ምሳሌ 6:1-35

  • ዋስ መሆን ችግር ሊያስከትል ይችላል (1-5)

  • “አንተ ሰነፍ፣ ወደ ጉንዳን ሂድ” (6-11)

  • የማይረባና ክፉ ሰው (12-15)

  • ይሖዋ የሚጠላቸው ሰባት ነገሮች (16-19)

  • ከክፉ ሴት ራስህን ጠብቅ (20-35)

6  ልጄ ሆይ፣ ለባልንጀራህ ዋስ* ብትሆን፣+የማታውቀውን ሰው እጅ ብትመታ፣*+  2  በገባኸው ቃል ብትጠመድ፣ከአፍህ በወጣው ቃል ብትያዝ፣+  3  ልጄ ሆይ፣ በባልንጀራህ እጅ ወድቀሃልና፣ይህን በማድረግ ራስህን ነፃ አውጣ፦ ሂድና ባልንጀራህን በትሕትና አጥብቀህ ለምነው።+  4  ይህን ሳታደርግ አትተኛ፤በዓይንህም እንቅልፍ አይዙር።  5  እንደ ሜዳ ፍየል ከአዳኝ እጅ፣እንደ ወፍም ከወፍ አዳኝ እጅ ራስህን አድን።  6  አንተ ሰነፍ፣ ወደ ጉንዳን ሂድ፤+መንገዷንም በጥሞና ተመልክተህ ጥበበኛ ሁን።  7  አዛዥ፣ አለቃ ወይም ገዢ ባይኖራትም እንኳ፣  8  ምግቧን በበጋ ታዘጋጃለች፤+ቀለቧንም በመከር ወቅት ትሰበስባለች።  9  አንተ ሰነፍ፣ የምትጋደመው እስከ መቼ ነው? ከእንቅልፍህ የምትነሳውስ መቼ ነው? 10  ቆይ ትንሽ ልተኛ፣ ቆይ ትንሽ ላንቀላፋ፣እጄንም አጣጥፌ እስቲ ትንሽ ጋደም ልበል ካልክ፣+ 11  ድህነት እንደ ወንበዴ፣እጦትም መሣሪያ እንደታጠቀ ሰው ይመጣብሃል።+ 12  የማይረባና ክፉ ሰው ንግግሩ ጠማማ ነው፤+ 13  በዓይኑ ይጣቀሳል፤+ በእግሩ ምልክት ይሰጣል፤ በጣቶቹም ይጠቁማል። 14  ጠማማ በሆነው ልቡ፣ነጋ ጠባ ሴራ ይጠነስሳል፤+ ጠብም ይዘራል።+ 15  በመሆኑም ጥፋት በድንገት ይመጣበታል፤እንደማይጠገን ሆኖ በቅጽበት ይሰበራል።+ 16  ይሖዋ የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች አሉ፤እንዲያውም እሱ የሚጸየፋቸው* ነገሮች ሰባት ናቸው፦ 17  ትዕቢተኛ ዓይን፣+ ውሸታም ምላስ፣+ ንጹሕ ደም የሚያፈሱ እጆች፣+ 18  ክፉ ሐሳብ የሚያውጠነጥን ልብና+ ወደ ክፋት በፍጥነት የሚሮጡ እግሮች፣ 19  ባወራ ቁጥር ውሸት የሚናገር ሐሰተኛ ምሥክርና+በወንድማማቾች መካከል ጠብ የሚዘራ ሰው።+ 20  ልጄ ሆይ፣ የአባትህን ትእዛዝ ጠብቅ፤የእናትህንም መመሪያ* ቸል አትበል።+ 21  ምንጊዜም በልብህ አኑራቸው፤በአንገትህም ዙሪያ እሰራቸው። 22  በምትሄድበት ሁሉ ይመራሃል፤ስትተኛም ይጠብቅሃል፤ስትነቃም ያነጋግርሃል።* 23  ትእዛዙ መብራት ነውና፤+ሕጉም ብርሃን ነው፤+የተግሣጽ ወቀሳም ወደ ሕይወት ይመራል።+ 24  ከክፉ ሴት፣+ ከባለጌ* ሴትምየሚያባብል አንደበት ይጠብቁሃል።+ 25  ውበቷን በልብህ አትመኝ፤+የሚያማምሩ ዓይኖቿም አይማርኩህ፤ 26  አንድ ሰው በዝሙት አዳሪ የተነሳ ለድህነት ይዳረጋልና፤*+አመንዝራ ሴት ደግሞ የሰውን ውድ ሕይወት* ታጠምዳለች። 27  በጉያው እሳት ታቅፎ ልብሱ የማይቃጠልበት ሰው አለ?+ 28  ወይስ በፍም ላይ ተራምዶ እግሮቹ የማይቃጠሉበት ሰው ይኖራል? 29  ከባልንጀራው ሚስት ጋር የሚተኛ ሰውም እንደዚሁ ነው፤የሚነካት ሁሉ መቀጣቱ አይቀርም።+ 30  ሌባ በተራበ ጊዜ ራሱን* ሊያጠግብ ቢሰርቅ፣ሰዎች በንቀት አያዩትም። 31  በተያዘ ጊዜ ግን ሰባት እጥፍ ይከፍላል፤በቤቱ ያለውን ውድ ነገር ሁሉ ያስረክባል።+ 32  ከሴት ጋር ምንዝር የሚፈጽም ሁሉ ማስተዋል* ይጎድለዋል፤እንዲህ የሚያደርግ ሰው በራሱ* ላይ ጥፋት ያመጣል።+ 33  የሚያተርፈው ነገር ቢኖር ቁስልና ውርደት ነው፤+ኀፍረቱም መቼም አይወገድም።+ 34  ቅናት ባልን እጅግ ያስቆጣዋልና፤ለበቀል በሚነሳበት ጊዜም ፈጽሞ ርኅራኄ አያሳይም።+ 35  ማንኛውንም ዓይነት ካሳ* አይቀበልም፤ምንም ያህል ስጦታ ብታቀርብለት ቁጣው አይበርድም።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ብትጨብጥ።” ቃል መግባትን ያመለክታል።
ቃል በቃል “ተያዥ።”
ወይም “ነፍሱ የምትጸየፋቸው።”
ወይም “ሕግ፤ ትምህርት።”
ወይም “ያስተምርሃል።”
ቃል በቃል “ከባዕድ።” ምሳሌ 2:16ን ተመልከት።
ወይም “ነፍስ።”
ቃል በቃል “አንድ ሰው ያለውን ሁሉ አጥቶ አንድ ዳቦ ብቻ ይቀረዋል።”
ወይም “ነፍሱን።”
ቃል በቃል “ልብ።”
ወይም “በነፍሱ።”
ወይም “ቤዛ።”