ሕዝቅኤል 5:1-17

  • ኢየሩሳሌም ጥፋት እንደሚደርስባት በምሳሌያዊ ሁኔታ ተገለጸ (1-17)

    • ነቢዩ ከተላጨ በኋላ ፀጉሩን ሦስት ቦታ ይከፍለዋል (1-4)

    • ኢየሩሳሌም ከሌሎች ብሔራት የከፋ ድርጊት ፈጽማለች (7-9)

    • በሦስት መንገድ ቅጣት ይደርስባታል (12)

5  “አንተም የሰው ልጅ ሆይ፣ እንደ ፀጉር አስተካካይ ምላጭ የምትጠቀምበት ስለታም ሰይፍ ውሰድ። የራስህን ፀጉርና ጢምህን ተላጭ፤ ከዚያም ሚዛን ወስደህ ፀጉሩን መዝነውና ከፋፍለው።  የከበባው ጊዜ ሲፈጸም+ አንድ ሦስተኛውን በከተማዋ ውስጥ በእሳት ታቃጥለዋለህ። ከዚያም ሌላ አንድ ሦስተኛ ወስደህ በከተማዋ ዙሪያ በሰይፍ ትመታዋለህ፤+ የመጨረሻውንም አንድ ሦስተኛ ለነፋስ ትበትነዋለህ፤ እኔም እነሱን ለማሳደድ ሰይፍ እመዛለሁ።+  “ደግሞም ከፀጉሮቹ ላይ ጥቂት ወስደህ በልብስህ እጥፋት* ቋጥራቸው።  የተወሰነውን ደግሞ ወስደህ እሳት ውስጥ ጨምረው፤ ሙሉ በሙሉም በእሳት አቃጥለው። ይህ እሳት ወጥቶ በእስራኤል ቤት ሁሉ ይሰራጫል።+  “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ይህች ኢየሩሳሌም ናት። አገሮችን በዙሪያዋ አድርጌ፣ በብሔራት መካከል አስቀምጫታለሁ።  እሷ ግን ከብሔራትና በዙሪያዋ ካሉ አገሮች ሁሉ የባሰ ክፋት በመሥራት በድንጋጌዎቼና ባወጣኋቸው ደንቦች ላይ ዓምፃለች።+ ሕዝቡ ድንጋጌዎቼን ወደ ጎን ገሸሽ አድርጓልና፤ ደንቦቼንም አክብሮ አልተመላለሰም።’  “ስለዚህ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በዙሪያችሁ ካሉት ብሔራት ይበልጥ አስቸጋሪ በመሆናችሁ፣ ደንቦቼን አክብራችሁ ባለመመላለሳችሁ ወይም ድንጋጌዎቼን ባለመጠበቃችሁ፣ ይልቁንም በዙሪያችሁ ያሉትን ብሔራት ድንጋጌዎች በመከተላችሁ፣+  ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “አንቺ ከተማ ሆይ፣ በአንቺ ላይ ተነስቻለሁ፤+ ደግሞም እኔ ራሴ በብሔራት ፊት በመካከልሽ ፍርዴን አስፈጽማለሁ።+  በአስጸያፊ ድርጊቶችሽ ሁሉ የተነሳ ከዚህ በፊት ፈጽሞ ያላደረግኩትን፣ ከዚህም በኋላ የማልደግመውን በአንቺ ላይ አደርጋለሁ።+ 10  “‘“ስለዚህ በመካከልሽ አባቶች ልጆቻቸውን ይበላሉ፤+ ልጆችም አባቶቻቸውን ይበላሉ፤ በመካከልሽ ፍርዴን አስፈጽማለሁ፤ ከአንቺ የቀሩትንም በሙሉ በየአቅጣጫው* እበትናቸዋለሁ።”’+ 11  “‘ስለዚህ በሕያውነቴ እምላለሁ’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ፣ ‘በአስጸያፊ ጣዖቶችሽ ሁሉና ጸያፍ በሆኑ ድርጊቶችሽ ሁሉ መቅደሴን ስላረከስሽ፣+ እኔ ራሴ እተውሻለሁ፤* ዓይኔ አያዝንም ደግሞም አልራራም።+ 12  ከአንቺም አንድ ሦስተኛው በቸነፈር* ይሞታል ወይም በመካከልሽ በረሃብ ያልቃል። ሌላ አንድ ሦስተኛ ደግሞ በዙሪያሽ በሰይፍ ይወድቃል።+ የመጨረሻውን አንድ ሦስተኛ ደግሞ በየአቅጣጫው* እበትነዋለሁ፤ እነሱንም ለማሳደድ ሰይፍ እመዛለሁ።+ 13  ከዚያም ቁጣዬ ይፈጸማል፤ በእነሱም ላይ የነደደው ቁጣዬ ይበርዳል፤ እኔም እረካለሁ።+ በእነሱም ላይ ቁጣዬን ፈጽሜ ባወረድኩ ጊዜ፣ እኔ ብቻ መመለክ የምፈልገው፣+ እኔ ይሖዋ ይህን እንደተናገርኩ ያውቃሉ። 14  “‘በዙሪያሽ ባሉ ብሔራት መካከል እንዲሁም በአጠገብሽ በሚያልፉ ሁሉ ፊት ባድማና መሳለቂያ አደርግሻለሁ።+ 15  በቁጣ፣ በንዴትና በኃይለኛ ቅጣት የፍርድ እርምጃ ስወስድብሽ በዙሪያሽ ባሉ ብሔራት ዘንድ መሳለቂያና መዘባበቻ+ ደግሞም የማስጠንቀቂያ ምሳሌና ማስፈራሪያ ትሆኛለሽ። እኔ ይሖዋ ይህን ተናግሬአለሁ። 16  “‘እነሱን ለማጥፋት ገዳይ የሆኑ የረሃብ ፍላጻዎችን እሰድባቸዋለሁ። የምሰዳቸው የረሃብ ፍላጻዎች ያጠፏችኋል።+ የምግብ አቅርቦታችሁ እንዲቋረጥ በማድረግ* ረሃቡን አባብሳለሁ።+ 17  በእናንተ ላይ ረሃብንና አደገኛ የዱር አራዊትን እሰዳለሁ፤+ እነሱም የወላድ መሃን ያደርጓችኋል። ቸነፈርና ደም መፋሰስ ያጥለቀልቋችኋል፤ ሰይፍም አመጣባችኋለሁ።+ እኔ ይሖዋ ይህን ተናግሬአለሁ።’”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “በቀሚስህ።”
ቃል በቃል “ወደ ነፋስ ሁሉ።”
ወይም “አሳንስሻለሁ።”
ወይም “በበሽታ።”
ቃል በቃል “ወደ ነፋስ ሁሉ።”
ቃል በቃል “የዳቦ በትሮቻችሁን በመስበር።” ዳቦ ለማስቀመጥ የሚያገለግሉ በትሮችን የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።