ሕዝቅኤል 42:1-20

  • የመመገቢያ ክፍሎቹ ሕንፃዎች (1-14)

  • የቤተ መቅደሱ አራት ጎኖች ተለኩ (15-20)

42  ከዚያም በስተ ሰሜን ወዳለው ወደ ውጨኛው ግቢ ወሰደኝ።+ ደግሞም በአቅራቢያው ከሚገኘው ሕንፃ+ በስተ ሰሜን፣ ክፍት ከሆነው ስፍራ አጠገብ ወዳሉት የመመገቢያ ክፍሎች ያሏቸው ሕንፃዎች+ አመጣኝ።  ሕንፃዎቹ በሰሜኑ መግቢያ በኩል ርዝመታቸው 100 ክንድ* ነበር፤ ወርዳቸው ደግሞ 50 ክንድ ነበር።  ሕንፃዎቹ የሚገኙት ወርዱ 20 ክንድ በሆነው በውስጠኛው ግቢና+ በውጨኛው ግቢ መመላለሻ መንገድ መካከል ነበር። ሕንፃዎቹ ባለ ሁለት ፎቅ ሲሆኑ ትይዩ ሆነው የተሠሩ ሰገነቶች ነበሯቸው።  በመመገቢያ ክፍሎቹ ፊት* ወርዱ 10 ክንድ፣ ርዝመቱ ደግሞ 100 ክንድ የሆነ መተላለፊያ* በውስጥ በኩል ነበር፤+ የክፍሎቹም መግቢያዎች የሚገኙት በስተ ሰሜን በኩል ነበር።  ከላይ ያሉት የመመገቢያ ክፍሎች ከታች ካሉትና መካከል ላይ ካሉት የሕንፃው ክፍሎች ይልቅ ጠበብ ያሉ ነበሩ፤ ምክንያቱም ሰገነቶቹ ሰፋ ያለ ቦታ ይዘውባቸው ነበር።  የመመገቢያ ክፍሎቹ ባለ ሁለት ፎቅ ነበሩ፤ ይሁንና በግቢው ውስጥ እንዳሉት ዓይነት ዓምዶች አልነበሯቸውም። ከታች ካሉትና መካከል ላይ ካሉት ይበልጥ ከላይኛው ፎቅ ክፍሎች ሰፊ ቦታ የተወሰደው ለዚህ ነው።  ከሌሎቹ የመመገቢያ ክፍሎች ጋር ትይዩ ከሆኑትና በውጨኛው ግቢ በኩል ካሉት የመመገቢያ ክፍሎች አጠገብ የሚገኘው የውጨኛው የድንጋይ ቅጥር ርዝመት 50 ክንድ ነበር።  በውጨኛው ግቢ በኩል ያሉት የመመገቢያ ክፍሎች ርዝመት 50 ክንድ ሲሆን ከመቅደሱ ትይዩ ያሉት የመመገቢያ ክፍሎች ርዝመት ግን 100 ክንድ ነበር።  የመመገቢያ ክፍሎቹ በስተ ምሥራቅ በኩል፣ ከውጨኛው ግቢ ወደ ክፍሎቹ የሚወስድ መግቢያ ነበራቸው። 10  በደቡብም በኩል ክፍት በሆነው ስፍራና በሕንፃው አቅራቢያ፣ በስተ ምሥራቅ ባለው የግቢው የድንጋይ ቅጥር ውስጥ* የመመገቢያ ክፍሎች ነበሩ።+ 11  በስተ ሰሜን እንዳሉት የመመገቢያ ክፍሎች ሁሉ በእነዚህ የመመገቢያ ክፍሎች ፊትም መተላለፊያ ነበር።+ ክፍሎቹ ተመሳሳይ ርዝመትና ወርድ ነበራቸው፤ መውጫዎቻቸውም ሆኑ ንድፎቻቸው ተመሳሳይ ነበሩ። መግቢያዎቻቸው 12  በደቡብ በኩል ከሚገኙት የመመገቢያ ክፍሎች መግቢያዎች ጋር ተመሳሳይ ነበሩ። በስተ ምሥራቅ በኩል በአቅራቢያው ካለው የድንጋይ ቅጥር ፊት፣ በመተላለፊያው መንገድ መነሻ ላይ ሰው ሊገባበት የሚችል መግቢያ ነበር።+ 13  ከዚያም እንዲህ አለኝ፦ “ክፍት ከሆነው ስፍራ አጠገብ የሚገኙት በስተ ሰሜን ያሉት የመመገቢያ ክፍሎችና በስተ ደቡብ ያሉት የመመገቢያ ክፍሎች፣+ ወደ ይሖዋ የሚቀርቡት ካህናት እጅግ ቅዱስ የሆኑትን መባዎች የሚበሉባቸው የተቀደሱ መመገቢያ ክፍሎች ናቸው።+ በዚያም እጅግ ቅዱስ የሆኑትን መባዎች፣ የእህል መባ፣ የኃጢአት መባና የበደል መባ ያስቀምጣሉ፤ ምክንያቱም ቦታው ቅዱስ ነው።+ 14  ካህናቱ በሚገቡበት ጊዜ፣ ሲያገለግሉ የሚለብሱትን ልብስ ሳያወልቁ ከቅዱሱ ስፍራ ወደ ውጨኛው አደባባይ መውጣት አይችሉም፤+ ልብሶቹ ቅዱስ ናቸውና። ለሕዝቡ ወደተፈቀዱት ቦታዎች ከመሄዳቸው በፊት ልብሳቸውን ይቀይሩ ነበር።” 15  የቤተ መቅደሱን የውስጠኛውን ስፍራ ለክቶ* ሲጨርስ ከምሥራቅ ትይዩ ወደሆነው በር+ በሚወስደው መተላለፊያ በኩል ይዞኝ ወጣ፤ ከዚያም ስፍራውን በጠቅላላ ለካ። 16  በስተ ምሥራቅ በኩል ያለውን በመለኪያ ዘንግ* ለካ። በመለኪያ ዘንጉ ከአንዱ ጎን እስከ ሌላው ጎን ርዝመቱ 500 ዘንግ ሆነ። 17  በስተ ሰሜን በኩል ያለውን ለካ፤ በመለኪያ ዘንጉም ርዝመቱ 500 ዘንግ ሆነ። 18  በስተ ደቡብ በኩል ያለውን ለካ፤ በመለኪያ ዘንጉም ርዝመቱ 500 ዘንግ ሆነ። 19  ከዚያም ወደ ምዕራብ ዞረ። በመለኪያ ዘንጉ ሲለካ ርዝመቱ 500 ዘንግ ሆነ። 20  ስፍራውን በአራቱም ጎን ለካ። ቅዱስ የሆነውንና ቅዱስ ያልሆነውን ስፍራ ለመለየት የሚያገለግል+ ርዝመቱ 500 ዘንግ፣ ወርዱም 500 ዘንግ+ የሆነ ቅጥር በዙሪያው ነበር።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ይህ ረጅም ክንድ የሚባለውን መለኪያ ያመለክታል። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “በክፍሎቹ ፊት።”
በግሪክኛው ሰብዓ ሊቃናት መሠረት “100 ክንድ የሆነ መተላለፊያ” ነው። የዕብራይስጡ ጽሑፍ “አንድ ክንድ የሆነ መንገድ” ይላል። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ቃል በቃል “በድንጋይ ቅጥሩ ወርድ ውስጥ።”
ቃል በቃል “የውስጠኛውን ቤት ለክቶ።”
ቃል በቃል “ሸምበቆ።” ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።