የማቴዎስ ወንጌል 25:1-46

  • የክርስቶስ መገኘት ምልክት (1-46)

    • የአሥሩ ደናግል ምሳሌ (1-13)

    • የታላንቱ ምሳሌ (14-30)

    • በጎችና ፍየሎች (31-46)

25  “በተጨማሪም መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን+ ይዘው ሙሽራውን+ ሊቀበሉ ከወጡ አሥር ደናግል ጋር ሊመሳሰል ይችላል። 2  አምስቱ ሞኞች፣ አምስቱ ደግሞ ልባሞች* ነበሩ።+ 3  ሞኞቹ መብራታቸውን ቢይዙም መጠባበቂያ ዘይት አልያዙም ነበር፤ 4  ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በዕቃ ዘይት ይዘው ነበር። 5  ሙሽራው በዘገየ ጊዜ ሁሉም እንቅልፍ ተጫጫናቸውና ተኙ። 6  እኩለ ሌሊት ላይ ‘ሙሽራው እየመጣ ነው፤ ወጥታችሁ ተቀበሉት!’ የሚል ጫጫታ ተሰማ። 7  በዚህ ጊዜ ደናግሉ ሁሉ ተነስተው መብራቶቻቸውን አዘጋጁ።+ 8  ሞኞቹ ደናግል ልባሞቹን ‘መብራታችን ሊጠፋብን ስለሆነ ከያዛችሁት ዘይት ላይ ስጡን’ አሏቸው። 9  ልባሞቹም ‘ለእናንተ ከሰጠናችሁ ለእኛም ለእናንተም ላይበቃን ስለሚችል ወደ ሻጮች ሄዳችሁ ለራሳችሁ የተወሰነ ዘይት ብትገዙ ይሻላል’ ብለው መለሱላቸው። 10  ሊገዙ ሄደው ሳሉም ሙሽራው ደረሰ። ተዘጋጅተው የነበሩት ደናግልም ወደ ሠርጉ ድግስ ገቡ፤+ በሩም ተዘጋ። 11  በኋላም የቀሩት ደናግል መጥተው ‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ ክፈትልን!’ አሉ።+ 12  እሱ ግን ‘እውነቴን ነው የምላችሁ፣ አላውቃችሁም’ አላቸው። 13  “እንግዲህ ቀኑንም ሆነ ሰዓቱን ስለማታውቁ+ ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ።+ 14  “ደግሞም መንግሥተ ሰማያት ባሪያዎቹን ጠርቶ ንብረቱን ለእነሱ በአደራ በመስጠት ወደ ሌላ አገር ለመሄድ ከተነሳ ሰው ጋር ይመሳሰላል።+ 15  ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው፣ ለአንዱ አምስት ታላንት፣* ለሌላው ሁለት፣ ለሌላው ደግሞ አንድ በመስጠት ወደ ሌላ አገር ሄደ። 16  አምስት ታላንት የተቀበለው ሰው ወዲያው ሄዶ ነገደበትና ሌላ አምስት ታላንት አተረፈ። 17  በተመሳሳይም ሁለት ታላንት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ። 18  አንድ ታላንት ብቻ የተቀበለው ባሪያ ግን ሄዶ መሬት ቆፈረና ጌታው የሰጠውን ገንዘብ* ቀበረ። 19  “ከረጅም ጊዜ በኋላ የእነዚያ ባሪያዎች ጌታ መጥቶ ሒሳቡን ከባሪያዎቹ ጋር ተሳሰበ።+ 20  ስለዚህ አምስት ታላንት የተቀበለው ባሪያ ሌላ አምስት ተጨማሪ ታላንት ይዞ በመቅረብ ‘ጌታ ሆይ፣ አምስት ታላንት ሰጥተኸኝ ነበር፤ ይኸው ሌላ አምስት ታላንት አተረፍኩ’ አለ።+ 21  ጌታውም ‘ጎበዝ፣ አንተ ጥሩና ታማኝ ባሪያ! በጥቂት ነገሮች ታማኝ ሆነህ ተገኝተሃል። ስለዚህ በብዙ ነገሮች ላይ እሾምሃለሁ።+ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው።+ 22  ቀጥሎም ሁለት ታላንት የተቀበለው ባሪያ ቀርቦ ‘ጌታ ሆይ፣ ሁለት ታላንት ሰጥተኸኝ ነበር፤ ይኸው ሌላ ሁለት ታላንት አተረፍኩ’ አለ።+ 23  ጌታውም ‘ጎበዝ፣ አንተ ጥሩና ታማኝ ባሪያ! በጥቂት ነገሮች ታማኝ ሆነህ ተገኝተሃል። ስለዚህ በብዙ ነገሮች ላይ እሾምሃለሁ። ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው። 24  “በመጨረሻም አንድ ታላንት የተቀበለው ባሪያ ቀርቦ እንዲህ አለው፦ ‘ጌታ ሆይ፣ አንተ ያልዘራኸውን የምታጭድ፣ ያልደከምክበትንም እህል የምትሰበስብ ኃይለኛ ሰው መሆንህን አውቃለሁ።