ሕዝቅኤል 3:1-27

  • ሕዝቅኤል አምላክ የሰጠውን ጥቅልል እንዲበላ ታዘዘ (1-15)

  • ሕዝቅኤል ጠባቂ ሆኖ እንዲያገለግል ተሾመ (16-27)

    • ቸልተኛ መሆን የደም ዕዳ ያስከትላል (18-21)

3  ከዚያም “የሰው ልጅ ሆይ፣ በፊትህ ያለውን ብላ።* ይህን ጥቅልል ብላ፤ ሄደህም ለእስራኤል ቤት ተናገር” አለኝ።+  ስለዚህ አፌን ከፈትኩ፤ እሱም ጥቅልሉን እንድበላው ሰጠኝ።  ከዚያም “የሰው ልጅ ሆይ፣ ይህን የሰጠሁህን ጥቅልል ብላ፤ ሆድህንም ሙላ” አለኝ። እኔም ጥቅልሉን መብላት ጀመርኩ፤ በአፌም ውስጥ እንደ ማር ጣፈጠኝ።+  እሱም እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ፣ ወደ እስራኤል ቤት ሂድ፤ ቃሌንም ንገራቸው።  የተላክኸው ወደ እስራኤል ቤት እንጂ ለመረዳት የሚያዳግት ቋንቋ ወይም የማይታወቅ ልሳን ወደሚናገር ሕዝብ አይደለምና።  ለመረዳት የሚያዳግት ቋንቋ ወይም የማይታወቅ ልሳን ወደሚናገሩና ቃላቸው ሊገባህ ወደማይችል ብዙ ሕዝቦች አልተላክህም። ወደ እነሱ ብልክህማ ኖሮ ይሰሙህ ነበር።+  የእስራኤል ቤት ግን ሊሰሙህ አይፈልጉም፤ እኔን መስማት አይፈልጉምና።+ የእስራኤል ቤት ወገኖች ሁሉ ግትርና ልበ ደንዳና ናቸው።+  እነሆ፣ ፊትህን ልክ እንደ እነሱ ፊት ጠንካራ አድርጌዋለሁ፤ ግንባርህንም ልክ እንደ እነሱ ግንባር አጠንክሬዋለሁ።+  ግንባርህን እንደ አልማዝ፣ ከባልጩትም ይበልጥ ጠንካራ አድርጌዋለሁ።+ አትፍራቸው፤ ከፊታቸውም የተነሳ አትሸበር፤+ እነሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና።” 10  እሱም እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ፣ የምነግርህን ቃል ሁሉ በልብህ ያዝ፤ ደግሞም አዳምጥ። 11  በምርኮ ወደተወሰዱት ወገኖችህ*+ ሄደህ ንገራቸው። ቢሰሙም ባይሰሙም ‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል’ በላቸው።”+ 12  ከዚያም መንፈስ ወደ ላይ አነሳኝ፤+ ከበስተ ኋላዬም ታላቅ የጉምጉምታ ድምፅ “የይሖዋ ክብር ከስፍራው ይወደስ” ሲል ሰማሁ። 13  በዚያም የሕያዋን ፍጥረታቱ ክንፎች እርስ በርስ ሲነካኩ የሚያሰሙት ድምፅ፣+ በአጠገባቸው ያሉት መንኮራኩሮች*+ የሚያሰሙት ድምፅና የታላቅ ጉምጉምታ ድምፅ ነበር። 14  መንፈስም ወደ ላይ አንስቶ ወሰደኝ፤ እኔም ተማርሬና መንፈሴ ተቆጥቶ ሄድኩ፤ የይሖዋም ብርቱ እጅ በእኔ ላይ አርፋ ነበር። 15  ስለሆነም በቴልአቢብ፣ በኬባር ወንዝ+ አቅራቢያ ይኖሩ ወደነበሩት በግዞት የተወሰዱ ሰዎች ሄድኩ፤ እነሱም በሚኖሩበት ስፍራ ተቀመጥኩ፤ በድንጋጤ ፈዝዤም+ በመካከላቸው ሰባት ቀን ቆየሁ። 