መዝሙር 97:1-12

  • ይሖዋ ከሌሎች አማልክት በላይ ከፍ ከፍ ያለ ነው

    • “ይሖዋ ነገሠ!” (1)

    • ይሖዋን የምትወዱ፣ ክፋትን ጥሉ (10)

    • “ብርሃን ለጻድቃን ወጣ” (11)

97  ይሖዋ ነገሠ!+ ምድር ደስ ይበላት።+ ብዙ ደሴቶችም ሐሴት ያድርጉ።+  2  ደመናና ድቅድቅ ጨለማ በዙሪያው አለ፤+ጽድቅና ፍትሕ የዙፋኑ መሠረት ናቸው።+  3  እሳት በፊቱ ይሄዳል፤+ጠላቶቹንም በሁሉም አቅጣጫ ይፈጃል።+  4  የመብረቅ ብልጭታዎቹ በመሬት ላይ አበሩ፤ምድር ይህን አይታ ተንቀጠቀጠች።+  5  ተራሮች በይሖዋ ፊት፣በምድርም ሁሉ ጌታ ፊት እንደ ሰም ቀለጡ።+  6  ሰማያት ጽድቁን ያውጃሉ፤ሕዝቦችም ሁሉ ክብሩን ያያሉ።+  7  ማንኛውንም የተቀረጸ ምስል የሚያመልኩ ሁሉ፣ከንቱ በሆኑ አማልክታቸው የሚኩራሩ ይፈሩ።+ እናንተ አማልክት ሁሉ፣ ለእሱ ስገዱ።*+  8  ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ስላስተላለፍካቸው የፍርድ ውሳኔዎች፣ጽዮን ሰምታ ሐሴት አደረገች፤የይሁዳ ከተሞች* ደስ አላቸው።+  9  ይሖዋ ሆይ፣ አንተ በመላው ምድር ላይ ልዑል ነህና፤ከሌሎች አማልክት ሁሉ በላይ እጅግ ከፍ ከፍ ብለሃል።+ 10  እናንተ ይሖዋን የምትወዱ፣ ክፉ የሆነውን ነገር ጥሉ።+ እሱ የታማኝ አገልጋዮቹን ሕይወት* ይጠብቃል፤+ከክፉዎች እጅ* ይታደጋቸዋል።+ 11  ብርሃን ለጻድቃን ወጣ፤ደስታም ለልበ ቅኖች ተዳረሰ።+ 12  እናንተ ጻድቃን፣ በይሖዋ ሐሴት አድርጉ፤ለቅዱስ ስሙም* ምስጋና አቅርቡ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “እሱን አምልኩ።”
ቃል በቃል “ሴት ልጆች።”
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ኃይል።”
ቃል በቃል “ለቅዱስ መታሰቢያውም።”