ምሳሌ 15:1-33
15 የለዘበ* መልስ ቁጣን ያበርዳል፤+ክፉ* ቃል ግን ቁጣን ያነሳሳል።+
2 የጥበበኞች ምላስ እውቀትን በሚገባ ይጠቀማል፤+የሞኞች አፍ ግን ሞኝነትን ይገልጣል።
3 የይሖዋ ዓይኖች በሁሉም ቦታ ናቸው፤ክፉዎችንም ሆነ ጥሩ ሰዎችን ይመለከታሉ።+
4 የረጋ አንደበት* የሕይወት ዛፍ ነው፤+ጠማማ ንግግር ግን ተስፋ ያስቆርጣል።*
5 ሞኝ የአባቱን ተግሣጽ ይንቃል፤+ብልህ ግን እርማትን ይቀበላል።+
6 በጻድቅ ሰው ቤት ብዙ ሀብት አለ፤የክፉ ሰው ምርት* ግን ችግር ያስከትልበታል።+
7 የጥበበኞች ከንፈር እውቀትን ታስፋፋለች፤+የሞኞች ልብ ግን እንዲህ አይደለም።+
8 ይሖዋ የክፉዎችን መሥዋዕት ይጸየፋል፤+የቅኖች ጸሎት ግን ደስ ያሰኘዋል።+
9 ይሖዋ የክፉውን መንገድ ይጸየፋል፤+ጽድቅን የሚከታተለውን ግን ይወደዋል።+
10 ከመንገድ የሚወጣ ሰው፣ ተግሣጽ መጥፎ* ነገር ይመስለዋል፤+ወቀሳን የሚጠላ ሁሉ ግን ይሞታል።+
11 መቃብርና* የጥፋት ቦታ* በይሖዋ ፊት ወለል ብለው ይታያሉ።+
የሰዎች ልብማ በፊቱ ምንኛ የተገለጠ ነው!+
12 ፌዘኛ የሚያርመውን* ሰው አይወድም።+
ጥበበኞችን አያማክርም።+
13 ደስተኛ ልብ ፊትን ያፈካል፤የልብ ሐዘን ግን መንፈስን ይደቁሳል።+
14 አስተዋይ ልብ እውቀትን ይፈልጋል፤+የሞኞች አፍ ግን ቂልነትን ይመገባል።*+
15 ጎስቋላ ሰው ዘመኑ ሁሉ አስከፊ ነው፤+ደስተኛ* ልብ ያለው ሰው ግን ሁልጊዜ ግብዣ ላይ ያለ ያህል ነው።+
16 ከጭንቀት* ጋር ከሚገኝ ብዙ ሀብት ይልቅይሖዋን በመፍራት የሚገኝ ጥቂት ነገር ይሻላል።+
17 ጥላቻ ባለበት የሰባ* ፍሪዳ ከመብላት ይልቅፍቅር ባለበት አትክልት መብላት ይሻላል።+
18 ግልፍተኛ ሰው ጭቅጭቅ ይፈጥራል፤+ቶሎ የማይቆጣ ሰው ግን ጠብን ያበርዳል።+
19 የሰነፍ መንገድ እንደ እሾህ አጥር ነው፤+የቅኖች መንገድ ግን እንደተስተካከለ አውራ ጎዳና ነው።+
20 ጥበበኛ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፤+ሞኝ ግን እናቱን ያቃልላል።+
21 ማስተዋል* የጎደለው ሰው ሞኝነት ያስደስተዋል፤+ጥልቅ ግንዛቤ ያለው ሰው ግን ቀጥተኛውን መንገድ ተከትሎ ይሄዳል።+
22 መመካከር* ከሌለ የታቀደው ነገር ሳይሳካ ይቀራል፤በብዙ አማካሪዎች ግን ይሳካል።+
23 ሰው ትክክለኛውን መልስ በመስጠት* ሐሴት ያደርጋል፤+በትክክለኛው ጊዜ የተነገረ ቃልም ምንኛ መልካም ነው!+
24 ጥልቅ ማስተዋል ያለው ሰው ወደ መቃብር* ከመውረድ ይድን ዘንድየሕይወት መንገድ ወደ ላይ ይመራዋል።+
25 ይሖዋ የትዕቢተኞችን ቤት ያፈርሳል፤+የመበለቲቱን ወሰን ግን ያስከብራል።+
26 ይሖዋ የክፉውን ሰው ሐሳብ ይጸየፋል፤+ያማረ ቃል ግን በፊቱ ንጹሕ ነው።+
27 በማጭበርበር የተገኘ ትርፍ የሚያጋብስ ሰው በቤተሰቡ ላይ ችግር* ያመጣል፤+ጉቦን የሚጠላ ግን በሕይወት ይኖራል።+
28 የጻድቅ ልብ፣ መልስ ከመስጠቱ በፊት ያሰላስላል፤*+የክፉዎች አፍ ግን መጥፎ ነገር ይዘከዝካል።
29 ይሖዋ ከክፉዎች እጅግ የራቀ ነው፤የጻድቃንን ጸሎት ግን ይሰማል።+
30 ብሩህ ዓይን* ልብን ደስ ያሰኛል፤መልካም ዜናም አጥንትን ያበረታል።*+
31 ሕይወት የሚያስገኝ ወቀሳን የሚሰማ፣በጥበበኛ ሰዎች መካከል ይኖራል።+
32 ተግሣጽን ገሸሽ የሚያደርግ ሰው ሁሉ ሕይወቱን* ያቃልላል፤+ወቀሳን የሚሰማ ሁሉ ግን ማስተዋል* ያገኛል።+
33 ይሖዋን መፍራት ጥበብን ያስተምራል፤+ትሕትናም ክብርን ትቀድማለች።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “የሚያቆስል።”
^ ወይም “ደግነት የተሞላበት።”
^ ወይም “ፈዋሽ ምላስ።”
^ ቃል በቃል “መንፈስን ያደቃል።”
^ ወይም “ገቢ።”
^ ወይም “ከባድ።”
^ ወይም “ሲኦልና።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ወይም “አባዶን።”
^ ወይም “የሚወቅሰውን።”
^ ወይም “ይከታተላል።”
^ ወይም “ጥሩ።”
^ ወይም “ከሽብር።”
^ ቃል በቃል “በግርግም የተቀለበ።”
^ ቃል በቃል “ልብ።”
^ ወይም “ልብ ለልብ መነጋገር።”
^ ቃል በቃል “በአፉ መልስ።”
^ ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ወይም “ውርደት።”
^ ወይም “ምን ብሎ እንደሚመልስ በጥሞና ያስባል፤ ከመናገሩ በፊት ያስባል።”
^ ቃል በቃል “ያሰባል።”
^ ወይም “በፈገግታ የተሞላ ፊት።”
^ ወይም “ነፍሱን።”
^ ቃል በቃል “ልብ።”