የማቴዎስ ወንጌል 24:1-51

  • የክርስቶስ መገኘት ምልክት (1-51)

    • ጦርነት፣ የምግብ እጥረት፣ የምድር ነውጥ (7)

    • ምሥራቹ ይሰበካል (14)

    • “ታላቅ መከራ” (21, 22)

    • የሰው ልጅ ምልክት (30)

    • የበለስ ዛፍ (32-34)

    • እንደ ኖኅ ዘመን (37-39)

    • “ነቅታችሁ ጠብቁ” (42-44)

    • ታማኙ ባሪያና ክፉው ባሪያ (45-51)

24  ኢየሱስ ከቤተ መቅደሱ ወጥቶ እየሄደ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ የቤተ መቅደሱን ግንቦች ሊያሳዩት ወደ እሱ ቀረቡ። 2  እሱም መልሶ “ይህን ሁሉ ታያላችሁ? እውነት እላችኋለሁ፣ ይህ ሁሉ ሳይፈርስ እንዲህ ድንጋይ በድንጋይ ላይ እንደተነባበረ ከቶ አይኖርም” አላቸው።+ 3  በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እሱ መጥተው “እስቲ ንገረን፣ እነዚህ ነገሮች የሚፈጸሙት መቼ ነው? የመገኘትህና*+ የዚህ ሥርዓት* መደምደሚያ+ ምልክትስ ምንድን ነው?” አሉት። 4  ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ማንም እንዳያሳስታችሁ ተጠንቀቁ፤+ 5  ብዙዎች ‘እኔ ክርስቶስ ነኝ’ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያሳስታሉ።+ 6  ጦርነትና የጦርነት ወሬ ትሰማላችሁ። በዚህ ጊዜ እንዳትደናገጡ ተጠንቀቁ፤ ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች መፈጸማቸው የግድ ነው፤ ሆኖም ፍጻሜው ገና ነው።+ 7  “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳልና፤+ በተለያየ ስፍራ የምግብ እጥረትና+ የምድር ነውጥ ይከሰታል።+ 8  እነዚህ ነገሮች ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው። 9  “በዚያን ጊዜ ሰዎች ለመከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል፣+ ይገድሏችኋል+ እንዲሁም በስሜ ምክንያት በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ።+ 10  በተጨማሪም ብዙዎች ይሰናከላሉ፤ አንዱ ሌላውን አሳልፎ ይሰጣል፤ እርስ በርሳቸውም ይጠላላሉ። 11  ብዙ ሐሰተኛ ነቢያት ይነሳሉ፤ ብዙዎችንም ያሳስታሉ፤+ 12  ክፋት* እየበዛ ስለሚሄድ የብዙዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል። 13  እስከ መጨረሻው የጸና* ግን ይድናል።+ 14  ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤+ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል። 15  “ስለዚህ ነቢዩ ዳንኤል በተናገረው መሠረት ጥፋት የሚያመጣው ‘ርኩስ ነገር’ በተቀደሰ ስፍራ ቆሞ ስታዩ+ አንባቢው ያስተውል፤ 16  በዚህ ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ።+ 17  በጣሪያ* ላይ ያለ ሰው ዕቃውን ከቤቱ ለመውሰድ አይውረድ፤ 18  በእርሻም ያለ መደረቢያውን ለመውሰድ አይመለስ። 19  በእነዚያ ቀናት ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው! 20  ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት* ቀን እንዳይሆን ዘወትር ጸልዩ፤ 21  ምክንያቱም በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ አንስቶ እስካሁን ድረስ ሆኖ የማያውቅ ዳግመኛም የማይሆን+ ታላቅ መከራ+ ይከሰታል። 22  እንዲያውም ቀኖቹ ባያጥሩ ኖሮ ሥጋ ሁሉ ባልዳነ ነበር፤ ሆኖም ለተመረጡት ሲባል ቀኖቹ ያጥራሉ።+ 23  “በዚያን ጊዜ ማንም ‘እነሆ፣ ክርስቶስ ይኸውላችሁ’+ ወይም ‘ያውላችሁ’ ቢላችሁ አትመኑ።+ 24  ምክንያቱም ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት ይነሳሉ፤+ ቢቻላቸው የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክቶችና አስደናቂ ነገሮች ያደርጋሉ።+ 25  እንግዲህ አስቀድሜ አስጠንቅቄያችኋለሁ። 26  ስለዚህ ሰዎች ‘እነሆ፣ በምድረ በዳ ነው’ ቢሏችሁ ወደዚያ አትውጡ፤ ‘እነሆ፣ ቤት ውስጥ በውስጠኛው ክፍል ይገኛል’ ቢሏችሁ አትመኑ።