የማርቆስ ወንጌል 10:1-52

  • ጋብቻና ፍቺ (1-12)

  • ኢየሱስ ልጆችን ባረከ (13-16)

  • አንድ ሀብታም ሰው ያቀረበው ጥያቄ (17-25)

  • ለመንግሥቱ ሲባል መሥዋዕትነት መክፈል (26-31)

  • ኢየሱስ እንደሚሞት በድጋሚ ተናገረ (32-34)

  • ያዕቆብና ዮሐንስ ያቀረቡት ጥያቄ (35-45)

    • ኢየሱስ የመጣው ለብዙዎች ቤዛ ሊሆን ነው (45)

  • ዓይነ ስውሩ በርጤሜዎስ ተፈወሰ (46-52)

10  ከዚያም ተነስቶ ከዮርዳኖስ ማዶ ወዳሉት የይሁዳ ድንበሮች መጣ፤ ብዙ ሰዎችም እንደገና ወደ እሱ ተሰበሰቡ። አሁንም እንደ ልማዱ ያስተምራቸው ጀመር።+ 2  ፈሪሳውያንም ቀርበው እሱን ለመፈተን በማሰብ አንድ ሰው ሚስቱን እንዲፈታ ሕግ ይፈቅድለት እንደሆነ ጠየቁት።+ 3  እሱም መልሶ “ሙሴ ምን ብሎ ነው ያዘዛችሁ?” አላቸው። 4  እነሱም “ሙሴ የፍቺ የምሥክር ወረቀት ጽፎ እንዲፈታት ፈቅዷል” አሉት።+ 5  ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው፦ “ሙሴ ይህን ትእዛዝ የጻፈላችሁ ልባችሁ ደንዳና+ መሆኑን አይቶ ነው።+ 6  ይሁን እንጂ በፍጥረት መጀመሪያ ‘አምላክ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።+ 7  ከዚህ የተነሳ ሰው ከአባቱና ከእናቱ ይለያል፤+ 8  ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ’፤+ በመሆኑም ከዚህ በኋላ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም። 9  ስለዚህ አምላክ ያጣመረውን* ማንም ሰው አይለያየው።”+ 10  እንደገና ወደ ቤት በገቡ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ ጉዳይ ይጠይቁት ጀመር። 11  እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ሚስቱን ፈቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ በማመንዘር+ ሚስቱን ይበድላል፤ 12  አንዲት ሴትም ብትሆን ባሏን ፈታ ሌላ ብታገባ ታመነዝራለች።”+ 13  ሰዎችም ኢየሱስ እጁን እንዲጭንባቸው ትናንሽ ልጆችን ወደ እሱ ያመጡ ጀመር፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ገሠጿቸው።+ 14  ኢየሱስ ይህን ሲያይ ተቆጥቶ እንዲህ አላቸው፦ “ልጆቹ ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሏቸው፤ የአምላክ መንግሥት እንደነዚህ ላሉት ነውና።+ 15  እውነት እላችኋለሁ፣ የአምላክን መንግሥት እንደ አንድ ትንሽ ልጅ ሆኖ የማይቀበል ሁሉ ፈጽሞ ወደዚህ መንግሥት አይገባም።”+ 16  ልጆቹንም አቀፋቸው፤ እጁንም ጭኖ ባረካቸው።+ 17  ከዚያ ወጥቶ በመሄድ ላይ ሳለ አንድ ሰው እየሮጠ መጣ፤ በፊቱም በጉልበቱ ተንበርክኮ “ጥሩ መምህር ሆይ፣ የዘላለም ሕይወት ለመውረስ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?” ሲል ጠየቀው።