መዝሙር 72:1-20
ስለ ሰለሞን የተዘመረ መዝሙር።
72 አምላክ ሆይ፣ ፍርዶችህን ለንጉሡ ስጥ፤ጽድቅህንም ለንጉሡ ልጅ አጎናጽፍ።+
2 ስለ ሕዝብህ በጽድቅ ይሟገት፤ለተቸገሩ አገልጋዮችህም ፍትሕ ያስፍን።+
3 ተራሮች ለሕዝቡ ሰላም ያምጡ፤ኮረብቶችም ጽድቅን ያስገኙ።
4 በሕዝቡ መካከል ላሉት ችግረኞች ጥብቅና ይቁም፤*የድሃውን ልጆች ያድን፤ቀማኛውንም ይደምስሰው።+
5 ፀሐይ ብርሃኗን እስከሰጠች፣ጨረቃም በሰማይ ላይ እስካለች ድረስ፣ከትውልድ እስከ ትውልድ+ አንተን ይፈሩሃል።
6 እሱ በታጨደ ሣር ላይ እንደሚዘንብ ዝናብ፣ምድርንም እንደሚያጠጣ ካፊያ ይወርዳል።+
7 በእሱ ዘመን ጻድቅ ይለመልማል፤*+ጨረቃም በምትኖርበት ዘመን ሁሉ ሰላም ይበዛል።+
8 ከባሕር እስከ ባሕር ድረስ፣ከወንዙም* እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ተገዢዎች ይኖሩታል።*+
9 በበረሃ የሚኖሩ ሰዎች በፊቱ ይሰግዳሉ፤ጠላቶቹም አፈር ይልሳሉ።+
10 የተርሴስና የደሴቶች ነገሥታት፣ ግብር ያመጣሉ።+
የሳባና የሴባ ነገሥታት፣ ስጦታ ይሰጣሉ።+
11 ነገሥታትም ሁሉ በፊቱ ይሰግዳሉ፤ብሔራትም ሁሉ ያገለግሉታል።
12 እርዳታ ለማግኘት የሚጮኸውን ድሃ፣እንዲሁም ችግረኛውንና ረዳት የሌለውን ሁሉ ይታደጋልና።
13 ለችግረኛውና ለድሃው ያዝናል፤የድሆችንም ሕይወት* ያድናል።
14 ከጭቆናና ከግፍ ይታደጋቸዋል፤*ደማቸውም በዓይኖቹ ፊት ክቡር ነው።
15 ረጅም ዘመን ይኑር፤ የሳባም ወርቅ ይሰጠው።+
ስለ እሱም ሁልጊዜ ጸሎት ይቅረብ፤ቀኑንም ሙሉ ይባረክ።
16 በምድር ላይ እህል ይትረፈረፋል፤+በተራሮችም አናት ላይ በብዛት ይኖራል።
የንጉሡም ፍሬ እንደ ሊባኖስ ዛፎች ይንዠረገጋል፤+በከተሞቹም ውስጥ ሰዎች በምድር ላይ እንዳሉ ዕፀዋት ያብባሉ።+
17 ስሙ ለዘላለም ጸንቶ ይኑር፤+ፀሐይም እስካለች ድረስ ስሙ ይግነን።
ሰዎች በእሱ አማካኝነት ለራሳቸው በረከት ያግኙ፤+ብሔራት ሁሉ ደስተኛ ብለው ይጥሩት።
18 እሱ ብቻ አስደናቂ ነገሮችን የሚያደርገው፣+የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ይወደስ።+
19 ክብራማ ስሙ ለዘላለም ይወደስ፤+ምድርም ሁሉ በክብሩ ትሞላ።+
አሜን፣ አሜን።
20 የእሴይ ልጅ+ የዳዊት ጸሎቶች እዚህ ላይ አበቁ።
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ቃል በቃል “ይፍረድ።”
^ ቃል በቃል “ያቆጠቁጣል።”
^ ኤፍራጥስን ያመለክታል።
^ ወይም “ይገዛል።”
^ ወይም “ነፍስ።”
^ ወይም “ነፍሳቸውን ይዋጃል።”