መሳፍንት 7:1-25

  • ጌድዮንና 300ዎቹ ሰዎች (1-8)

  • የጌድዮን ሠራዊት ምድያማውያንን ድል አደረገ (9-25)

    • “የይሖዋና የጌድዮን ሰይፍ!” (20)

    • በምድያማውያን የጦር ሰፈር የተከሰተው ግራ መጋባት (21, 22)

7  ከዚያም የሩባአል የተባለው ጌድዮንና+ ከእሱ ጋር የነበሩት ሰዎች በሙሉ በማለዳ ተነስተው በሃሮድ ምንጭ አጠገብ ሰፈሩ፤ የምድያማውያን ሰፈር ደግሞ ከእሱ በስተ ሰሜን በሞሬ ኮረብታ በሸለቋማው ሜዳ* ላይ ይገኝ ነበር።  ይሖዋም ጌድዮንን እንዲህ አለው፦ “ምድያማውያንን በእጃቸው አሳልፌ እንዳልሰጥ አብረውህ ያሉት ሰዎች በጣም ብዙ ናቸው።+ ይህን ባደርግ እስራኤላውያን ‘የገዛ እጄ አዳነኝ’+ ብለው ይታበዩብኛል።  በመሆኑም እባክህ ሕዝቡ በተሰበሰበበት ‘ከመካከላችሁ የፈራና የተሸበረ ካለ ወደ ቤት ይመለስ’ ብለህ ተናገር።”+ ስለዚህ ጌድዮን ፈተናቸው። በዚህ ጊዜ ከሕዝቡ መካከል 22,000 ሰዎች ወደ ቤታቸው ተመለሱና 10,000 ብቻ ቀሩ።  ይሖዋም እንደገና ጌድዮንን እንዲህ አለው፦ “አሁንም ሰዎቹ በጣም ብዙ ናቸው። በዚያ እነሱን እንድፈትንልህ ወደ ውኃው ይዘሃቸው ውረድ። እኔም ‘ይህ ከአንተ ጋር ይሄዳል’ የምልህ ከአንተ ጋር ይሄዳል፤ ‘ይህ ከአንተ ጋር አይሄድም’ የምልህ ግን ከአንተ ጋር አይሄድም።”  እሱም ሰዎቹን ወደ ውኃው ይዟቸው ወረደ። ከዚያም ይሖዋ ጌድዮንን “ልክ እንደ ውሻ ውኃውን በምላሱ እየጨለፈ የሚጠጣውን ሁሉ በጉልበታቸው ተንበርክከው ከሚጠጡት ለይ” አለው።  ውኃውን በእጃቸው እየጨለፉ የሚጠጡት ሰዎች ቁጥር 300 ነበር። የቀሩት ሰዎች ሁሉ ግን ውኃ ለመጠጣት በጉልበታቸው ተንበረከኩ።  ይሖዋም ጌድዮንን እንዲህ አለው፦ “ውኃውን በእጃቸው እየጨለፉ በጠጡት 300 ሰዎች አድናችኋለሁ፤ ምድያማውያንንም በእጃችሁ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ።+ የቀሩት ሰዎች ሁሉ ግን ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ አሰናብታቸው።”  በመሆኑም ከሕዝቡ ላይ ስንቃቸውንና ቀንደ መለከታቸውን ከተቀበሉ በኋላ ጌድዮን 300ዎቹን ብቻ አስቀርቶ ሌሎቹን እስራኤላውያን በሙሉ ወደ ቤታቸው አሰናበታቸው። የምድያማውያኑ ሰፈር የሚገኘው ከእሱ በታች በሸለቋማው ሜዳ ላይ ነበር።+  በዚያ ምሽት ይሖዋ ጌድዮንን እንዲህ አለው፦ “ተነስ፤ በእጅህ አሳልፌ ስለሰጠሁህ በሰፈሩ ላይ ጥቃት ሰንዝር።+ 10  በሰፈሩ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ከፈራህ ግን ከአገልጋይህ ከፑራ ጋር ወደ ሰፈሩ ውረድ። 11  የሚናገሩትንም ነገር አዳምጥ፤ ከዚያም በሰፈሩ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ድፍረት ታገኛለህ።”* ስለዚህ እሱና አገልጋዩ ፑራ ወርደው ሠራዊቱ ወደሰፈረበት ቦታ ተጠጉ። 12  ምድያማውያንና አማሌቃውያን እንዲሁም የምሥራቅ ሰዎች በሙሉ+ ሸለቋማውን ሜዳ ልክ እንደ አንበጣ መንጋ ወረውት ነበር፤ ግመሎቻቸውም በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ለቁጥር የሚያታክቱ ነበሩ።+ 13  ጌድዮንም እዚያ ደረሰ፤ በዚህ ጊዜ አንድ ሰው ለጓደኛው እንዲህ በማለት አንድ ሕልም እየነገረው ነበር፦ “ያለምኩት ሕልም ይህ ነው። አንድ የገብስ ዳቦ እየተንከባለለ ወደ ምድያም ሰፈር መጣ። ከዚያም ወደ አንድ ድንኳን በመምጣት በኃይል መትቶ ጣለው።