መዝሙር 62:1-12
ለሙዚቀኞች ቡድን መሪ፤ በየዱቱን።* የዳዊት ማህሌት።
62 ዝም ብዬ አምላክን እጠባበቃለሁ።*
መዳን የማገኘው ከእሱ ዘንድ ነው።+
2 በእርግጥም እሱ ዓለቴና አዳኜ እንዲሁም አስተማማኝ መጠጊያዬ ነው፤+ከልክ በላይ አልናወጥም።+
3 አንድን ሰው ለመግደል ጥቃት የምትሰነዝሩበት እስከ መቼ ነው?+
ሁላችሁም እንዳዘመመ ግንብ፣ ሊወድቅ እንደተቃረበም የድንጋይ ቅጥር አደገኛ ናችሁ።*
4 ካለበት ከፍ ያለ ቦታ ሊጥሉት* እርስ በርሳቸው ይማከራሉና፤በመዋሸት ደስ ይሰኛሉ።
በአፋቸው ይባርካሉ፤ በልባቸው ግን ይራገማሉ።+ (ሴላ)
5 ዝም ብዬ አምላክን እጠባበቃለሁ፤*+ምክንያቱም ተስፋዬ የሚመጣው ከእሱ ዘንድ ነው።+
6 በእርግጥም እሱ ዓለቴና አዳኜ እንዲሁም አስተማማኝ መጠጊያዬ ነው፤በምንም ዓይነት አልናወጥም።+
7 የእኔ መዳንና ክብር የተመካው በአምላክ ላይ ነው።
እሱ ጠንካራ ዓለቴና መጠጊያዬ ነው።+
8 ሰዎች ሆይ፣ ሁልጊዜ በእሱ ታመኑ።
ልባችሁን በፊቱ አፍስሱ።+
አምላክ መጠጊያችን ነው።+ (ሴላ)
9 የሰው ልጆች እስትንፋስ ናቸው፤ሰዎች ከንቱ መመኪያ ናቸው።+
አንድ ላይ ሆነው በሚዛን ሲመዘኑ ከአየር እንኳ ይቀልላሉ።+
10 በዝርፊያ አትታመኑ፤ወይም በስርቆት እጠቀማለሁ ብላችሁ በከንቱ ተስፋ አታድርጉ።
ሀብታችሁ ቢበዛ ልባችሁን በእሱ ላይ አትጣሉ።+
11 አምላክ አንድ ጊዜ ተናገረ፤ እኔም ይህን ሁለት ጊዜ ሰማሁ፦
ብርታት የአምላክ ነው።+
12 ይሖዋ ሆይ፣ ታማኝ ፍቅርም የአንተ ነው፤+ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ትከፍላለህና።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ወይም “ነፍሴ ዝም ብላ አምላክን ትጠባበቃለች።”
^ “እሱ ያዘመመ ግንብ፣ ሊወድቅ የተቃረበም የድንጋይ ቅጥር የሆነ ይመስል ሁላችሁም የምታጠቁት እስከ መቼ ነው?” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ ወይም “ከታላቅ ክብሩ ሊያዋርዱት።”
^ ወይም “ነፍሴ ሆይ፣ አምላክን ዝም ብለሽ ተጠባበቂ።”