+ 27  መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚያበራ ሁሉ የሰው ልጅ መገኘትም* እንዲሁ ይሆናል።+ 28  በድን ባለበት ሁሉ ንስሮች ይሰበሰባሉ።+ 29  “በእነዚያ ቀናት ከሚኖረው መከራ በኋላ ወዲያውኑ ፀሐይ ትጨልማለች፤+ ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም፤ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ የሰማያት ኃይላትም ይናወጣሉ።+ 30  ከዚያም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፤ የምድር ወገኖችም ሁሉ በሐዘን ደረታቸውን ይደቃሉ፤+ የሰው ልጅም+ በኃይልና በታላቅ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል።+ 31  እሱም መላእክቱን በታላቅ የመለከት ድምፅ ይልካል፤ እነሱም ከአራቱ ነፋሳት፣* ከአንዱ የሰማይ ዳርቻ እስከ ሌላው የሰማይ ዳርቻ ለእሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ።+ 32  “እንግዲያው ይህን ምሳሌ ከበለስ ዛፍ ተማሩ፦ ቅርንጫፎቿ ሲለመልሙና ቅጠሎቿ ሲያቆጠቁጡ በጋ* እንደቀረበ ታውቃላችሁ።+ 33  በተመሳሳይ እናንተም እነዚህን ሁሉ ነገሮች ስታዩ የሰው ልጅ ደጃፍ ላይ እንደደረሰ እርግጠኞች ሁኑ።+ 34  እውነት እላችኋለሁ፣ እነዚህ ነገሮች ሁሉ እስኪፈጸሙ ድረስ ይህ ትውልድ ፈጽሞ አያልፍም። 35  ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን ፈጽሞ አያልፍም።+ 36  “ስለዚያ ቀንና ሰዓት ከአብ ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ሆኑ ወልድ፣+ ማንም አያውቅም።+ 37  በኖኅ ዘመን እንደነበረው ሁሉ+ የሰው ልጅ መገኘትም* እንደዚሁ ይሆናል።+ 38  ከጥፋት ውኃ በፊት በነበረው ዘመን ኖኅ ወደ መርከቡ እስከገባበት ቀን+ ድረስ ሰዎች ይበሉና ይጠጡ እንዲሁም ወንዶች ያገቡ፣ ሴቶችም ይዳሩ ነበር፤ 39  የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉንም ጠራርጎ እስከወሰዳቸው ጊዜ ድረስ ምንም አላስተዋሉም፤+ የሰው ልጅ መገኘትም እንደዚሁ ይሆናል። 40  በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በእርሻ ቦታ ይሠራሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው እዚያው ይተዋል። 41  ሁለት ሴቶች በወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዷ ትወሰዳለች፤ ሌላዋ እዚያው ትተዋለች።+ 42  ስለዚህ ጌታችሁ በየትኛው ቀን እንደሚመጣ ስለማታውቁ ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ።+ 43  “ነገር ግን ይህን እወቁ፦ አንድ ሰው ሌባ+ በየትኛው ክፍለ ሌሊት* እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ ነቅቶ በጠበቀና ቤቱ እንዳይደፈር በተከላከለ ነበር።+ 44  ስለዚህ እናንተም የሰው ልጅ ባላሰባችሁት ሰዓት ስለሚመጣ ዝግጁ ሁኑ።+ 45  “በተገቢው ጊዜ ምግባቸውን እንዲሰጣቸው ጌታው በቤተሰቦቹ ላይ የሾመው ታማኝና ልባም* ባሪያ በእርግጥ ማን ነው?+ 46  ጌታው በሚመጣበት ጊዜ እንዲህ ሲያደርግ ካገኘው ያ ባሪያ ደስተኛ ነው!+ 47  እውነት እላችኋለሁ፣ ጌታው በንብረቱ ሁሉ ላይ ይሾመዋል። 48  “ነገር ግን ያ ክፉ ባሪያ በልቡ ‘ጌታዬ ይዘገያል’ ብሎ ቢያስብ+ 49  ደግሞም ባልንጀሮቹ የሆኑትን ባሪያዎች መደብደብ ቢጀምር እንዲሁም ከሰካራሞች ጋር ቢበላና ቢጠጣ፣ 50  የዚያ ባሪያ ጌታ ባልጠበቀው ቀንና ባላሰበው ሰዓት ይመጣል፤+ 51  ከባድ ቅጣት ይቀጣዋል፤* ዕጣውንም ከግብዞች ጋር ያደርገዋል። በዚያም ያለቅሳል፤ ጥርሱንም ያፋጫል።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ቃል በቃል “ሕገ ወጥነት።”
ወይም “የሚጸና።”
በዚያ ወቅት የሚሠሩት አብዛኞቹ ቤቶች ጠፍጣፋ ጣሪያ የነበራቸው ሲሆን ሰዎች በጣሪያው ላይ የተለያዩ ሥራዎችን ያከናውኑ ነበር።
ሥራ 1:12 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
ከሰሜን፣ ከምሥራቅ፣ ከደቡብና ከምዕራብ አቅጣጫ የሚነፍሱ ነፋሳትን ያመለክታል።
በጳለስጢና ምድር ዕፀዋት የሚለመልሙት በበጋ ነው።
ወይም “ሌሊት በስንት ሰዓት።”
ወይም “ጥበበኛ።”
ወይም “ለሁለት ይቆርጠዋል።”