+ 25  ስለዚህ ፈራሁ፤ ሄጄም ታላንትህን መሬት ውስጥ ቀበርኩት። ገንዘብህ ይኸውልህ።’ 26  ጌታውም መልሶ እንዲህ አለው፦ ‘አንተ ክፉና ሰነፍ ባሪያ፣ ያልዘራሁትን የማጭድ፣ ያልደከምኩበትንም እህል የምሰበስብ መሆኔን ታውቅ ኖሯል? 27  ይህን ካወቅክ ገንዘቤን፣* ገንዘብ ለዋጮች ጋ ማስቀመጥ ነበረብህ፤ እኔም ስመጣ ገንዘቤን ከነወለዱ እወስደው ነበር። 28  “‘ስለዚህ ታላንቱን ውሰዱበትና አሥር ታላንት ላለው ስጡት።+ 29  ምክንያቱም ላለው ሁሉ ይጨመርለታል፤ ደግሞም ይትረፈረፍለታል። የሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።+ 30  ይህን የማይረባ ባሪያ ውጭ ወዳለው ጨለማ ጣሉት። በዚያም ያለቅሳል፤ ጥርሱንም ያፋጫል።’ 31  “የሰው ልጅ+ ከመላእክቱ ሁሉ ጋር+ በክብሩ ሲመጣ በክብራማ ዙፋኑ ላይ ይቀመጣል። 32  ሕዝቦች ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛ በጎቹን ከፍየሎቹ እንደሚለይ ሁሉ እሱም ሰዎችን አንዱን ከሌላው ይለያል። 33  በጎቹን+ በቀኙ፣ ፍየሎቹን ግን በግራው ያደርጋቸዋል።+ 34  “ከዚያም ንጉሡ በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል፦ ‘እናንተ አባቴ የባረካችሁ ኑ፤ ዓለም ከተመሠረተበት* ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ። 35  ምክንያቱም ተርቤ አብልታችሁኛል፤ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛል። እንግዳ ሆኜ አስተናግዳችሁኛል፤+ 36  ታርዤ* አልብሳችሁኛል።+ ታምሜ አስታማችሁኛል። ታስሬ ጠይቃችሁኛል።’+ 37  ከዚያም ጻድቃኑ መልሰው እንዲህ ይሉታል፦ ‘ጌታ ሆይ፣ ተርበህ አይተን መቼ አበላንህ? ተጠምተህ አይተንስ መቼ አጠጣንህ?+ 38  እንግዳ ሆነህ አይተን መቼ አስተናገድንህ? ወይስ ታርዘህ አይተን መቼ አለበስንህ? 39  ታመህ ወይም ታስረህ አይተን መቼ ጠየቅንህ?’ 40  ንጉሡም መልሶ ‘እውነት እላችኋለሁ፣ ከሁሉ ከሚያንሱት ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ ያደረጋችሁት ሁሉ ለእኔ እንዳደረጋችሁት ይቆጠራል’ ይላቸዋል።+ 41  “ከዚያም በግራው ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል፦ ‘እናንተ የተረገማችሁ፣ ከእኔ ራቁ፤+ ለዲያብሎስና ለመላእክቱ ወደተዘጋጀው+ ዘላለማዊ እሳት+ ሂዱ። 42  ምክንያቱም ተርቤ አላበላችሁኝም፤ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝም። 43  እንግዳ ሆኜ አላስተናገዳችሁኝም፤ ታርዤ አላለበሳችሁኝም፤ ታምሜና ታስሬ አልጠየቃችሁኝም።’ 44  እነሱም መልሰው ‘ጌታ ሆይ፣ ተርበህ ወይስ ተጠምተህ ወይስ እንግዳ ሆነህ ወይስ ታርዘህ ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ መቼ አይተን ሳናገለግልህ ቀረን?’ ይሉታል። 45  እሱም መልሶ ‘እውነት እላችኋለሁ፣ ከሁሉ ከሚያንሱት ከእነዚህ ለአንዱ ይህን ሳታደርጉ መቅረታችሁ ለእኔ እንዳላደረጋችሁት ይቆጠራል’ ይላቸዋል።+ 46  እነዚህ ወደ ዘላለም ጥፋት*+ ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት+ ይሄዳሉ።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ጥበበኞች።”
የግሪኩ ታላንት 20.4 ኪሎ ግራም ነው። ለ14ን ተመልከት።
ቃል በቃል “ብር።” ብር ከተባለው ማዕድን የተሠራ ገንዘብ።
ቃል በቃል “ብሬን።”
ይህ አባባል የአዳምንና የሔዋንን ዘሮች ያመለክታል።
በቂ ልብስ አለመልበስን ያመለክታል።
ቃል በቃል “መቆረጥ፤ መገረዝ።” ከሕይወት መቆረጥን ያመለክታል።