የማርቆስ ወንጌል 5:1-43

  • ኢየሱስ፣ አጋንንቱ ወደ አሳማዎች እንዲገቡ ፈቀደ (1-20)

  • የኢያኢሮስ ሴት ልጅ፤ አንዲት ሴት የኢየሱስን ልብስ ነካች (21-43)

5  ከዚያም ወደ ባሕሩ ማዶ ተሻግረው ጌርጌሴኖን+ ወደተባለው ክልል ደረሱ። 2  ኢየሱስ ከጀልባ እንደወረደ፣ ርኩስ መንፈስ ያደረበት አንድ ሰው ከመቃብር ቦታ ወጥቶ ከእሱ ጋር ተገናኘ። 3  ይህ ሰው በመቃብር ቦታ ይኖር የነበረ ሲሆን እስከዚያ ጊዜ ድረስ በሰንሰለት እንኳ አጥብቆ ሊያስረው የቻለ አንድም ሰው አልነበረም። 4  ብዙ ጊዜ በእግር ብረትና በሰንሰለት ይታሰር የነበረ ቢሆንም ሰንሰለቱን ይበጣጥስ፣ እግር ብረቱንም ይሰባብር ነበር፤ እሱን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የሚያስችል ጉልበት ያለው አንድም ሰው አልነበረም። 5  ዘወትር ሌሊትና ቀን በመቃብር ቦታና በተራሮች ላይ ይጮኽ እንዲሁም ሰውነቱን በድንጋይ ይተለትል ነበር። 6  ኢየሱስን ከሩቅ ባየው ጊዜ ግን ወደ እሱ ሮጦ በመሄድ ሰገደለት።+ 7  ከዚያም በታላቅ ድምፅ እየጮኸ “የልዑል አምላክ ልጅ ኢየሱስ ሆይ፣ እኔ ከአንተ ጋር ምን ጉዳይ አለኝ? እንዳታሠቃየኝ በአምላክ ስም አስምልሃለሁ” አለው።+ 8  ይህን ያለው ኢየሱስ “አንተ ርኩስ መንፈስ ከዚህ ሰው ውጣ”+ ብሎት ስለነበር ነው። 9  ኢየሱስም “ስምህ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀው። እሱም “ብዙ ስለሆንን ስሜ ሌጌዎን* ነው” ብሎ መለሰለት። 10  መናፍስቱን ከአገሪቱ እንዳያስወጣቸውም ኢየሱስን ተማጸነው።+ 11  በዚያም በተራራው ላይ ብዙ የአሳማ+ መንጋ ተሰማርቶ ነበር።+ 12  ርኩሳን መናፍስቱም “አሳማዎቹ ውስጥ እንድንገባ ወደ እነሱ ስደደን” ብለው ተማጸኑት። 13  እሱም ፈቀደላቸው። በዚህ ጊዜ ርኩሳን መናፍስቱ ወጥተው አሳማዎቹ ውስጥ ገቡ፤ ወደ 2,000 የሚጠጉ አሳማዎችም ከገደሉ አፋፍ* እየተንደረደሩ በመውረድ ባሕሩ ውስጥ ሰጠሙ። 14  የአሳማዎቹ እረኞች ግን ሸሽተው በመሄድ ወሬውን በከተማውና በገጠሩ አዳረሱ፤ ሰዎችም የሆነውን ነገር ለማየት መጡ።+ 15  ወደ ኢየሱስም መጥተው ጋኔን ያደረበትን ይኸውም ቀደም ሲል ሌጌዎን የነበረበትን ሰው ልብስ ለብሶና አእምሮው ተመልሶለት ተቀምጦ አዩት፤ በዚህ ጊዜ ፍርሃት አደረባቸው። 16  የተፈጸመውንም ነገር ያዩ ሰዎች አጋንንት አድረውበት የነበረው ሰው እንዴት እንዲህ ሊሆን እንደቻለና በአሳማዎቹ ላይ የሆነውን ነገር አወሩላቸው። 17  በመሆኑም አካባቢያቸውን ለቆ እንዲሄድ ኢየሱስን ይማጸኑት ጀመር።+ 18  ኢየሱስ ወደ ጀልባው በመውጣት ላይ ሳለ ጋኔን አድሮበት የነበረው ሰው አብሮት ይሄድ ዘንድ ተማጸነው።+ 19  ኢየሱስ ግን አልፈቀደለትም፤ ከዚህ ይልቅ “ወደ ቤት ሄደህ ይሖዋ * ያደረገልህን ነገር ሁሉና ያሳየህን ምሕረት ለዘመዶችህ ንገራቸው” አለው። 20  ሰውየውም ሄዶ ኢየሱስ ያደረገለትን ነገር በሙሉ በዲካፖሊስ* ያውጅ ጀመር፤ ሕዝቡም ሁሉ ተደነቁ። 21  ኢየሱስ በጀልባ ዳግመኛ ወደ ባሕሩ ማዶ ከተሻገረ በኋላ እጅግ ብዙ ሕዝብ ወደ እሱ ተሰበሰበ፤ እሱም በባሕሩ አጠገብ ነበር።+ 22  በዚህ ጊዜ ከምኩራብ አለቆች አንዱ የሆነ ኢያኢሮስ የሚባል ሰው ወደዚያ መጣ፤ ኢየሱስንም ባየው ጊዜ እግሩ ላይ ወደቀ።