መዝሙር 107:1-43
107 ይሖዋ ጥሩ+ ስለሆነ ምስጋና አቅርቡለት፤ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።+
2 ይሖዋ የዋጃቸው፣*አዎ፣ ከጠላት እጅ* የዋጃቸው+ ይህን ይበሉ፤
3 ከምሥራቅና ከምዕራብ፣*ከሰሜንና ከደቡብ፣ከየአገሩ አንድ ላይ የሰበሰባቸው+ ይህን ይናገሩ።
4 በምድረ በዳ፣ በበረሃም ተቅበዘበዙ፤ሊኖሩ ወደሚችሉበት ከተማ የሚወስድ መንገድ አላገኙም።
5 ተርበውና ተጠምተው ነበር፤ኃይላቸው ከመሟጠጡ የተነሳ ተዝለፈለፉ።*
6 በተጨነቁ ጊዜ ወደ ይሖዋ ይጮኹ ነበር፤+እሱም ከደረሰባቸው መከራ ታደጋቸው።+
7 መኖር ወደሚችሉበት ከተማ እንዲደርሱ+በትክክለኛው መንገድ መራቸው።+
8 ሕዝቦች ስለ ታማኝ ፍቅሩናለሰው ልጆች ስላደረጋቸው አስደናቂ ሥራዎች+ ይሖዋን ያመስግኑት።+
9 እሱ የተጠማውን* አርክቷልና፤የተራበውንም* በመልካም ነገሮች አጥግቧል።+
10 አንዳንዶች በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የሚኖሩ፣በመከራ ውስጥ ያሉና በሰንሰለት የተጠፈሩ እስረኞች ነበሩ።
11 በአምላክ ቃል ላይ ዓምፀዋልና፤የልዑሉን አምላክ ምክር ንቀዋል።+
12 ስለዚህ በደረሰባቸው መከራ ልባቸው እንዲለሰልስ አደረገ፤+ተሰናከሉ፤ የሚረዳቸውም አንዳች ሰው አልነበረም።
13 በተጨነቁ ጊዜ እርዳታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ተጣሩ፤እሱም ከደረሰባቸው መከራ አዳናቸው።
14 ከድቅድቅ ጨለማ አወጣቸው፤የታሰሩበትንም ሰንሰለት በጠሰ።+
15 ሕዝቦች ስለ ታማኝ ፍቅሩናለሰው ልጆች ስላደረጋቸው አስደናቂ ሥራዎች ይሖዋን ያመስግኑት።+
16 እሱ የመዳብ በሮችን ሰብሯልና፤የብረት መወርወሪያዎችንም ቆርጧል።+
17 ከጥፋታቸውና ከበደላቸው የተነሳ+ሞኝ ሆኑ፤ ለመከራም ተዳረጉ።+
18 የምግብ ፍላጎታቸው ሙሉ በሙሉ ጠፋ፤*ወደ ሞት ደጆች ቀረቡ።
19 በተጨነቁ ጊዜ እርዳታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ይጣሩ ነበር፤እሱም ከደረሰባቸው መከራ ያድናቸው ነበር።
20 ቃሉን ልኮ ይፈውሳቸው፣+ከተያዙበትም ጉድጓድ ይታደጋቸው ነበር።
21 ሕዝቦች ስለ ታማኝ ፍቅሩናለሰው ልጆች ስላደረጋቸው አስደናቂ ሥራዎች ይሖዋን ያመስግኑት።
22 የምስጋና መሥዋዕት ያቅርቡ፤+በእልልታም ሥራዎቹን ያስታውቁ።
23 በባሕር ላይ በመርከቦች የሚጓዙ፣በሰፋፊ ውኃዎች ላይ ንግድ የሚያካሂዱ፣+
