የማርቆስ ወንጌል 13:1-37

  • የሥርዓቱ መደምደሚያ (1-37)

    • ጦርነት፣ የምድር ነውጥ፣ የምግብ እጥረት (8)

    • ምሥራቹ ይሰበካል (10)

    • ታላቅ መከራ (19)

    • የሰው ልጅ መምጣት (26)

    • የበለስ ዛፍ ምሳሌ (28-31)

    • “ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ” (32-37)

13  ከቤተ መቅደስ እየወጣ ሳለ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ “መምህር፣ እንዴት ያሉ ግሩም ድንጋዮችና ሕንጻዎች እንደሆኑ ተመልከት!” አለው።+ 2  ኢየሱስ ግን “እነዚህን ታላላቅ ሕንጻዎች ታያለህ? ይህ ሁሉ ሳይፈርስ እንዲህ ድንጋይ በድንጋይ ላይ እንደተነባበረ ከቶ አይኖርም” አለው።+ 3  በቤተ መቅደሱ ትይዩ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብ፣ ዮሐንስና እንድርያስ ብቻቸውን ሆነው እንዲህ በማለት ጠየቁት፦ 4  “እስቲ ንገረን፣ እነዚህ ነገሮች የሚፈጸሙት መቼ ነው? የእነዚህ ነገሮች ሁሉ መደምደሚያ መቅረቡን የሚያሳየው ምልክትስ ምንድን ነው?”+ 5  ኢየሱስም እንዲህ ይላቸው ጀመር፦ “ማንም እንዳያሳስታችሁ ተጠንቀቁ።+ 6  ብዙዎች ‘እኔ እሱ ነኝ’ እያሉ በስሜ ይመጣሉ፤ ብዙዎችንም ያሳስታሉ። 7  ከዚህም ሌላ ጦርነትና የጦርነት ወሬ ስትሰሙ አትደናገጡ፤ እነዚህ ነገሮች መፈጸማቸው የግድ ነው፤ ሆኖም ፍጻሜው ገና ነው።+ 8  “ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳልና፤+ በተለያየ ስፍራ የምድር ነውጥ ይከሰታል፤ በተጨማሪም የምግብ እጥረት ይኖራል።+ እነዚህ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።+ 9  “እናንተ ግን ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ሰዎች ለፍርድ ሸንጎዎች አሳልፈው ይሰጧችኋል፤+ በምኩራብም ትገረፋላችሁ፤+ በእኔ ምክንያት በገዢዎችና በነገሥታት ፊት ያቀርቧችኋል፤ በዚያ ጊዜ ለእነሱ መመሥከር ትችላላችሁ።+ 10  አስቀድሞም ምሥራቹ ለብሔራት ሁሉ መሰበክ አለበት።+ 11  አሳልፈው ለመስጠት በሚወስዷችሁ ጊዜም ምን እንላለን በማለት አስቀድማችሁ አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ በዚያች ሰዓት የሚሰጣችሁን ተናገሩ፤ የሚናገረው መንፈስ ቅዱስ እንጂ እናንተ አይደላችሁምና።+ 12  በተጨማሪም ወንድም ወንድሙን፣ አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሳሉ፤ ደግሞም ያስገድሏቸዋል።+ 13  በስሜ የተነሳም ሰዎች ሁሉ ይጠሏችኋል።+ እስከ መጨረሻው የጸና+ ግን* ይድናል።+ 14  “ይሁንና ጥፋት የሚያመጣው ‘ርኩስ ነገር’+ በማይገባው ስፍራ ቆሞ ስታዩ አንባቢው ያስተውል፤ በዚህ ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ።+ 15  በጣሪያ* ላይ ያለ ሰው አይውረድ፤ አንዳችም ነገር ለመውሰድ ወደ ቤቱ አይግባ፤ 16  በእርሻም ያለ መደረቢያውን ለመውሰድ ወደ ኋላ አይመለስ። 17  በእነዚያ ቀናት ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው!+ 18  ይህ በክረምት እንዳይሆን ዘወትር ጸልዩ፤ 19  ምክንያቱም በእነዚያ ቀናት ከአምላክ የፍጥረት ሥራ መጀመሪያ አንስቶ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ሆኖ የማያውቅ ዳግመኛም የማይሆን+ መከራ+ ይከሰታል። 