መሳፍንት 10:1-18

  • መሳፍንቱ ቶላና ያኢር (1-5)

  • እስራኤላውያን ዓመፁ፤ በኋላም ንስሐ ገቡ (6-16)

  • አሞናውያን እስራኤላውያንን ለመውጋት ተሰበሰቡ (17, 18)

10  ከአቢሜሌክ በኋላ የዶዶ ልጅ፣ የፑሃ ልጅ የይሳኮር ሰው የሆነው ቶላ እስራኤልን ለማዳን ተነሳ።+ እሱም በኤፍሬም ተራራማ አካባቢዎች በምትገኘው በሻሚር ይኖር ነበር።  በእስራኤልም ውስጥ ለ23 ዓመት ፈራጅ ሆኖ አገለገለ። ከዚያም ሞተ፤ በሻሚርም ተቀበረ።  ከእሱም በኋላ ጊልያዳዊው ያኢር ተነሳ፤ በእስራኤልም ውስጥ ለ22 ዓመት ፈራጅ ሆኖ አገለገለ።  ያኢር በ30 አህዮች የሚጋልቡ 30 ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነሱም እስከ ዛሬ ድረስ ሃዎትያኢር+ ተብለው የሚጠሩ 30 ከተሞች ነበሯቸው፤ ከተሞቹም የሚገኙት በጊልያድ ምድር ነው።  ከዚያም ያኢር ሞተ፤ በቃሞንም ተቀበረ።  እስራኤላውያንም በይሖዋ ፊት እንደገና መጥፎ ነገር አደረጉ፤+ ባአልን፣+ የአስታሮትን ምስሎች፣ የአራምን* አማልክት፣ የሲዶናን አማልክት፣ የሞዓብን አማልክት፣+ የአሞናውያንን አማልክትና+ የፍልስጤማውያንን አማልክት+ ማገልገል ጀመሩ። ይሖዋን ተዉት፤ እሱንም አላገለገሉም።  የይሖዋም ቁጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፤ እነሱንም ለፍልስጤማውያንና ለአሞናውያን ሸጣቸው።+  ስለሆነም በዚያ ዓመት እስራኤላውያንን አደቀቋቸው፤ ክፉኛም ጨቆኗቸው፤ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ በጊልያድ በሚገኘው በአሞራውያን ምድር የነበሩትን እስራኤላውያን በሙሉ ለ18 ዓመት ጨቆኗቸው።  በተጨማሪም አሞናውያን ይሁዳን፣ ቢንያምንና የኤፍሬምን ቤት ለመውጋት ዮርዳኖስን ይሻገሩ ነበር፤ እስራኤላውያንም እጅግ ተጨንቀው ነበር። 10  ከዚያም እስራኤላውያን “አንተን አምላካችንን ትተን ባአልን በማገልገላችን+ በአንተ ላይ ኃጢአት ሠርተናል” በማለት ይሖዋ እንዲረዳቸው ጮኹ።+ 11  ሆኖም ይሖዋ እስራኤላውያንን እንዲህ አላቸው፦ “ግብፃውያን፣+ አሞራውያን፣+ አሞናውያን፣ ፍልስጤማውያን፣+ 12  ሲዶናውያን፣ አማሌቃውያንና ምድያማውያን በጨቆኗችሁ ጊዜ አላዳንኳችሁም? ወደ እኔ ስትጮኹ ከእጃቸው ታደግኳችሁ። 13  እናንተ ግን እኔን ትታችሁ ሌሎች አማልክትን አገለገላችሁ።+ ዳግመኛ የማላድናችሁም በዚህ የተነሳ ነው።+ 14  ወደመረጣችኋቸው አማልክት ሂዱና እንዲረዷችሁ ጠይቋቸው።+ በጭንቀታችሁ ጊዜ እነሱ ያድኗችሁ።”+ 15  እስራኤላውያን ግን ይሖዋን “ኃጢአት ሠርተናል። መልካም መስሎ የታየህን ማንኛውንም ነገር አድርግብን። እባክህ፣ የዛሬን ብቻ አድነን” አሉት። 16  እነሱም ከመካከላቸው ባዕዳን አማልክትን አስወግደው ይሖዋን አገለገሉ፤+ በመሆኑም በእስራኤል ላይ እየደረሰ የነበረውን መከራ ሊታገሥ አልቻለም።* + 17  ከጊዜ በኋላም አሞናውያን+ ተሰባስበው በጊልያድ ሰፈሩ። በመሆኑም እስራኤላውያን ተሰባስበው በምጽጳ ሰፈሩ። 18  የጊልያድ ሕዝብና መኳንንት እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፦ “ከአሞናውያን ጋር የሚደረገውን ውጊያ ግንባር ቀደም ሆኖ የሚመራው ማን ነው?+ ይህ ሰው በጊልያድ ነዋሪዎች ሁሉ ላይ አለቃ ይሁን።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “የሶርያን።”
ወይም “ነፍሱ ልትታገሥ አልቻለችም።”