መሳፍንት 15:1-20

  • ሳምሶን ፍልስጤማውያንን ተበቀለ (1-20)

15  ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በስንዴ መከር ወቅት ሳምሶን አንድ የፍየል ጠቦት ይዞ ሚስቱን ሊጠይቅ ሄደ። እሱም “ሚስቴ ወዳለችበት መኝታ ቤት* መግባት እፈልጋለሁ” አለ። አባቷ ግን እንዲገባ አልፈቀደለትም።  ከዚያም አባትየው እንዲህ አለው፦ “እኔ እኮ ‘ፈጽሞ ጠልተሃታል’ ብዬ አስቤ ነበር።+ ስለሆነም ለሚዜህ ዳርኳት።+ ታናሽ እህቷ ከእሷ ይልቅ ቆንጆ አይደለችም? እባክህ በዚያችኛዋ ፋንታ ይህችኛዋን አግባት።”  ሳምሶን ግን “ከእንግዲህ ፍልስጤማውያን ለማደርስባቸው ጉዳት ተጠያቂ ሊያደርጉኝ አይችሉም” አላቸው።  ሳምሶንም ሄዶ 300 ቀበሮዎችን ያዘ። ከዚያም ችቦዎች አመጣ፤ ቀበሮዎቹንም ፊታቸውን አዙሮ ጭራና ጭራቸውን አንድ ላይ ካሰረ በኋላ በጭራቸው መሃል አንድ አንድ ችቦ አደረገ።  በመቀጠልም ችቦዎቹን በእሳት በመለኮስ ቀበሮዎቹን በፍልስጤማውያን እርሻ ላይ ባለው ያልታጨደ እህል ውስጥ ለቀቃቸው። ከነዶው አንስቶ እስካልታጨደው እህል ድረስ እንዲሁም የወይን እርሻዎችንና የወይራ ዛፎችን አቃጠለ።  ፍልስጤማውያኑም “ይህን ያደረገው ማን ነው?” ብለው ጠየቁ። እነሱም “የቲምናዊው አማች ሳምሶን ነው፤ ይህን ያደረገውም ሚስቱን ወስዶ ለሚዜው ስለሰጠበት ነው” ተብሎ ተነገራቸው።+ በዚህ ጊዜ ፍልስጤማውያን ሄደው እሷንና አባቷን በእሳት አቃጠሉ።+  ሳምሶንም “እንግዲህ እናንተ ይህን ካደረጋችሁ እኔ ደግሞ እናንተን ሳልበቀል አርፌ አልቀመጥም” አላቸው።+  ከዚያም አንድ በአንድ እየመታ* ረፈረፋቸው፤ ከዚህ በኋላ ወርዶ በኤጣም በሚገኝ አንድ የዓለት ዋሻ* ውስጥ ተቀመጠ።  በኋላም ፍልስጤማውያን ወጥተው በይሁዳ ሰፈሩ፤ የሊሃይንም+ አካባቢ ያስሱ ጀመር። 10  የይሁዳም ሰዎች “እኛን ልትወጉ የመጣችሁት ለምንድን ነው?” አሏቸው፤ እነሱም መልሰው “እኛ የመጣነው ሳምሶንን ለመያዝና* እሱ እንዳደረገብን ሁሉ እኛም እንድናደርግበት ነው” አሉ። 11  በመሆኑም 3,000 የይሁዳ ሰዎች በኤጣም ወደሚገኘው የዓለት ዋሻ* ወርደው ሳምሶንን “ፍልስጤማውያን ገዢዎቻችን መሆናቸውን አታውቅም?+ ታዲያ እንዲህ ያለ ነገር የፈጸምክብን ለምንድን ነው?” አሉት። እሱም “እነሱ እንዳደረጉብኝ እኔም አደረግኩባቸው” አላቸው። 12  እነሱ ግን “አሁን የመጣነው ይዘን* ለፍልስጤማውያን ልናስረክብህ ነው” አሉት። ከዚያም ሳምሶን “እናንተ ራሳችሁ ምንም ጥቃት እንደማታደርሱብኝ ማሉልኝ” አላቸው። 13  እነሱም “አስረን ብቻ ለእነሱ እናስረክብሃለን እንጂ አንገድልህም” አሉት። በመሆኑም በሁለት አዳዲስ ገመዶች አስረው ከዓለቱ ውስጥ አወጡት። 14  እሱም ሊሃይ ሲደርስ ፍልስጤማውያኑ እሱን በማግኘታቸው በድል አድራጊነት ጮኹ። በዚህ ጊዜ የይሖዋ መንፈስ ኃይል ሰጠው፤+ እጆቹ የታሰሩባቸውም ገመዶች እሳት እንደበላው የበፍታ ክር ሆኑ፤ ማሰሪያዎቹም ከእጆቹ ላይ ቀልጠው ወደቁ።+ 15  እሱም በቅርቡ የሞተ የአንድ አህያ መንጋጋ አገኘ፤ መንጋጋውንም አንስቶ በእሱ 1,000 ሰው ገደለ።+ 16  ከዚያም ሳምሶን እንዲህ አለ፦ “በአህያ መንጋጋ በክምር ላይ ክምር አነባባሪ፤ በአህያ መንጋጋ 1,000 ሰው ዘራሪ!”+ 17  እሱም ይህን ተናግሮ ሲጨርስ የአህያውን መንጋጋ ወረወረው፤ ያንንም ቦታ ራማትሊሃይ* + ብሎ ጠራው። 18  ከዚያም በጣም ተጠማ፤ ወደ ይሖዋም እንዲህ ሲል ጮኸ፦ “ይህ ታላቅ መዳን በአገልጋይህ እጅ እንዲፈጸም ያደረግከው አንተ ነበርክ። ታዲያ አሁን በውኃ ጥም ልሙት? በእነዚህ ባልተገረዙ ሰዎች እጅስ ልውደቅ?” 19  በመሆኑም አምላክ በሊሃይ የሚገኝ አንድ ዓለት ነደለ፤ ውኃም ከዓለቱ መውጣት ጀመረ።+ እሱም በጠጣ ጊዜ መንፈሱ* ተመለሰ፤ ብርታትም አገኘ። እስከ ዛሬ ድረስ በሊሃይ የሚገኘውን ያንን ቦታ ኤንሃቆሬ* ሲል የጠራው ለዚህ ነው። 20  እሱም በፍልስጤማውያን ዘመን ለ20 ዓመት በእስራኤል ውስጥ ፈራጅ ሆኖ አገለገለ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ወደ ውስጠኛው ክፍል።”
ቃል በቃል “እግር ጭናቸው ላይ እየመታ።”
ወይም “ስንጥቅ።”
ወይም “ለማሰርና።”
ወይም “ስንጥቅ።”
ወይም “አስረን።”
“የመንጋጋ ከፍ ያለ ቦታ” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “ጥንካሬው።”
“የጠሪው ምንጭ” የሚል ትርጉም አለው።