+ 18  ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “ለምን ጥሩ ብለህ ትጠራኛለህ? ከአንዱ ከአምላክ በቀር ጥሩ የለም።+ 19  ‘አትግደል፣+ አታመንዝር፣+ አትስረቅ፣+ በሐሰት አትመሥክር፣+ አታታል፣+ አባትህንና እናትህን አክብር’+ የሚሉትን ትእዛዛት ታውቃለህ።” 20  ሰውየውም “መምህር፣ እነዚህን ሁሉ ከልጅነቴ ጀምሮ ስጠብቅ ኖሬአለሁ” አለው። 21  ኢየሱስም ተመለከተውና ወደደው፤ ከዚያም “አንድ ነገር ይጎድልሃል፤ ሂድና ያለህን ነገር ሁሉ ሸጠህ ገንዘቡን ለድሆች ስጥ፤ በሰማይም ውድ ሀብት ታገኛለህ፤ ደግሞም መጥተህ ተከታዬ ሁን” አለው።+ 22  ሰውየው ግን ይህን ሲሰማ አዘነ፤ ብዙ ንብረት ስለነበረውም እያዘነ ሄደ።+ 23  ኢየሱስ ዙሪያውን ከተመለከተ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን “ገንዘብ ላላቸው ሰዎች ወደ አምላክ መንግሥት መግባት ምንኛ አስቸጋሪ ነው!” አላቸው።+ 24  ደቀ መዛሙርቱ ግን በንግግሩ ተገረሙ። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “ልጆቼ ሆይ፣ ወደ አምላክ መንግሥት መግባት እንዴት አስቸጋሪ ነው! 25  ሀብታም ሰው ወደ አምላክ መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀልላል።”+ 26  ደቀ መዛሙርቱ ይበልጥ በመገረም “ታዲያ ማን ሊድን ይችላል?” አሉት።*+ 27  ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ትኩር ብሎ በመመልከት “ይህ በሰዎች ዘንድ አይቻልም፤ በአምላክ ዘንድ ግን እንዲህ አይደለም፤ በአምላክ ዘንድ ሁሉ ነገር ይቻላል” አለ።+ 28  ጴጥሮስም “እነሆ፣ እኛ ሁሉን ትተን ተከትለንሃል” አለው።+ 29  ኢየሱስም እንዲህ አለ፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ ስለ እኔና ስለ ምሥራቹ ሲል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እህቶችን ወይም እናትን ወይም አባትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ፣+ 30  አሁን በዚህ ዘመን ከስደት+ ጋር ቤቶችን፣ ወንድሞችን፣ እህቶችን፣ እናቶችን፣ ልጆችንና እርሻን 100 እጥፍ፣ በሚመጣው ሥርዓት* ደግሞ የዘላለም ሕይወት ያገኛል። 31  ሆኖም ፊተኞች የሆኑ ብዙዎች ኋለኞች፣ ኋለኞች የሆኑ ደግሞ ፊተኞች ይሆናሉ።”+ 32  ወደ ኢየሩሳሌም በሚወስደው መንገድ እያቀኑ ሳሉ ኢየሱስ ከፊት ከፊታቸው ይሄድ ነበር፤ እነሱም ተደነቁ፤ ይከተሉት የነበሩት ሰዎች ግን ፍርሃት አደረባቸው። እሱም እንደገና አሥራ ሁለቱን ገለል አድርጎ በመውሰድ የሚደርስበትን ነገር ይነግራቸው ጀመር፦+ 33  “እነሆ፣ ወደ ኢየሩሳሌም እየወጣን ነው፤ የሰው ልጅ ለካህናት አለቆችና ለጸሐፍት አልፎ ይሰጣል። እነሱም ሞት ይፈርዱበታል፤ ለአሕዛብም አሳልፈው ይሰጡታል፤ 34  ያፌዙበታል፤ ይተፉበታል፤ ይገርፉታል፤ ከዚያም ይገድሉታል፤ ሆኖም ከሦስት ቀን በኋላ ይነሳል።”+ 35  ሁለቱ የዘብዴዎስ ልጆች+ ያዕቆብና ዮሐንስ ወደ እሱ ቀርበው “መምህር፣ የምንለምንህን ማንኛውንም ነገር እንድታደርግልን እንፈልጋለን” አሉት።