16  ሰባቱ ቀናት ካለፉ በኋላ የይሖዋ ቃል ወደ እኔ መጣ፦ 17  “የሰው ልጅ ሆይ፣ ለእስራኤል ቤት ጠባቂ አድርጌ ሾሜሃለሁ፤+ ከአፌ የሚወጣውንም ቃል ስትሰማ ማስጠንቀቂያዬን ንገራቸው።+ 18  ክፉውን ሰው ‘በእርግጥ ትሞታለህ’ ባልኩት ጊዜ ባታስጠነቅቀው፣ ደግሞም ክፉው ሰው በሕይወት ይኖር ዘንድ ከክፉ መንገዱ እንዲመለስ ማስጠንቀቂያ ባትሰጠው፣+ እሱ ክፉ በመሆኑ በሠራው በደል ይሞታል፤+ ደሙን ግን ከአንተ እጅ እሻዋለሁ።*+ 19  ሆኖም ክፉውን ሰው አስጠንቅቀኸው ከክፋቱና ከክፉ መንገዱ ባይመለስ፣ እሱ በሠራው በደል ይሞታል፤ አንተ ግን የገዛ ሕይወትህን* በእርግጥ ታድናለህ።+ 20  ይሁንና ጻድቅ ሰው ጽድቅ ማድረጉን ቢተውና መጥፎ ነገር ቢፈጽም፣* እኔ በፊቱ መሰናክል አስቀምጣለሁ፤ እሱም ይሞታል።+ ሳታስጠነቅቀው ከቀረህ በሠራው ኃጢአት የተነሳ ይሞታል፤ ያከናወነውም የጽድቅ ሥራ አይታወስም፤ ደሙን ግን ከአንተ እጅ እሻዋለሁ።*+ 21  ሆኖም ጻድቁን ሰው ኃጢአት እንዳይሠራ ብታስጠነቅቀውና ኃጢአት ባይሠራ፣ ማስጠንቀቂያውን በመስማቱ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል፤+ አንተም የገዛ ሕይወትህን* ታድናለህ።” 22  በዚያም የይሖዋ እጅ በእኔ ላይ ሆነች፤ እሱም “ተነስተህ ወደ ሸለቋማው ሜዳ ሂድ፤ በዚያም አናግርሃለሁ” አለኝ። 23  ስለዚህ ተነስቼ ወደ ሸለቋማው ሜዳ ሄድኩ፤ እነሆም በኬባር ወንዝ+ አጠገብ ያየሁትን ክብር የሚመስል የይሖዋ ክብር በዚያ ነበር፤+ እኔም በግንባሬ ተደፋሁ። 24  ከዚያም መንፈስ ወደ ውስጤ ገብቶ በእግሬ አቆመኝ፤+ አምላክም አናገረኝ፤ እንዲህም አለኝ፦ “ወደ ቤትህ ሄደህ በርህን ዘግተህ ተቀመጥ። 25  የሰው ልጅ ሆይ፣ አንተን በገመድ ይጠፍሩሃል፤ በመካከላቸውም እንዳትመላለስ ያስሩሃል። 26  እኔም ምላስህን ከላንቃህ ጋር አጣብቃለሁ፤ ዱዳም ትሆናለህ፤ ልትወቅሳቸውም አትችልም፤ ምክንያቱም እነሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸው። 27  በማናግርህ ጊዜ ግን አፍህን እከፍታለሁ፤ አንተም ‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል’ በላቸው።+ የሚሰማ ይስማ፤+ የማይሰማም አይስማ፤ ምክንያቱም እነሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸው።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ያገኘኸውን ብላ።”
ቃል በቃል “የሕዝብህ ወንዶች ልጆች።”
የሠረገላ ተሽከርካሪ እግር።
ወይም “ይሁንና ስለ ደሙ አንተን ተጠያቂ አደርግሃለሁ።”
ወይም “ነፍስህን።”
ወይም “ኢፍትሐዊ ድርጊት ቢፈጽም።”
ወይም “ይሁንና ስለ ደሙ አንተን ተጠያቂ አደርግሃለሁ።”
ወይም “ነፍስህን።”