ሕዝቅኤል 25:1-17
25 የይሖዋ ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦
2 “የሰው ልጅ ሆይ፣ ፊትህን ወደ አሞናውያን+ አዙረህ በእነሱ ላይ ትንቢት ተናገር።+
3 አሞናውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘የሉዓላዊውን ጌታ የይሖዋን ቃል ስሙ። ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “መቅደሴ በረከሰ ጊዜና የእስራኤል ምድር ባድማ በሆነ ጊዜ እንዲሁም የይሁዳ ቤት ሰዎች በግዞት በተወሰዱ ጊዜ ‘እሰይ!’ ስላላችሁ
4 ለምሥራቅ ሰዎች ርስት አድርጌ እሰጣችኋለሁ። እነሱ በእናንተ ውስጥ ይሰፍራሉ፤* ድንኳኖቻቸውንም በመካከላችሁ ይተክላሉ። ፍሬያችሁን ይበላሉ፤ ወተታችሁንም ይጠጣሉ።
5 ራባን+ የግመሎች መሰማሪያ፣ የአሞናውያንን ምድርም መንጋ የሚያርፍበት ስፍራ አደርጋለሁ፤ እናንተም እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ።”’”
6 “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦ ‘በእጅህ ስላጨበጨብክና+ በእግርህ መሬቱን ስለመታህ እንዲሁም በእስራኤል ምድር ላይ የደረሰውን ሁኔታ ስታይ በንቀት ተሞልተህ* ሐሴት ስላደረግክ፣+
7 ብሔራት እንዲበዘብዙህ ለእነሱ አሳልፌ እሰጥህ ዘንድ እጄን በአንተ ላይ እዘረጋለሁ። ከሕዝቦች መካከል አስወግድሃለሁ፤ ከአገራትም መካከል ለይቼ አጠፋሃለሁ።+ እደመስስሃለሁ፤ እኔም ይሖዋ እንደሆንኩ ታውቃለህ።’
8 “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ሞዓብና+ ሴይር+ “እነሆ፣ የይሁዳ ቤት ልክ እንደ ሌሎቹ ብሔራት ነው” ስላሉ፣
9 በድንበሩ ላይ የሚገኙትና የምድሪቱ ውበት* የሆኑት ከተሞች ማለትም ከቤትየሺሞትና ከበዓልመዖን አንስቶ እስከ ቂርያታይም+ ድረስ ያለው የሞዓብ ክንፍ* ለጠላት እንዲጋለጥ አደርጋለሁ።
10 ከአሞናውያን ጋር ለምሥራቅ ሰዎች ርስት አድርጌ እሰጠዋለሁ፤+ ይህም አሞናውያን በብሔራት መካከል እንዳይታወሱ ለማድረግ ነው።+
11 በሞዓብም ላይ የፍርድ እርምጃ እወስዳለሁ፤+ እነሱም እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ።’
12 “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ኤዶም በቂም በቀል ተነሳስቶ በይሁዳ ቤት ላይ እርምጃ ወስዷል፤ ደግሞም እነሱን በመበቀል ከፍተኛ በደል ፈጽሟል፤+
13 ስለዚህ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እጄን በኤዶምም ላይ እዘረጋለሁ፤ ከምድሪቱም ላይ ሰውንም ሆነ ከብትን አጠፋለሁ፤ ባድማም አደርጋታለሁ።+ ከቴማን አንስቶ እስከ ዴዳን ድረስ በሰይፍ ይወድቃሉ።+
14 ‘በሕዝቤ በእስራኤል እጅ ኤዶምን እበቀላለሁ።+ እነሱም፣ ኤዶም የምወስደውን የበቀል እርምጃ ይቀምስ ዘንድ ቁጣዬንና መዓቴን በኤዶም ላይ ያወርዳሉ’+ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ።”’
15 “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ፍልስጤማውያን በማይበርድ የጠላትነት ስሜት ተነሳስተው በክፋት* የበቀል እርምጃ ለመውሰድና ጥፋት ለማድረስ ጥረት አድርገዋል።+
16 ስለዚህ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፣ በፍልስጤማውያን ላይ እጄን እዘረጋለሁ፤+ ከሪታውያንንም አጠፋለሁ፤+ በባሕሩ ዳርቻ ላይ የቀሩትንም ነዋሪዎች እደመስሳለሁ።+
17 ኃይለኛ ቅጣት በመቅጣት ታላቅ የበቀል እርምጃ እወስድባቸዋለሁ፤ በምበቀላቸውም ጊዜ እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ።”’”
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “በግንብ የታጠሩ ሰፈሮቻቸውን ይመሠርታሉ።”
^ ወይም “ነፍስህ በንቀት ተሞልታ።”
^ ወይም “የሞዓብ አቀበት።”
^ ወይም “ጌጥ።”
^ ወይም “በነፍሳቸው ንቀት።”