰዎች የሚያመጡልህንም ምግብ* አትብላ።”+ 18  እኔም በጠዋት ለሕዝቡ ተናገርኩ፤ ሚስቴም ማታ ላይ ሞተች። ስለሆነም ጠዋት፣ ልክ እንደታዘዝኩት አደረግኩ። 19  ሕዝቡም “ይህ የምታደርገው ነገር ለእኛ ምን መልእክት እንዳለው አትነግረንም?” አሉኝ። 20  እኔም እንዲህ አልኳቸው፦ “የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦ 21  ‘ለእስራኤል ቤት ሰዎች እንዲህ በል፦ “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እጅግ የምትኮሩበትን፣ በፊታችሁ ተወዳጅ የሆነውንና የልባችሁ ምኞት የሆነውን* መቅደሴን ላረክስ ነው።+ ትታችኋቸው የሄዳችሁት ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ።+ 22  ከዚያም እኔ እንዳደረግኩት ታደርጋላችሁ። ሪዛችሁን አትሸፍኑም፤ ሰዎች የሚያመጡላችሁንም ምግብ አትበሉም።+ 23  ጥምጥማችሁ አይፈታም፤ ጫማችሁ ከእግራችሁ ላይ አይወልቅም። ዋይታ አታሰሙም ወይም አታለቅሱም። ይልቁንም በበደላችሁ ትመነምናላችሁ፤+ አንዳችሁ ለሌላው እሮሮ ታሰማላችሁ። 24  ሕዝቅኤል ምልክት ይሆንላችኋል።+ እሱ እንዳደረገው ሁሉ ታደርጋላችሁ። ይህ በሚሆንበት ጊዜ እኔ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ።’”’” 25  “አንተም የሰው ልጅ ሆይ፣ ምሽጋቸውን ይኸውም ደስ የሚሰኙበትን ያማረ ነገር፣ በፊታቸው ተወዳጅ የሆነውን ነገርና የልባቸውን* ምኞት እንዲሁም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በምወስድባቸው ቀን፣+ 26  አምልጦ የመጣ ሰው ወሬውን ይነግርሃል።+ 27  በዚያን ቀን አፍህን ከፍተህ፣ ካመለጠው ሰው ጋር ትነጋገራለህ፤ ከዚያ በኋላ ዱዳ አትሆንም።+ ምልክት ትሆንላቸዋለህ፤ እኔም ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “የቀኑን ስም።”
ወይም “ውስጠ ወይራ ንግግር።”
ወይም “አፉ ሰፊ የሆነውን ድስት።”
ወይም “ደረትህን አትምታ።”
ወይም “የላይኛውን ከንፈርህን።”
ቃል በቃል “የሰዎችን ዳቦ።”
ወይም “ነፍሳችሁ የሚራራለትን።”
ወይም “የነፍሳቸውን።”