ሕዝቅኤል 35:1-15

  • በሴይር ተራሮች ላይ የተነገረ ትንቢት (1-15)

35  የይሖዋ ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦  “የሰው ልጅ ሆይ፣ ፊትህን ተራራማ ወደሆነው የሴይር+ ምድር አዙረህ በእሱ ላይ ትንቢት ተናገር።+  እንዲህም በለው፦ ‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “የሴይር ተራራማ ምድር ሆይ፣ እነሆ በአንተ ላይ ተነስቻለሁ፤ እጄን በአንተ ላይ እዘረጋለሁ፤ ባድማና ወና አደርግሃለሁ።+  ከተሞችህን አፈራርሳለሁ፤ አንተም ባድማና ወና ትሆናለህ፤+ እኔም ይሖዋ እንደሆንኩ ታውቃለህ።  የእስራኤል ልጆች ጥፋት በደረሰባቸውና የመጨረሻውን ቅጣት በተቀበሉበት ጊዜ የማያባራ የጠላትነት ስሜት በማሳየት+ ለሰይፍ አሳልፈህ ሰጥተሃቸዋልና።”’+  “‘ስለዚህ በሕያውነቴ እምላለሁ’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ፣ ‘ለእርድ አዘጋጅሃለሁ፤ ደምህም ይፈስሳል።+ ደም ጠልተህ ስለነበር ደምህ ይፈስሳል።+  የሴይርን ተራራማ ምድር ባድማና ወና አደርጋለሁ፤+ በዚያ የሚያልፈውንም ሆነ የሚመለሰውን ማንኛውንም ሰው አጠፋለሁ።  ተራሮቹን በታረዱ ሰዎች እሞላለሁ፤ በሰይፍ የታረዱት በኮረብቶችህ፣ በሸለቆዎችህና በጅረቶችህ ላይ ይወድቃሉ።  ለዘላለም ባድማ አደርግሃለሁ፤ ከተሞችህም ሰው አልባ ይሆናሉ፤+ እናንተም እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ።’ 10  “ይሖዋ ራሱ በዚያ ቢኖርም እንኳ፣ አንተ ‘እነዚህ ሁለት ብሔራትና ሁለት አገሮች የእኔ ይሆናሉ፤ እኛም ሁለቱን አገሮች እንወርሳለን’+ ስላልክ፣ 11  ‘በሕያውነቴ እምላለሁ’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ፣ ‘ለእነሱ ካደረብህ የጥላቻ ስሜት የተነሳ በእነሱ ላይ በገለጥከው በዚያው ዓይነት ቁጣና ቅናት እኔም እርምጃ እወስድብሃለሁ፤+ በአንተም ላይ በምፈርድበት ጊዜ በእነሱ መካከል ማንነቴ እንዲታወቅ አደርጋለሁ። 12  አንተ “ወና ሆነዋል፤ ለእኛም እንደ መብል ተሰጥተዋል” ባልክ ጊዜ በእስራኤል ተራሮች ላይ በንቀት የተናገርከውን ነገር ሁሉ እኔ ይሖዋ ራሴ እንደሰማሁ በዚያን ጊዜ ታውቃለህ።” 13  እናንተ በእኔ ላይ በእብሪት ተናግራችኋል፤ ደግሞም በእኔ ላይ ብዙ ነገር ተናግራችኋል።+ የተናገራችሁትን ሁሉ ሰምቻለሁ።’ 14  “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘አንተን ባድማና ወና በማደርግበት ጊዜ መላዋ ምድር ሐሴት ታደርጋለች። 15  የእስራኤል ቤት ርስት ባድማ በሆነበት ጊዜ ስለተደሰትክ እኔም እንዲሁ አደርግብሃለሁ።+ የሴይር ተራራማ ምድር ሆይ፣ አንተም ሆንክ መላው የኤዶም ምድር ሙሉ በሙሉ ባድማ ትሆናላችሁ፤+ እነሱም እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ።’”

የግርጌ ማስታወሻዎች