መዝሙር 90:1-17
የእውነተኛው አምላክ ሰው የሙሴ ጸሎት።+
90 ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ከትውልድ እስከ ትውልድ መኖሪያችን* ሆነሃል።+
2 ተራሮች ሳይወለዱ፣ምድርንና ዓለምን ከመፍጠርህ*+ በፊት፣ከዘላለም እስከ ዘላለም አንተ አምላክ ነህ።+
3 ሟች የሆነ ሰው ወደ አፈር እንዲመለስ ታደርጋለህ፤“የሰው ልጆች ሆይ፣ ወደ አፈር ተመለሱ”+ ትላለህ።
4 በአንተ ዘንድ ሺህ ዓመት፣ እንዳለፈችው እንደ ትናንት ቀን፣+እንደ አንድ ክፍለ ሌሊትም* ነው።
5 ጠራርገህ ታስወግዳቸዋለህ፤+ እንደ ሕልም ይጠፋሉ፤በማለዳ ሲታዩ እንደሚለመልም ሣር ናቸው።+
6 ጠዋት ላይ ሣሩ ያቆጠቁጣል፤ ደግሞም ይለመልማል፤ምሽት ላይ ግን ጠውልጎ ይደርቃል።+
7 በቁጣህ አልቀናልና፤+ከታላቅ ቁጣህም የተነሳ ተሸብረናል።
8 በደላችንን በፊትህ ታኖራለህ፤*+የደበቅናቸው ነገሮች በፊትህ ብርሃን ተጋልጠዋል።+
9 ከኃይለኛ ቁጣህ የተነሳ ዘመናችን* ይመናመናል፤ዕድሜያችንም ሽው ብሎ ያልፋል።*
10 የዕድሜያችን ርዝማኔ 70 ዓመት ነው፤ለየት ያለ ጥንካሬ ካለን* ደግሞ 80+ ዓመት ቢሆን ነው።
ይህም በችግርና በሐዘን የተሞላ ነው፤ፈጥኖ ይነጉዳል፤ እኛም እናልፋለን።+
11 የቁጣህን ኃይል መረዳት የሚችል ማን ነው?
ቁጣህ፣ አንተ መፈራት የሚገባህን ያህል ታላቅ ነው።+
12 ጥበበኛ ልብ ማግኘት እንችል ዘንድ፣ዕድሜያችንን እንዴት መቁጠር እንዳለብን አስተምረን።+
13 ይሖዋ ሆይ፣ ተመለስ!+ ይህ ሁኔታ የሚቀጥለው እስከ መቼ ነው?+
ለአገልጋዮችህ ራራላቸው።+
14 በሕይወት ዘመናችን ሁሉ እልል እንድንልና ሐሴት እንድናደርግ፣+በማለዳ ታማኝ ፍቅርህን አጥግበን።+
15 ባጎሳቆልከን ዘመን ልክ፣መከራም ባየንባቸው ዓመታት መጠን+ ሐሴት እንዲሰማን አድርገን።+
16 አገልጋዮችህ ሥራህን ይዩ፤ልጆቻቸውም ግርማህን ይመልከቱ።+
17 የአምላካችን የይሖዋ ሞገስ በእኛ ላይ ይሁን፤የእጆቻችንን ሥራ ፍሬያማ አድርግልን።*
አዎ፣ የእጆቻችንን ሥራ ፍሬያማ አድርግልን።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ “መጠጊያችን” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ ወይም “አምጠህ ከመውለድህ።”
^ ክፍለ ሌሊት ፀሐይ ከጠለቀችበት አንስቶ እስከምትወጣበት ድረስ ካለው ጊዜ ውስጥ አንድ ሦስተኛውን ይሸፍናል። በመሆኑም እንደ ወቅቱ ሁኔታ፣ አንድ ክፍለ ሌሊት የአራት ሰዓት ገደማ ርዝማኔ ሊኖረው ይችላል።
^ ወይም “በደላችንን ታውቃለህ።”
^ ወይም “ሕይወታችን።”
^ ወይም “እንደ እስትንፋስ ወዲያው ያከትማል።”
^ ወይም “ልዩ ብርታት ቢኖረን።”
^ ወይም “አጽናልን።”