+ 23  ከዚያም “ትንሿ ልጄ በጠና ታምማለች።* እንድትድንና በሕይወት እንድትኖር፣ እባክህ መጥተህ እጅህን ጫንባት”+ በማለት ደጋግሞ ተማጸነው። 24  ኢየሱስም አብሮት ሄደ፤ እጅግ ብዙ ሕዝብም ተከትሎት እየተጋፋው ይሄድ ነበር። 25  በዚያም፣ ለ12 ዓመት ደም ሲፈሳት+ የኖረች አንዲት ሴት ነበረች።+ 26  ይህች ሴት በርካታ ሐኪሞች ጋር የሄደች ሲሆን ሕክምናው ለብዙ ሥቃይ ዳርጓት ነበር፤ ያላትን ጥሪት ሁሉ ብትጨርስም ሕመሙ ባሰባት እንጂ አልተሻላትም። 27  ስለ ኢየሱስ የተወራውን በሰማች ጊዜ በሰዎች መካከል ከኋላው መጥታ ልብሱን ነካች፤+ 28  ምክንያቱም “ልብሱን ብቻ እንኳ ብነካ እድናለሁ” ብላ ታስብ ነበር።+ 29  ወዲያውም ይፈሳት የነበረው ደም ቆመ፤ ያሠቃያት ከነበረው ሕመም እንደተፈወሰችም ታወቃት። 30  ወዲያውኑ ኢየሱስ ኃይል ከእሱ እንደወጣ ታወቀው፤+ በመሆኑም ወደ ሕዝቡ በመዞር “ልብሴን የነካው ማን ነው?” ሲል ጠየቀ።+ 31  ደቀ መዛሙርቱ ግን “ሕዝቡ እንዲህ ሲጋፋህ እያየህ ‘የነካኝ ማን ነው?’ እንዴት ትላለህ?” አሉት። 32  ይሁንና ኢየሱስ ይህን ያደረገው ማን እንደሆነ ለማየት ዙሪያውን ተመለከተ። 33  ሴትየዋ በእሷ ላይ የተፈጸመውን ነገር ስላወቀች በፍርሃት እየተንቀጠቀጠች መጥታ በፊቱ ተደፋች፤ ከዚያም ምንም ሳታስቀር እውነቱን ነገረችው። 34  እሱም “ልጄ ሆይ፣ እምነትሽ አድኖሻል። በሰላም ሂጂ፤+ ከሚያሠቃይ ሕመምሽም ተፈወሽ” አላት።+ 35  ገና እየተናገረ ሳለ ከምኩራብ አለቃው ቤት የመጡ ሰዎች “ልጅህ ሞታለች! ከዚህ በኋላ መምህሩን ለምን ታስቸግረዋለህ?” አሉት።+ 36  ኢየሱስ ግን የተናገሩትን ሰምቶ የምኩራብ አለቃውን “አትፍራ፤ ብቻ እመን” አለው።+ 37  ከዚህ በኋላ ከጴጥሮስ፣ ከያዕቆብና ከያዕቆብ ወንድም ከዮሐንስ በስተቀር ማንም እንዲከተለው አልፈቀደም።+ 38  ወደ ምኩራብ አለቃው ቤት በደረሱም ጊዜ ትርምሱን እንዲሁም የሚያለቅሱትንና ዋይ ዋይ የሚሉትን ሰዎች ተመለከተ።+ 39  ወደ ውስጥ ከገባም በኋላ “የምታለቅሱትና የምትንጫጩት ለምንድን ነው? ልጅቷ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” አላቸው።+ 40  በዚህ ጊዜ በማፌዝ ይስቁበት ጀመር። እሱ ግን ሁሉንም ወደ ውጭ ካስወጣ በኋላ የልጅቷን አባትና እናት እንዲሁም ከእሱ ጋር የነበሩትን አስከትሎ ልጅቷ ወዳለችበት ገባ። 41  ከዚያም የልጅቷን እጅ ይዞ “ጣሊታ ቁሚ” አላት፤ ትርጉሙም “አንቺ ልጅ፣ ተነሽ!” ማለት ነው።+ 42  ልጅቷም ወዲያው ተነስታ መራመድ ጀመረች። (ዕድሜዋ 12 ዓመት ነበር።) ወዲያውም እጅግ ከመደሰታቸው የተነሳ የሚሆኑት ጠፋቸው። 43  እሱ ግን ይህን ለማንም እንዳይናገሩ ደጋግሞ አስጠነቀቃቸው፤*+ ለልጅቷም የሚበላ ነገር እንዲሰጧት ነገራቸው።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ማቴ 26:53 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
ወይም “ገደላማ ከሆነው የባሕሩ ዳርቻ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “አሥሩ ከተሞች በሚገኙበት ክልል።”
ወይም “ልትሞት ተቃርባለች።”
ወይም “አጥብቆ አዘዛቸው።”