+ 36  እሱም “ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። 37  እነሱም “በክብር ቦታህ ላይ ስትቀመጥ አንዳችን በቀኝህ፣ አንዳችን ደግሞ በግራህ እንድንቀመጥ ፍቀድልን” ሲሉ መለሱለት።+ 38  ኢየሱስ ግን “የምትለምኑትን አታውቁም። እኔ እየጠጣሁት ያለውን ጽዋ ልትጠጡ ወይም እኔ እየተጠመቅኩት ያለውን ጥምቀት ልትጠመቁ ትችላላችሁ?” አላቸው።+ 39  እነሱም “እንችላለን” አሉት። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “እኔ እየጠጣሁት ያለውን ጽዋ ትጠጣላችሁ፤ እኔ እየተጠመቅኩት ያለውን ጥምቀት ትጠመቃላችሁ።+ 40  በቀኜ ወይም በግራዬ መቀመጥ ግን ለተዘጋጀላቸው የሚሰጥ እንጂ በእኔ ፈቃድ የሚሆን አይደለም።” 41  የቀሩት አሥሩ ይህን ሲሰሙ በያዕቆብና በዮሐንስ ላይ ተቆጡ።+ 42  ሆኖም ኢየሱስ ወደ እሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “ብሔራትን የሚገዙ* ነገሥታት በሕዝባቸው ላይ ሥልጣናቸውን እንደሚያሳዩ፣ ታላላቆቻቸውም በኃይል እንደሚገዟቸው ታውቃላችሁ።+ 43  በእናንተ መካከል ግን እንዲህ መሆን የለበትም፤ ከመካከላችሁ ታላቅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ አገልጋያችሁ ሊሆን ይገባል፤+ 44  እንዲሁም ከመካከላችሁ ፊተኛ መሆን የሚፈልግ ሁሉ፣ የሁሉ ባሪያ ሊሆን ይገባል። 45  ምክንያቱም የሰው ልጅ እንኳ የመጣው ለማገልገልና+ በብዙ ሰዎች ምትክ ሕይወቱን* ቤዛ አድርጎ ለመስጠት+ እንጂ እንዲገለገል አይደለም።” 46  ከዚያም ወደ ኢያሪኮ መጡ። እሱና ደቀ መዛሙርቱ ከብዙ ሕዝብ ጋር ከኢያሪኮ ሲወጡ ዓይነ ስውሩ የጤሜዎስ ልጅ በርጤሜዎስ መንገድ ዳር ተቀምጦ ይለምን ነበር።+ 47  እሱም የናዝሬቱ ኢየሱስ መሆኑን ሲሰማ “የዳዊት ልጅ፣+ ኢየሱስ ሆይ፣ ምሕረት አድርግልኝ!”+ እያለ ይጮኽ ጀመር። 48  በዚህ ጊዜ ብዙዎች ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እሱ ግን “የዳዊት ልጅ ሆይ፣ ምሕረት አድርግልኝ!” እያለ ይበልጥ መጮኹን ቀጠለ። 49  ኢየሱስም ቆመና “ጥሩት” አለ። እነሱም ዓይነ ስውሩን “አይዞህ! ተነስ፤ እየጠራህ ነው” አሉት። 50  እሱም መደረቢያውን ጥሎ ዘሎ በመነሳት ወደ ኢየሱስ ሄደ። 51  ኢየሱስም “ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?” አለው። ዓይነ ስውሩም “ራቦኒ፣* የዓይኔን ብርሃን መልስልኝ” አለው። 52  ኢየሱስም “ሂድ፣ እምነትህ አድኖሃል” አለው።+ ወዲያውም የዓይኑ ብርሃን ተመለሰለት፤+ እሱም ከሕዝቡ ጋር አብሮ ይከተለው ጀመር።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “በአንድ ቀንበር ያጣመደውን።”
“ተባባሉ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ብሔራትን እንደሚገዙ ተደርገው የሚታሰቡ።”
ወይም “ነፍሱን።”
“መምህር” የሚል ትርጉም አለው።