24 እነሱ የይሖዋን ሥራዎች፣በጥልቁም ውስጥ ያከናወናቸውን አስደናቂ ነገሮች+ ተመልክተዋል፤
25 እሱ በቃሉ አውሎ ነፋስ ሲያስነሳ፣+የባሕሩንም ማዕበል ሲያናውጥ አይተዋል።
26 ወደ ሰማይ ይወጣሉ፣ወደ ጥልቆችም ይወርዳሉ።
እየመጣባቸው ካለው መከራ የተነሳ ሐሞታቸው ፈሰሰ።*
27 እንደሰከረ ሰው ይንገዳገዳሉ፤ ደግሞም ይወላገዳሉ፤ችሎታቸውም ሁሉ የፈየደላቸው ነገር የለም።+
28 በዚህ ጊዜ ከጭንቀታቸው የተነሳ ወደ ይሖዋ ይጮኻሉ፤+እሱም ከደረሰባቸው መከራ ይታደጋቸዋል።
29 አውሎ ነፋሱ እንዲቆም ያደርጋል፤የባሕሩም ሞገዶች ጸጥ ይላሉ።+
30 ሞገዶቹ ጸጥ ሲሉ ሰዎቹ ሐሴት ያደርጋሉ፤እሱም ወዳሰቡት ወደብ ይመራቸዋል።
31 ሕዝቦች ስለ ታማኝ ፍቅሩናለሰው ልጆች ስላደረጋቸው አስደናቂ ሥራዎች ይሖዋን ያመስግኑት።+
32 በሕዝብ ጉባኤ መካከል ከፍ ከፍ ያድርጉት፤+በሽማግሌዎችም ሸንጎ* ያወድሱት።
33 እሱ ወንዞችን ወደ በረሃ፣የውኃ ምንጮችንም ወደ ደረቅ መሬት ይለውጣል፤+
34 ከነዋሪዎቿ ክፋት የተነሳፍሬያማዋን አገር ጨዋማ የሆነ ጠፍ ምድር ያደርጋታል።+
35 በረሃውን ቄጠማ የሞላበት ኩሬ፣ደረቁንም ምድር የውኃ ምንጭ ያደርጋል።+
36 ሊኖሩ የሚችሉበትን ከተማ እንዲመሠርቱ፣+የተራቡ ሰዎችን በዚያ ያኖራል።+
37 መሬት ላይ ዘሩ፤ ወይንም ተከሉ፤+መሬቱም ብዙ ምርት ሰጠ።+
38 እሱ ይባርካቸዋል፤ እነሱም እጅግ ይበዛሉ፤የከብቶቻቸው ብዛት እንዲያንስ አያደርግም።+
39 ሆኖም ከደረሰባቸው ጭቆና፣ መከራና ሐዘን የተነሳዳግመኛ ቁጥራቸው ተመናመነ፤ ተዋረዱም።
40 በታላላቅ ሰዎች ላይ የውርደት መዓት ያዘንባል፤መንገድ በሌለበት ጠፍ መሬትም እንዲቅበዘበዙ ያደርጋል።+
41 ድሆችን ግን ከጭቆና ይጠብቃል፤*+ቤተሰባቸውንም እንደ መንጋ ያበዛል።
42 ቅኖች ይህን አይተው ሐሴት ያደርጋሉ፤+ዓመፀኞች ሁሉ ግን አፋቸውን ይዘጋሉ።+
43 ጥበበኛ የሆነ ሁሉ እነዚህን ነገሮች ልብ ይላል፤+ደግሞም ይሖዋ በታማኝ ፍቅር ያከናወናቸውን ነገሮች በትኩረት ይመለከታል።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “ይሖዋ የተቤዣቸው።”
^ ወይም “ኃይል።”
^ ወይም “ከፀሐይ መውጫና ከፀሐይ መግቢያ።”
^ ወይም “ነፍሳቸው ተዝለፈለፈች።”
^ ወይም “የተጠማችውን ነፍስ።”
^ ወይም “የተራበችውንም ነፍስ።”
^ ወይም “ነፍሳቸው ማንኛውንም ምግብ ተጸየፈች።”
^ ወይም “ነፍሳቸው ቀለጠች።”
^ ቃል በቃል “መቀመጫ።”
^ ወይም “ከፍ ያለ ቦታ ላይ ያስቀምጣቸዋል።” የማይደረስበት ቦታ ላይ ያደርጋቸዋል ማለት ነው።