ምሳሌ 8:1-36

  • ጥበብ በሰው ተመስላ ተናገረች (1-36)

    • ‘አምላክ ከሥራዎቹ ቀዳሚ አደረገኝ’ (22)

    • ‘የተዋጣለት ሠራተኛ ሆኜ ከአምላክ ጎን ነበርኩ’ (30)

    • “በሰው ልጆች እጅግ እደሰት ነበር” (31)

8  ጥበብ እየተጣራች አይደለም? ማስተዋልስ ድምፅዋን ከፍ አድርጋ እያሰማች አይደለም?+  2  በጎዳና አጠገብ በሚገኙ ከፍታ ቦታዎች፣+መንገዶች በሚገናኙበት ቦታ ላይ ቆማለች።  3  ወደ ከተማዋ በሚያስገቡት በሮች አጠገብ፣በደጆቹ መግቢያዎች ላይድምፅዋን ከፍ አድርጋ ትጮኻለች፦+  4  “ሰዎች ሆይ፣ የምጣራው እናንተን ነው፤ድምፄን ከፍ አድርጌ የማሰማው ለሁሉም* ነው።  5  እናንተ ተሞክሮ የሌላችሁ፣ ብልሃትን ተማሩ፤+እናንተ ሞኞች፣ አስተዋይ ልብ ይኑራችሁ።  6  የምናገረው ነገር በጣም አስፈላጊ ስለሆነ አዳምጡኝ፤ከንፈሮቼ ትክክል የሆነውን ይናገራሉ፤  7  አንደበቴ በለሰለሰ ድምፅ እውነትን ይናገራልና፤ከንፈሮቼም ክፋትን ይጸየፋሉ።  8  ከአፌ የሚወጡት ቃላት ሁሉ ጽድቅ ናቸው። የተጣመመ ወይም የተወላገደ ነገር አይገኝባቸውም።  9  ጥልቅ ግንዛቤ ላለው፣ ሁሉም ቀና ናቸው፤እውቀት ላላቸውም ትክክል ናቸው። 10  ከብር ይልቅ ተግሣጼን፣ጥራት ካለውም ወርቅ ይልቅ እውቀትን ተቀበሉ፤+ 11  ጥበብ ከዛጎል* ትበልጣለችና፤ተፈላጊ የሆኑ ሌሎች ነገሮች ሁሉ ከእሷ ጋር ሊወዳደሩ አይችሉም። 12  እኔ ጥበብ፣ ከብልሃት ጋር አብሬ እኖራለሁ፤እውቀትና የማመዛዘን ችሎታ አግኝቻለሁ።+ 13  ይሖዋን መፍራት ማለት ክፉ ነገርን መጥላት ነው።+ ትዕቢትን፣ ኩራትን፣+ ክፉ መንገድንና ጠማማ ንግግርን እጠላለሁ።+ 14  ጥሩ ምክር መስጠት እችላለሁ፤ ማስተዋል የታከለበት ጥበብም አለኝ፤+ማስተዋልና+ ኃይል+ የእኔ ናቸው። 15  ነገሥታት የሚገዙት በእኔ ነው፤ከፍተኛ ባለሥልጣናትም የጽድቅ ድንጋጌ የሚያወጡት በእኔ ነው።+ 16  መኳንንት የሚገዙት በእኔ ነው፤ታላላቅ ሰዎችም በጽድቅ የሚፈርዱት በእኔ ነው። 17  የሚወዱኝን እወዳቸዋለሁ፤የሚፈልጉኝም ያገኙኛል።+ 18  ሀብትና ክብር፣ዘላቂ ብልጽግናና* ጽድቅ በእኔ ዘንድ አሉ። 19  ፍሬዬ ከወርቅ፣ አልፎ ተርፎም ከጠራ ወርቅ ይሻላል፤ከእኔ የምታገኙት ስጦታም ጥራት ካለው ብር ይበልጣል።+ 20  በጽድቅ መንገድ፣በፍትሕ ጎዳና መካከል እጓዛለሁ፤ 21  ለሚወዱኝ ውድ የሆኑ ነገሮችን አወርሳለሁ፤ግምጃ ቤቶቻቸውንም እሞላለሁ። 22  ይሖዋ የመንገዱ መጀመሪያ አድርጎ ፈጠረኝ፤+ከብዙ ዘመን በፊት ካከናወናቸው ሥራዎች ቀዳሚው አደረገኝ።+ 23  ከጥንት፣* ከመጀመሪያው አንስቶ፣ምድርም ከመፈጠሯ አስቀድሞ+ ከፍ ያለ ቦታ ተሰጠኝ።+ 24  ጥልቅ ውኃዎች ባልነበሩበት ጊዜ፣+ምንጮች ከመፍለቃቸው በፊት ተወለድኩ።* 25  ተራሮች ገና ሳይመሠረቱ፣ከኮረብቶች በፊት ተወለድኩ፤ 26  ምድርንም ሆነ ሜዳዎቹን እንዲሁምየመጀመሪያዎቹን የአፈር ጓሎች ከመሥራቱ በፊት ተወለድኩ። 27  ሰማያትን ባዘጋጀ ጊዜ+ በዚያ ነበርኩ፤በውኃዎች ላይ የአድማስን ምልክት* ባደረገ ጊዜ፣+ 28  ደመናትን በላይ ባዘጋጀ* ጊዜ፣የጥልቅ ውኃ ምንጮችን በመሠረተ ጊዜ፣ 29  የባሕሩ ውኃከትእዛዙ አልፎ እንዳይሄድ በደነገገ ጊዜ፣+የምድርን መሠረቶች ባቆመ* ጊዜ፣ 30  በዚያን ወቅት የተዋጣለት ሠራተኛ ሆኜ ከጎኑ ነበርኩ።+ በየዕለቱ በእኔ የተነሳ ልዩ ደስታ ይሰማው ነበር፤+እኔም በፊቱ ሁልጊዜ ሐሴት አደርግ ነበር፤+ 31  እሱ በፈጠረው፣ ሰው በሚኖርበት ምድር ሐሴት አደረግኩ፤በተለይ ደግሞ በሰው ልጆች እጅግ እደሰት ነበር። 32  እንግዲህ ልጆቼ ሆይ፣ አዳምጡኝ፤አዎ፣ መንገዴን የሚጠብቁ ደስተኞች ናቸው። 33  ተግሣጽን ስሙ፤+ ጥበበኞችም ሁኑ፤ፈጽሞም ቸል አትበሉት። 34  በየዕለቱ በማለዳ በራፌ ላይ መጥቶ፣*በበሬ መቃን አጠገብ ቆሞ በመጠባበቅየሚያዳምጠኝ ሰው ደስተኛ ነው፤ 35  እኔን የሚያገኝ ሕይወትን ያገኛልና፤+በይሖዋም ዘንድ ሞገስ ያገኛል። 36  እኔን ችላ የሚል ግን ራሱን* ይጎዳል፤የሚጠሉኝ ሁሉ ሞትን ይወዳሉ።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ለሰው ወንዶች ልጆች።”
ወይም “በውርስ የተገኙ ውድ ነገሮችና።”
ወይም “በውል ከማይታወቁ ዘመናት በፊት።”
ወይም “በምጥ ተወለድኩ።”
ቃል በቃል “ክበብን።”
ቃል በቃል “ባጸና።”
ወይም “በደነገገ።”
ወይም “በየዕለቱ በራፌ ላይ ነቅቶ በመጠበቅ።”
ወይም “ነፍሱን።”