+ ድንኳኑንም ገለበጠው፤ ድንኳኑም መሬት ላይ ተነጠፈ።” 14  ጓደኛውም እንዲህ አለው፦ “ይሄማ ከዮአስ ልጅ ከእስራኤላዊው ከጌድዮን ሰይፍ በስተቀር ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም።+ አምላክ ምድያማውያንንና ሰፈሩን በሙሉ በእጁ አሳልፎ ሰጥቶታል።”+ 15  ጌድዮንም ሕልሙንና ፍቺውን ሲሰማ ለአምላክ ሰገደ።+ ከዚያም ወደ እስራኤላውያን ሰፈር ተመልሶ “ተነሱ፤ ይሖዋ የምድያማውያንን ሰፈር በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቷችኋል” አላቸው። 16  በመቀጠልም 300ዎቹን ሰዎች በሦስት ቡድን ከፈላቸው፤ ለሁሉም ቀንደ መለከትና+ በውስጣቸው ችቦ ያለባቸው ትላልቅ ባዶ ማሰሮዎች ሰጣቸው። 17  ከዚያም እንዲህ አላቸው፦ “ልብ ብላችሁ ተመልከቱኝ፤ እኔ የማደርገውንም አድርጉ። ወደ ሰፈሩ ዳርቻ በምጠጋበት ጊዜ ልክ እኔ እንደማደርገው አድርጉ። 18  እኔና ከእኔ ጋር ያሉት ሁሉ ቀንደ መለከቶቻችንን ስንነፋ እናንተም በሰፈሩ ዙሪያ ሁሉ ቀንደ መለከቶቻችሁን ነፍታችሁ ‘ለይሖዋና ለጌድዮን!’ ብላችሁ ጩኹ።” 19  ከዚያም ጌድዮንና ከእሱ ጋር የነበሩት 100 ሰዎች በመካከለኛው ክፍለ ሌሊት* መጀመሪያ ላይ ዘብ ጠባቂዎቹ ገና እንደተቀያየሩ ወደ ሰፈሩ ዳርቻ ተጠጉ። እነሱም ቀንደ መለከቶቻቸውን ነፉ፤+ የያዟቸውንም ትላልቅ የውኃ ማሰሮዎች ሰባበሩ።+ 20  በዚህ ጊዜ ሦስቱም ቡድኖች ቀንደ መለከቶቻቸውን ነፉ፤ ትላልቆቹንም ማሰሮዎች ሰባበሩ። ችቦዎቹን በግራ እጃቸው ይዘው በቀኝ እጃቸው የያዟቸውን ቀንደ መለከቶች እየነፉ “የይሖዋና የጌድዮን ሰይፍ!” በማለት ጮኹ። 21  እያንዳንዱም ሰው በሰፈሩ ዙሪያ ቦታ ቦታውን ይዞ ቆሞ ነበር፤ ሠራዊቱም ሁሉ ሮጠ፤ እየጮኸም ሸሸ።+ 22  ሦስት መቶዎቹ ሰዎችም ቀንደ መለከቶቹን መንፋታቸውን ቀጠሉ፤ ይሖዋም በሰፈሩ ውስጥ ያለው እያንዳንዱ ሰው አንዱ በሌላው ላይ ሰይፉን እንዲመዝበት አደረገ፤+ ሠራዊቱም በጸሬራህ አቅጣጫ እስከ ቤትሺጣ እንዲሁም ከጣባት አጠገብ እስከምትገኘው እስከ አቤልምሆላ+ ዳርቻ ድረስ ሸሸ። 23  እስራኤላውያንም ከንፍታሌም፣ ከአሴርና ከመላው ምናሴ+ ተጠርተው አንድ ላይ በመሰባሰብ ምድያማውያንን አሳደዷቸው። 24  ጌድዮንም በኤፍሬም ተራራማ አካባቢዎች ለሚኖሩ ሁሉ “በምድያማውያን ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ውረዱ፤ እስከ ቤትባራ ድረስ ያሉትን ውኃዎችና ዮርዳኖስን ያዙ” ብለው እንዲነግሯቸው መልእክተኞችን ላከ። በመሆኑም የኤፍሬም ሰዎች በሙሉ ተጠሩ፤ እነሱም እስከ ቤትባራ ድረስ ያሉትን ውኃዎችና ዮርዳኖስን ያዙ። 25  በተጨማሪም ሁለቱን የምድያም መኳንንት ማለትም ኦሬብን+ እና ዜብን ያዙ፤ ኦሬብን በኦሬብ ዓለት ላይ ገደሉት፤ ዜብን ደግሞ በዜብ የወይን መጭመቂያ ላይ ገደሉት። ምድያማውያንንም ማሳደዳቸውን ተያያዙት፤+ የኦሬብን እና የዜብን ጭንቅላት በዮርዳኖስ አካባቢ ወደነበረው ወደ ጌድዮን አመጡ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “በረባዳማው ሜዳ።”
ቃል በቃል “እጅህ ይበረታል።”
ከምሽቱ 4 ሰዓት ገደማ ጀምሮ እስከ ሌሊቱ 8 ሰዓት ገደማ ድረስ።