ሕዝቅኤል 26:1-21

  • በጢሮስ ላይ የተነገረ ትንቢት (1-21)

    • “የመረብ ማስጫ ቦታ” (5, 14)

    • ድንጋዮቿና አፈሯ ወደ ባሕር ይጣላሉ (12)

26  በ11ኛው ዓመት፣ ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦  “የሰው ልጅ ሆይ፣ ጢሮስ ስለ ኢየሩሳሌም+ ‘እሰይ! የሕዝቦች በር ተሰበረች!+ አሁን እሷ ስለጠፋች ሁሉም ነገር ይሳካልኛል፤ ደግሞም እበለጽጋለሁ’ ስላለች፣  ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ጢሮስ ሆይ፣ እነሆ በአንቺ ላይ ተነስቻለሁ፤ ባሕር ሞገዱን እንደሚያስነሳ ብዙ ብሔራትን በአንቺ ላይ አስነሳለሁ።  እነሱ የጢሮስን ቅጥሮች ያፈርሳሉ፤ ማማዎቿንም ያወድማሉ፤+ አፈሯን ከላይዋ ጠርጌ አስወግዳለሁ፤ የሚያንጸባርቅ ገላጣ ዓለትም አደርጋታለሁ።  በባሕር መካከል የመረብ ማስጫ ቦታ ትሆናለች።’+ “‘እኔ ራሴ ተናግሬአለሁና፣’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ፣ ‘ብሔራትም ይበዘብዟታል።  በገጠር ያሉ ሰፈሮቿም* በሰይፍ ይመታሉ፤ ሰዎችም እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ።’  “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦ ‘እነሆ፣ በጢሮስ ላይ የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነጾርን* ከሰሜን አመጣለሁ፤+ እሱ ፈረሶችን፣+ የጦር ሠረገሎችን፣+ ፈረሰኞችንና ብዙ ወታደሮችን* ያቀፈ ሠራዊት ያለው የነገሥታት ንጉሥ ነው።+  በገጠር ያሉ ሰፈሮችሽን በሰይፍ ያወድማል፤ በአንቺም ላይ ለከበባ የሚያገለግል ግንብ ይገነባል፤ የአፈር ቁልልም ይደለድላል፤ በአንቺም ላይ ትልቅ ጋሻ ያነሳል።  ቅጥሮችሽን በግንብ መደርመሻ መሣሪያ* ይደበድባል፤ ማማዎችሽንም በመጥረቢያ* ያፈርሳል። 10  ፈረሶቹ እጅግ ብዙ ከመሆናቸው የተነሳ አቧራ ያለብሱሻል፤ ሰዎች ቅጥሮቿ ወደፈረሱባት ከተማ እንደሚገቡ ሁሉ እሱም በበሮችሽ በሚገባበት ጊዜ የፈረሰኞቹ፣ የመንኮራኩሮቹና* የሠረገሎቹ ድምፅ ቅጥሮችሽን ያናውጣል። 11  የፈረሶቹ ኮቴዎች ጎዳናዎችሽን ሁሉ ይረግጣሉ፤+ ሕዝብሽን በሰይፍ ይገድላል፤ ግዙፍ የሆኑት ዓምዶችሽ መሬት ላይ ይንኮታኮታሉ። 12  ሀብትሽን ይበዘብዛሉ፤ ሸቀጥሽን ይዘርፋሉ፤+ ቅጥሮችሽን ያፈርሳሉ፤ የሚያማምሩ ቤቶችሽንም ያወድማሉ፤ ከዚያም ድንጋዮችሽን፣ ሳንቃዎችሽንና አፈርሽን ወደ ባሕር ይጥላሉ።’ 13  “‘የዘፈንሽ ጩኸት ጸጥ እንዲል አደርጋለሁ፤ የበገናሽም ድምፅ ከእንግዲህ አይሰማም።+ 14  የሚያንጸባርቅ ገላጣ ዓለትም አደርግሻለሁ፤ የመረብ ማስጫ ቦታ ትሆኛለሽ።+ ዳግመኛ አትገነቢም፤ እኔ ይሖዋ ራሴ ተናግሬአለሁና’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ። 15  “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ጢሮስን እንዲህ ይላል፦ ‘ሞት አፋፍ ላይ ያሉት* ሲያቃስቱና በመካከልሽ ጭፍጨፋ ሲካሄድ፣ ከውድቀትሽ ድምፅ የተነሳ ደሴቶች አይናወጡም?+ 16  የባሕርም ገዢዎች* ሁሉ ከዙፋኖቻቸው ይወርዳሉ፤ ልብሳቸውንም * ያወልቃሉ፤ የተጠለፉ ሸማዎቻቸውንም አውልቀው ይጥላሉ፤ ደግሞም በጣም ይንቀጠቀጣሉ።* መሬት ላይ ተቀምጠው ያለማቋረጥ ይንቀጠቀጣሉ፤ በመገረምም አተኩረው ይመለከቱሻል።+ 17  በአንቺም ላይ ሙሾ ያወርዳሉ፤*+ እንዲህም ይሉሻል፦ “ባሕር አቋርጠው የመጡ ሰዎች የሰፈሩብሽ፣ የተወደስሽ ከተማ ሆይ፣ እንዴት ጠፋሽ!+አንቺም ሆንሽ ነዋሪዎችሽ በምድር ነዋሪዎች ሁሉ ላይሽብር የምትነዙ የባሕር ላይ ኃያላን ነበራችሁ።+ 18  በምትወድቂበት ቀን ደሴቶች ይንቀጠቀጣሉ፤ጥፋት በሚደርስብሽ ጊዜ በባሕር ላይ ያሉ ደሴቶች ይሸበራሉ።”’+ 19  “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦ ‘ሰው እንደማይኖርባቸው ከተሞች ባድማ ሳደርግሽ፣ የሚያጥለቀልቅ ውኃ ሳመጣብሽና ኃይለኛ ውኃ ሲሸፍንሽ፣+ 20  አንቺንም ሆነ ከአንቺ ጋር ወደ ጉድጓድ* የሚወርዱትን፣ የጥንት ዘመን ሰዎች ወዳሉበት አወርዳችኋለሁ፤ ወደ ጉድጓድ ከሚወርዱት ጋር፣ ጥንት እንደወደሙት ቦታዎች እጅግ ዝቅተኛ በሆነ ምድር እንድትኖሪ አደርጋለሁ፤+ ይህም የሚሆነው ሰው እንዳይኖርብሽ ነው። ከዚያ በኋላ የሕያዋንን ምድር ከፍ ከፍ አደርጋለሁ።* 21  “‘በአንቺ ላይ ድንገተኛ ሽብር አመጣለሁ፤ ከእንግዲህም አትኖሪም።+ ይፈልጉሻል ግን ፈጽሞ አትገኚም’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ሴቶች ልጆቿም።”
ቃል በቃል “ናቡከደረጾርን።” ናቡከደነጾር የሚለው ስም የሚጻፍበት ሌላው መንገድ ነው።
ቃል በቃል “ሰዎችን።”
ወይም “በማጥቂያ መሣሪያ።”
ወይም “በሰይፍ።”
የሠረገላ ተሽከርካሪ እግር።
ቃል በቃል “የታረዱት።”
ወይም “አለቆች።”
ወይም “እጅጌ የሌለው ቀሚሳቸውንም።”
ቃል በቃል “መንቀጥቀጥን እንደ ልብስ ይለብሳሉ።”
ወይም “የሐዘን እንጉርጉሮ ያሰማሉ።”
ወይም “መቃብር።”
ወይም “አስጌጣለሁ።”