20  እንዲያውም ይሖዋ* ቀኖቹን ባያሳጥራቸው ኖሮ ሥጋ ሁሉ ባልዳነ ነበር። ሆኖም እሱ ለመረጣቸው ምርጦች ሲል ቀኖቹን አሳጥሯል።+ 21  “በዚያን ጊዜም ማንም ‘እነሆ፣ ክርስቶስ ይኸውላችሁ’ ወይም ‘እነሆ፣ ያውላችሁ’ ቢላችሁ አትመኑ።+ 22  ምክንያቱም ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት ይነሳሉ፤+ ቢቻላቸው የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ምልክቶችና አስደናቂ ነገሮች ያደርጋሉ። 23  ስለዚህ ተጠንቀቁ።+ ሁሉን ነገር አስቀድሜ ነግሬአችኋለሁ። 24  “ሆኖም በእነዚያ ቀናት፣ ከዚያ መከራ በኋላ ፀሐይ ትጨልማለች፤ ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም፤+ 25  ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ በሰማያት ያሉ ኃይላትም ይናወጣሉ። 26  ከዚያም የሰው ልጅ+ በታላቅ ኃይልና ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል።+ 27  እሱም መላእክቱን ልኮ ከአራቱ ነፋሳት፣ ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ ለእሱ የተመረጡትን ይሰበስባል።+ 28  “እንግዲያው ይህን ምሳሌ ከበለስ ዛፍ ተማሩ፦ ቅርንጫፎቿ ሲለመልሙና ቅጠሎቿ ሲያቆጠቁጡ በጋ* እንደቀረበ ታውቃላችሁ።+ 29  በተመሳሳይ እናንተም እነዚህ ነገሮች ሲፈጸሙ ስታዩ የሰው ልጅ ደጃፍ ላይ እንደደረሰ እርግጠኞች ሁኑ።+ 30  እውነት እላችኋለሁ፣ እነዚህ ነገሮች ሁሉ እስኪፈጸሙ ድረስ ይህ ትውልድ ፈጽሞ አያልፍም።+ 31  ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤+ ቃሌ ግን ፈጽሞ አያልፍም።+ 32  “ስለዚያ ቀን ወይም ሰዓት ከአብ በቀር በሰማይ ያሉ መላእክትም ሆኑ ወልድ፣ ማንም አያውቅም።+ 33  ስለዚህ የተወሰነው ጊዜ መቼ እንደሆነ ስለማታውቁ+ ምንጊዜም በንቃት ተከታተሉ፤ ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ።+ 34  ይህም ለባሪያዎቹ ሥልጣን ከሰጠና ለእያንዳንዱ የሥራ ድርሻውን ከመደበ በኋላ በር ጠባቂውን ነቅቶ እንዲጠብቅ በማዘዝ+ ቤቱን ትቶ ወደ ሌላ አገር እንደሄደ ሰው ነው።+ 35  ስለዚህ የቤቱ ጌታ፣ በምሽት* ይሁን በእኩለ ሌሊት* ወይም ዶሮ ሲጮኽ* ይሁን ከመንጋቱ* በፊት፣ መቼ እንደሚመጣ ስለማታውቁ ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ፤+ 36  አለዚያ ድንገት ሲመጣ ተኝታችሁ ያገኛችኋል።+ 37  ይሁንና ለእናንተ የምነግራችሁን ለሁሉም እናገራለሁ፤ ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “የሚጸና ግን።”
ማቴ 24:17 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
በጳለስጢና ምድር ዕፀዋት የሚለመልሙት በበጋ ነው።
“ምሽት።” ግሪካውያንና ሮማውያን የሌሊቱን ጊዜ በሚከፋፍሉበት መሠረት የመጀመሪያው ክፍለ ሌሊት ሲሆን ይህም ፀሐይ ከጠለቀችበት ጊዜ አንስቶ እስከ 3 ሰዓት ገደማ ድረስ ነው።
“እኩለ ሌሊት።” ሁለተኛው ክፍለ ሌሊት ሲሆን ይህም ከምሽቱ 3 ሰዓት ገደማ አንስቶ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ነው።
“ዶሮ ሲጮኽ።” ሦስተኛው ክፍለ ሌሊት ሲሆን ይህም ከእኩለ ሌሊት እስከ ሌሊቱ 9 ሰዓት ገደማ ድረስ ነው።
“ንጋት።” አራተኛው ክፍለ ሌሊት ሲሆን ይህም ከሌሊቱ 9 ሰዓት ገደማ አንስቶ ፀሐይ እስከምትወጣበት ጊዜ ድረስ ነው።