ምሳሌ 5:1-23

  • ሥነ ምግባር ከጎደላት ሴት ራቅ (1-14)

  • ከሚስትህ ጋር ደስ ይበልህ (15-23)

5  ልጄ ሆይ፣ ጥበቤን ልብ በል። ማስተዋልን በተመለከተ የምሰጠውን ትምህርት በጥሞና አዳምጥ፤*+  2  ይህም የማመዛዘን ችሎታህን እንድትጠብቅ፣በከንፈሮችህም እውቀትን በጥንቃቄ እንድትይዝ ነው።+  3  የጋጠወጥ* ሴት ከንፈር እንደ ማር እንጀራ ያንጠባጥባልና፤+አፏም ከዘይት ይለሰልሳል።+  4  በመጨረሻ ግን እንደ ጭቁኝ ትመርራለች፤+ደግሞም በሁለት በኩል እንደተሳለ ሰይፍ ትሆናለች።+  5  እግሮቿ ወደ ሞት ይወርዳሉ። እርምጃዎቿ በቀጥታ ወደ መቃብር* ይመራሉ።  6  ስለ ሕይወት መንገድ ግድ የላትም። በጎዳናዎቿ ላይ ትባዝናለች፤ ወዴት እንደሚወስዱም አታውቅም።  7  እንግዲህ ልጆቼ ሆይ፣ አዳምጡኝ፤ከምናገረውም ቃል አትራቁ።  8  ከእሷ ራቅ፤ወደ ቤቷም ደጃፍ አትቅረብ፤+  9  ይህም ክብርህን ለሌሎች አሳልፈህ እንዳትሰጥ ነው፤+ቀሪ የሕይወት ዘመንህም በመከራ የተሞላ እንዳይሆን ነው፤+ 10  ደግሞም እንግዳ የሆኑ ሰዎች ጥሪትህን* እንዳያሟጥጡ፣+የለፋህበትንም ነገር የባዕድ አገር ሰው እንዳይወርሰው ነው። 11  አለዚያ በሕይወትህ ማብቂያሥጋህና መላ ሰውነትህ እየመነመነ ሲሄድ ትቃትታለህ፤+ 12  ደግሞም እንዲህ ትላለህ፦ “ምነው ተግሣጽን ጠላሁ! ልቤስ ምነው ወቀሳን ናቀ! 13  የአስተማሪዎቼን ቃል አላዳመጥኩም፤መምህሮቼንም በጥሞና አልሰማሁም። 14  በመላው ጉባኤ መካከል*ሙሉ በሙሉ ልጠፋ ምንም አልቀረኝም ነበር።”+ 15  ከራስህ ጉድጓድ እንዲሁምከገዛ ምንጭህ የሚፈልቀውን ውኃ ጠጣ።*+ 16  ምንጮችህ ወደ ውጭ፣ጅረቶችህም በአደባባይ ሊፈሱ ይገባል?+ 17  ለአንተ ብቻ ይሁኑ፤ከአንተ ጋር ላሉ እንግዶችም አይሁኑ።+ 18  ምንጭህ የተባረከ ይሁን፤ከወጣትነት ሚስትህም ጋር ደስ ይበልህ፤+ 19  እሷ እንደምትወደድ ሚዳቋና እንደምታምር የተራራ ፍየል* ናት።+ ጡቶቿ ምንጊዜም ያርኩህ።* ፍቅሯ ምንጊዜም ይማርክህ።+ 20  ልጄ ሆይ፣ ጋጠወጥ* ሴት ለምን ትማርክሃለች?ባለጌ* ሴትንስ ለምን ታቅፋለህ?+ 21  የሰው መንገድ በይሖዋ ዓይኖች ፊት ነውና፤እሱ መንገዱን ሁሉ ይመረምራል።+ 22  ክፉ ሰው የገዛ ጥፋቱ ወጥመድ ይሆንበታል፤ኃጢአቱም እንደ ገመድ ተብትቦ ይይዘዋል።+ 23  ተግሣጽ ከማጣቱ የተነሳ ይሞታል፤በጣም ሞኝ ከመሆኑም የተነሳ መንገድ ይስታል።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ወደ ማስተዋሌ ጆሮህን አዘንብል።”
ቃል በቃል “የእንግዳ።” ምሳሌ 2:16ን ተመልከት።
ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ኃይልህን።”
ቃል በቃል “በማኅበርና በጉባኤ መካከል።”
ወይም “የምንጭህን ንጹሕ ውኃ ጠጣ።”
ወይም “ዋልያ።”
ወይም “ያስክሩህ።”
ቃል በቃል “እንግዳ።” ምሳሌ 2:16ን ተመልከት።
ቃል በቃል “ባዕድ።” ምሳሌ 2:16ን ተመልከት።