ምሳሌ 3:1-35

  • ጥበበኛ ሁን፤ በይሖዋ ታመን (1-12)

    • ባሉህ ውድ ነገሮች ይሖዋን አክብር (9)

  • ጥበብ ደስታ ታስገኛለች (13-18)

  • ጥበብ ጥበቃ ታስገኛለች (19-26)

  • ሌሎችን በአግባቡ መያዝ (27-35)

    • ‘ለሌሎች መልካም ነገር ከማድረግ ወደኋላ አትበል’ (27)

3  ልጄ ሆይ፣ ትምህርቴን* አትርሳ፤ልብህም ትእዛዛቴን ይጠብቅ፤  2  ረጅም ዕድሜና የሕይወት ዘመንእንዲሁም ሰላም ያስገኙልሃልና።+  3  ታማኝ ፍቅርና ታማኝነት* አይለዩህ።+ በአንገትህ ዙሪያ እሰራቸው፤በልብህ ጽላት ላይ ጻፋቸው፤+  4  ያን ጊዜ በአምላክና በሰው ፊት ሞገስ ታገኛለህ፤+እንዲሁም ጥሩ ማስተዋል እንዳለህ ታስመሠክራለህ።  5  በሙሉ ልብህ በይሖዋ ታመን፤+ደግሞም በገዛ ራስህ ማስተዋል አትመካ።*+  6  በመንገድህ ሁሉ እሱን ግምት ውስጥ አስገባ፤+እሱም ጎዳናህን ቀና ያደርገዋል።+  7  በራስህ አመለካከት ጥበበኛ አትሁን።+ ይሖዋን ፍራ፤ ከክፉም ራቅ።  8  ለሰውነትህ* ፈውስ፣ለአጥንትህም ብርታት ይሆንልሃል።  9  ባሉህ ውድ ነገሮች፣+ከምርትህ* ሁሉ በኩራት* ይሖዋን አክብር፤+ 10  ይህን ካደረግክ ጎተራዎችህ ጢም ብለው ይሞላሉ፤+በወይን መጭመቂያዎችህም አዲስ የወይን ጠጅ ሞልቶ ይፈስሳል። 11  ልጄ ሆይ፣ የይሖዋን ተግሣጽ ለመቀበል እንቢተኛ አትሁን፤+ወቀሳውም አያስመርርህ፤+ 12  አባት ደስ የሚሰኝበትን ልጁን እንደሚወቅስ ሁሉይሖዋም የሚወዳቸውን ይወቅሳልና።+ 13  ጥበብን የሚያገኝ፣+ጥልቅ ግንዛቤንም የራሱ የሚያደርግ ሰው ደስተኛ ነው፤ 14  ጥበብን ማግኘት ብርን ከማግኘት የተሻለ ነው፤እሷንም ማትረፍ ወርቅ ከማግኘት የተሻለ ነው።+ 15  ከዛጎል* ይበልጥ ውድ ናት፤አንተ የምትመኘው ማንኛውም ነገር ሊተካከላት አይችልም። 16  በቀኟ ረጅም ዕድሜ አለ፤በግራዋም ሀብትና ክብር ይገኛል። 17  መንገዷ ደስ የሚያሰኝ ነው፤ጎዳናዋም ሁሉ ሰላም የሰፈነበት ነው።+ 18  ለሚይዟት የሕይወት ዛፍ ናት፤አጥብቀው የሚይዟትም ደስተኞች ይባላሉ።+ 19  ይሖዋ በጥበብ ምድርን መሠረተ።+ በማስተዋል ሰማያትን አጸና።+ 20  በእውቀቱ ጥልቅ ውኃዎች ተከፈሉ፤ደመና ያዘሉ ሰማያትም ጠል አንጠባጠቡ።+ 21  ልጄ ሆይ፣ እነዚህ ባሕርያት ከእይታህ አይራቁ።* ጥበብንና* የማመዛዘን ችሎታን ጠብቅ፤ 22  ሕይወት ያስገኙልሃል፤*ለአንገትህም ጌጥ ይሆናሉ፤ 23  በዚያን ጊዜ በመንገድህ ላይ ተማምነህ ትሄዳለህ፤እግርህም ፈጽሞ አይሰናከልም።*+ 24  በምትተኛበት ጊዜ አትፈራም፤+ትተኛለህ፤ እንቅልፍህም ጣፋጭ ይሆናል።+ 25  ድንገት የሚከሰት የሚያሸብር ነገርም+ ሆነበክፉ ሰዎች ላይ የሚመጣ መዓት አያስፈራህም።+ 26  ይሖዋ መታመኛህ ይሆናልና፤+እግርህን በወጥመድ እንዳይያዝ ይጠብቃል።+ 27  ሰዎችን ለመርዳት የሚያስችል አቅም ካለህ*+ለሚገባቸው መልካም ነገር ከማድረግ ወደኋላ አትበል።+ 28  ለባልንጀራህ አሁኑኑ መስጠት እየቻልክ “ሂድና በኋላ ተመልሰህ ና! ነገ እሰጥሃለሁ” አትበለው። 29  ከአንተ ጋር ተማምኖ እየኖረ ሳለባልንጀራህን ለመጉዳት አታሲር።+ 30  መጥፎ ነገር ካላደረገብህከሰው ጋር ያለምክንያት አትጣላ።+ 31  በዓመፀኛ ሰው አትቅና፤+የትኛውንም መንገዱን አትምረጥ፤ 32  ይሖዋ ተንኮለኛን ሰው ይጸየፋልና፤+ከቅኖች ጋር ግን የጠበቀ ወዳጅነት አለው።+ 33  ይሖዋ የክፉውን ቤት ይረግማል፤+የጻድቁን መኖሪያ ግን ይባርካል።+ 34  በፌዘኞች ላይ ይሳለቃል፤+ለየዋሆች ግን ሞገስ ያሳያል።+ 35  ጥበበኞች ክብርን ይወርሳሉ፤ሞኞች ግን ለውርደት የሚዳርግን ነገር ከፍ አድርገው ይመለከታሉ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ሕጌን።”
ወይም “እውነት።”
ቃል በቃል “በገዛ ራስህ ማስተዋል አትደገፍ።”
ቃል በቃል “ለእምብርትህ።”
ወይም “ምርጥ በሆነው ነገር።”
ወይም “ከገቢህ።”
ከላይ በሚገኙት ቁጥሮች ላይ የተጠቀሱትን የአምላክ ባሕርያት የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።
ወይም “ማስተዋል የታከለበትን ጥበብና።”
ወይም “ለነፍስህ ሕይወት ያስገኙላታል።”
ወይም “ከምንም ነገር ጋር አይጋጭም።”
ወይም “ማድረግ እስከቻልክ ድረስ።”