የማቴዎስ ወንጌል 14:1-36
14 በዚያን ጊዜ የአውራጃ ገዢ* የነበረው ሄሮድስ ስለ ኢየሱስ ሲሰማ+
2 አገልጋዮቹን “ይህ መጥምቁ ዮሐንስ ነው። ከሞት ተነስቷል ማለት ነው፤ እነዚህን ተአምራት መፈጸም የቻለውም ለዚህ ነው” አላቸው።+
3 ሄሮድስ* የወንድሙ የፊልጶስ ሚስት በሆነችው በሄሮድያዳ ምክንያት ዮሐንስን ይዞ በሰንሰለት በማሰር ወህኒ አስገብቶት ነበር።+
4 ዮሐንስ ሄሮድስን “እሷን እንድታገባ ሕግ አይፈቅድልህም” ይለው ነበር።+
5 ሄሮድስ ሊገድለው ይፈልግ የነበረ ቢሆንም ሕዝቡ እንደ ነቢይ ይመለከተው ስለነበር ሕዝቡን ፈራ።+
6 ሆኖም የሄሮድስ ልደት+ በተከበረበት ዕለት የሄሮድያዳ ልጅ በግብዣው ላይ በመጨፈር ሄሮድስን እጅግ ደስ አሰኘችው፤+
7 በመሆኑም የጠየቀችውን ሁሉ ሊሰጣት በመሐላ ቃል ገባላት።
8 ከዚያም እናቷ በሰጠቻት ምክር መሠረት “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ በዚህ ሳህን ስጠኝ” አለችው።+
9 ንጉሡ ቢያዝንም ስለ መሐላዎቹና አብረውት ይበሉ ስለነበሩት ሲል የዮሐንስ ራስ እንዲሰጣት አዘዘ።
10 ሰው ልኮም የዮሐንስን ራስ በወህኒ ቤት አስቆረጠ።
11 ራሱን በሳህን አምጥተው ለልጅቷ ሰጧት፤ እሷም ለእናቷ ሰጠቻት።
12 በኋላም የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት መጡና አስከሬኑን ወስደው ቀበሩት፤ ከዚያም መጥተው ለኢየሱስ ነገሩት።
13 ኢየሱስ ይህን ሲሰማ ብቻውን ለመሆን በጀልባ ተሳፍሮ ገለል ወዳለ ስፍራ ሄደ። ሕዝቡ ግን መሄዱን ሰምተው ከየከተማው እየወጡ በእግር ተከተሉት።+
14 ኢየሱስ ወደ ባሕሩ ዳርቻ ሲመጣ እጅግ ብዙ ሕዝብ ተመለከተና በጣም አዘነላቸው፤+ በመካከላቸው የነበሩትንም ሕመምተኞች ፈወሰ።+
15 በመሸ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እሱ ቀርበው “ቦታው ገለል ያለ ነው፤ ሰዓቱ ደግሞ ገፍቷል፤ ስለዚህ ሕዝቡ ወደ መንደሮቹ ሄደው ምግብ እንዲገዙ አሰናብታቸው” አሉት።+
16 ይሁን እንጂ ኢየሱስ “መሄድ አያስፈልጋቸውም፤ እናንተ የሚበሉት ነገር ስጧቸው” አላቸው።
17 እነሱም “ከአምስት ዳቦና ከሁለት ዓሣ በስተቀር እዚህ ምንም ነገር የለንም” አሉት።
18 እሱም “ያለውን ወደ እኔ አምጡት” አላቸው።
19 ሕዝቡንም ሣሩ ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ። ከዚያም አምስቱን ዳቦና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ ቀና በማለት ባረከ፤+ ዳቦውን ከቆረሰ በኋላም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ እነሱ ደግሞ ለሕዝቡ ሰጡ።
20 ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ከዚያም የተረፈውን ቁርስራሽ ሰበሰቡ፤ ቁርስራሹም 12 ቅርጫት ሙሉ ሆነ።+
21 የበሉትም ከሴቶችና ከትናንሽ ልጆች ሌላ 5,000 ወንዶች ነበሩ።+
22 ወዲያውም፣ እሱ ሕዝቡን እያሰናበተ ሳለ ደቀ መዛሙርቱን ጀልባ ተሳፍረው ቀድመውት ወደ ማዶ እንዲሻገሩ ነገራቸው።+
23 ሕዝቡን ካሰናበተ በኋላ ለመጸለይ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ።+ በመሸም ጊዜ በዚያ ብቻውን ነበር።
24 በዚህ ጊዜ ጀልባው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሜትሮች* ከየብስ ርቆ የነበረ ሲሆን ነፋሱ ወደ እነሱ ይነፍስ ስለነበር ማዕበሉ በጣም አስቸገራቸው።
25 ሆኖም ኢየሱስ በአራተኛው ክፍለ ሌሊት* በባሕሩ ላይ እየተራመደ ወደ እነሱ መጣ።
26 ደቀ መዛሙርቱ በባሕሩ ላይ ሲራመድ ባዩት ጊዜ ደንግጠው “ምትሃት ነው!” አሉ። በፍርሃት ተውጠውም ጮኹ።
27 ሆኖም ኢየሱስ ወዲያውኑ “አይዟችሁ! እኔ ነኝ፤ አትፍሩ” አላቸው።+
28 ጴጥሮስም መልሶ “ጌታ ሆይ፣ አንተ ከሆንክ በውኃው ላይ እየተራመድኩ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ” አለው።
29 እሱም “ና!” አለው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ከጀልባው ላይ ወርዶ በውኃው ላይ እየተራመደ ወደ ኢየሱስ አመራ።
30 ሆኖም አውሎ ነፋሱን ሲያይ ፈራ። መስጠም ሲጀምርም “ጌታ ሆይ፣ አድነኝ!” ብሎ ጮኸ።
31 ወዲያው ኢየሱስ እጁን ዘርግቶ ያዘውና “አንተ እምነት የጎደለህ! ለምን ተጠራጠርክ?” አለው።+
32 ጀልባው ላይ ከወጡ በኋላ አውሎ ነፋሱ ጸጥ አለ።
33 ከዚያም በጀልባው ውስጥ ያሉት “አንተ በእርግጥ የአምላክ ልጅ ነህ” ብለው ሰገዱለት።*
34 ባሕሩንም ተሻግረው ጌንሴሬጥ+ ወደተባለ ቦታ ደረሱ።
35 በዚያ የሚኖሩ ሰዎች ኢየሱስ መሆኑን ሲያውቁ በዙሪያው ወዳለው አካባቢ ሁሉ መልእክት ላኩ፤ ሰዎችም የታመሙትን ሁሉ ወደ እሱ አመጡ።
36 የልብሱን ዘርፍ ብቻ እንኳ ለመንካት ይማጸኑት ነበር፤+ የነኩትም ሁሉ ሙሉ በሙሉ ተፈወሱ።
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ቃል በቃል “የአራተኛው ክፍል ገዢ።”
^ ሄሮድስ አንቲጳስን ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ቃል በቃል “ብዙ ስታዲዮን።” አንድ ስታዲዮን 185 ሜትር ነው።
^ ከሌሊቱ 9 ሰዓት ገደማ አንስቶ 12 ሰዓት ገደማ ላይ ፀሐይ እስከምትወጣበት ጊዜ ድረስ ያለውን ሰዓት ያመለክታል።
^ ወይም “እጅ ነሱት።”