የማቴዎስ ወንጌል 7:1-29

  • የተራራው ስብከት (1-27)

    • “በሌሎች ላይ አትፍረዱ” (1-6)

    • ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ፈልጉ፣ አንኳኩ (7-11)

    • ወርቃማው ሕግ (12)

    • ጠባቡ በር (13, 14)

    • “ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ” (15-23)

    • በዓለት ላይና በአሸዋ ላይ የተሠራ ቤት (24-27)

  • ሕዝቡ በኢየሱስ ትምህርት ተደነቁ (28, 29)

7  “እንዳይፈረድባችሁ በሌሎች ላይ አትፍረዱ፤*+ 2  በምትፈርዱት ፍርድ ይፈረድባችኋል፤+ በምትሰፍሩበት መስፈሪያም ይሰፍሩላችኋል።+ 3  ታዲያ በራስህ ዓይን ውስጥ ያለውን ግንድ ትተህ በወንድምህ ዓይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ ለምን ታያለህ?+ 4  ወይም በራስህ ዓይን ውስጥ ግንድ እያለ ወንድምህን ‘ዓይንህ ውስጥ ያለውን ጉድፍ ላውጣልህ’ እንዴት ትለዋለህ? 5  አንተ ግብዝ! መጀመሪያ በራስህ ዓይን ውስጥ ያለውን ግንድ አውጣ፤ ከዚያም በወንድምህ ዓይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ ለማውጣት አጥርተህ ማየት ትችላለህ። 6  “ቅዱስ የሆነውን ነገር ለውሾች አትስጡ፤ ዕንቁዎቻችሁንም በአሳማ ፊት አትጣሉ።+ አለዚያ ዕንቁዎቹን በእግራቸው ይረጋግጧቸዋል፤ ተመልሰውም ይጎዷችኋል። 7  “ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤+ ሳታቋርጡ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ ደጋግማችሁ አንኳኩ፣ ይከፈትላችኋል።+ 8  የሚለምን ሁሉ ይሰጠዋልና፤+ የሚፈልግ ሁሉ ያገኛል፤ ለሚያንኳኳም ሁሉ ይከፈትለታል። 9  ደግሞስ ከእናንተ መካከል ልጁ ዳቦ ቢለምነው ድንጋይ የሚሰጠው አለ? 10  ወይስ ዓሣ ቢለምነው እባብ ይሰጠዋል? 11  ታዲያ እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳለ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ በሰማያት ያለው አባታችሁማ ለሚለምኑት+ መልካም ነገር እንዴት አብልጦ አይሰጣቸው!+ 12  “እንግዲህ ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም አድርጉላቸው።+ ሕጉም ሆነ የነቢያት ቃል የሚሉት ይህንኑ ነው።+ 13  “በጠባቡ በር ግቡ፤+ ምክንያቱም ወደ ጥፋት የሚወስደው በር ትልቅ፣ መንገዱም ሰፊ ነው፤ በዚያ የሚሄዱም ብዙዎች ናቸው፤ 14  ወደ ሕይወት የሚወስደው በር ግን ጠባብ፣ መንገዱም ቀጭን ነው፤ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።+ 15  “በውስጣቸው ነጣቂ ተኩላዎች+ ሆነው ሳሉ የበግ ለምድ ለብሰው+ ወደ እናንተ ከሚመጡ ሐሰተኛ ነቢያት ተጠንቀቁ።+ 16  ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። ሰዎች ከእሾህ ወይን፣ ከአሜኬላስ በለስ ይለቅማሉ?+ 17  በተመሳሳይም ጥሩ ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያፈራል፤ የበሰበሰ ዛፍ ሁሉ ግን መጥፎ ፍሬ ያፈራል።+ 18  ጥሩ ዛፍ መጥፎ ፍሬ ሊያፈራ አይችልም፤ የበሰበሰም ዛፍ መልካም ፍሬ ሊያፈራ አይችልም።+ 19  መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ተቆርጦ ወደ እሳት ይጣላል።+ 20  በመሆኑም እነዚህን ሰዎች ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ።+ 21  “‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማያት አይገባም፤ ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚገባው በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ብቻ ነው።+ 22  በዚያ ቀን ብዙዎች እንዲህ ይሉኛል፦ ‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣+ በስምህ ትንቢት አልተናገርንም? በስምህ አጋንንትን አላወጣንም? በስምህስ ብዙ ተአምራት አላደረግንም?’+ 23  እኔም በዚያ ጊዜ ‘ቀድሞውንም አላውቃችሁም! እናንተ ዓመፀኞች፣ ከእኔ ራቁ!’ እላቸዋለሁ።+ 24  “ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ በተግባር የሚያውል ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራን አስተዋይ ሰው ይመስላል።+ 25  ዶፍ ወረደ፤ ጎርፍ ጎረፈ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ቤቱንም በኃይል መታው፤ ሆኖም ቤቱ በዓለት ላይ ስለተመሠረተ አልተደረመሰም። 26  ይህን ቃሌን ሰምቶ በተግባር የማያውል ሁሉ ግን ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራን ሞኝ ሰው ይመስላል።+ 27  ዶፍ ወረደ፤ ጎርፍ ጎረፈ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ቤቱንም በኃይል መታው፤+ ቤቱም ተደረመሰ፤ እንዳልነበረም ሆነ።” 28  ኢየሱስ ንግግሩን በጨረሰ ጊዜ ሕዝቡ በትምህርት አሰጣጡ እጅግ ተደነቁ፤+ 29  የሚያስተምራቸው እንደ እነሱ ጸሐፍት ሳይሆን እንደ ባለሥልጣን ነበርና።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “መፍረዳችሁን ተዉ።”