መክብብ 3:1-22

  • “ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው” (1-8)

  • በሕይወት መደሰት የአምላክ ስጦታ ነው (9-15)

    • ዘላለማዊነትን በሰው ልብ ውስጥ አኑሯል (11)

  • አምላክ በፍትሕ ይፈርዳል (16, 17)

  • ሰዎችም ሆኑ እንስሳት፣ ሁሉም ይሞታሉ (18-22)

    • “ሁሉም ወደ አፈር ይመለሳሉ” (20)

3  ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው፤ከሰማይ በታች ለሚከናወን ነገር ሁሉ ጊዜ አለው፦  2  ለመወለድ ጊዜ አለው፤* ለመሞትም ጊዜ አለው፤ለመትከል ጊዜ አለው፤ የተተከለውን ለመንቀልም ጊዜ አለው፤  3  ለመግደል ጊዜ አለው፤ ለመፈወስም ጊዜ አለው፤ለማፍረስ ጊዜ አለው፤ ለመገንባትም ጊዜ አለው፤  4  ለማልቀስ ጊዜ አለው፤ ለመሳቅም ጊዜ አለው፤ለዋይታ ጊዜ አለው፤ ለጭፈራም* ጊዜ አለው፤  5  ድንጋይ ለመጣል ጊዜ አለው፤ ድንጋይ ለመሰብሰብም ጊዜ አለው፤ለማቀፍ ጊዜ አለው፤ ከማቀፍ ለመቆጠብም ጊዜ አለው፤  6  ለመፈለግ ጊዜ አለው፤ ጠፍቷል ብሎ ለመተውም ጊዜ አለው፤ለማስቀመጥ ጊዜ አለው፤ አውጥቶ ለመጣልም ጊዜ አለው፤  7  ለመቅደድ ጊዜ አለው፤+ ለመስፋትም ጊዜ አለው፤ዝም ለማለት ጊዜ አለው፤+ ለመናገርም ጊዜ አለው፤+  8  ለመውደድ ጊዜ አለው፤ ለመጥላትም ጊዜ አለው፤+ለጦርነት ጊዜ አለው፤ ለሰላምም ጊዜ አለው። 9  ሠራተኛ ከልፋቱ ሁሉ የሚያገኘው ጥቅም ምንድን ነው?+ 10  አምላክ የሰው ልጆች እንዲጠመዱበት የሰጣቸውን ሥራ ተመለከትኩ። 11  አምላክ ሁሉንም ነገር በወቅቱ ውብ* አድርጎ ሠርቶታል።+ ደግሞም ዘላለማዊነትን በልባቸው ውስጥ አኑሯል፤ ይሁንና የሰው ልጆች እውነተኛው አምላክ ከመጀመሪያው አንስቶ እስከ መጨረሻው ድረስ ያከናወነውን ሥራ በምንም ዓይነት መርምረው ሊደርሱበት አይችሉም። 12  ለሰው በሕይወት ዘመኑ ከመደሰትና መልካም ከማድረግ የተሻለ ነገር የለም ብዬ ደመደምኩ፤+ 13  ደግሞም ለሰው ከመብላትና ከመጠጣት እንዲሁም ተግቶ በሚሠራው ሥራ ሁሉ ደስታ ከማግኘት የተሻለ ነገር የለም። ይህ የአምላክ ስጦታ ነው።+ 14  እውነተኛው አምላክ የሚሠራው ነገር ሁሉ ለዘላለም ጸንቶ እንደሚኖር ተረድቻለሁ። በእሱ ላይ የሚጨመር ምንም ነገር የለም፤ ከእሱም ላይ የሚቀነስ ምንም ነገር የለም። እውነተኛው አምላክ በዚህ መንገድ የሠራው ሰዎች ይፈሩት ዘንድ ነው።+ 15  አሁን የሚሆነው ነገር ሁሉ ከዚህ በፊት የሆነ ነው፤ ወደፊት የሚመጣው ነገር ከዚህ በፊት የነበረ ነው፤+ ሆኖም እውነተኛው አምላክ፣ ሲያሳድዱት የነበረውን* አጥብቆ ይሻዋል። 16  ደግሞም ከፀሐይ በታች ይህን አየሁ፦ በፍትሕ ቦታ ክፋት፣ በጽድቅም ቦታ ክፋት ነበር።+ 17  እኔም በልቤ እንዲህ አልኩ፦ “እውነተኛው አምላክ በጻድቁም ሆነ በኃጢአተኛው ላይ ይፈርዳል፤+ ማንኛውም ድርጊትና ማንኛውም ተግባር ጊዜ አለውና።” 18  እኔም በልቤ፣ እውነተኛው አምላክ የሰው ልጆችን ይፈትናቸዋል፤ እንደ እንስሳት መሆናቸውንም ያሳያቸዋል አልኩ፤ 19  የሰው ልጆች ፍጻሜና* የእንስሳት ፍጻሜ ተመሳሳይ ነውና፤ የሁሉም ፍጻሜ አንድ ነው።+ አንዱ እንደሚሞት ሌላውም እንዲሁ ይሞታል፤ የሁሉም መንፈስ አንድ ዓይነት ነው።+ በመሆኑም ሰው ከእንስሳ ብልጫ የለውም፤ ሁሉም ከንቱ ነውና። 20  ሁሉም ወደ አንድ ቦታ ይሄዳሉ።+ ሁሉም የተገኙት ከአፈር ነው፤+ ሁሉም ወደ አፈር ይመለሳሉ።+ 21  የሰው ልጆች መንፈስ ወደ ላይ ይወጣ እንደሆነ፣ የእንስሳት መንፈስ ደግሞ ወደ ታች ወደ ምድር ይወርድ እንደሆነ በእርግጠኝነት የሚያውቅ ማን ነው?+ 22  ሰው በሥራው ደስ ከመሰኘት የተሻለ ነገር እንደሌለው አስተዋልኩ፤+ ምክንያቱም ይህ ወሮታው* ነው፤ እሱ ካለፈ በኋላ የሚከናወነውን ነገር ተመልሶ እንዲያይ ሊያደርገው የሚችል ማን ነው?+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ለመውለድ ጊዜ አለው።”
ቃል በቃል “ለመዝለል፤ ለመፈንጨት።”
ወይም “በሚገባ የተደራጀ፤ ሥርዓታማ፤ ተስማሚ።”
“ያለፈውን” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ዕጣ ፋንታና።”
ወይም “ድርሻው።”