ለዮሐንስ የተገለጠለት ራእይ 8:1-13

  • ሰባተኛው ማኅተም ተከፈተ (1-6)

  • የመጀመሪያዎቹ አራት መለከቶች ተነፉ (7-12)

  • ሦስት ወዮታዎች ታወጁ (13)

8  ሰባተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ+ በሰማይ ለግማሽ ሰዓት ያህል ጸጥታ ሰፈነ። 2  እኔም በአምላክ ፊት የሚቆሙትን ሰባቱን መላእክት አየሁ፤+ ሰባት መለከትም ተሰጣቸው። 3  የወርቅ ጥና* የያዘ ሌላ መልአክ መጥቶ በመሠዊያው+ አጠገብ ቆመ፤ እሱም የቅዱሳኑ ሁሉ ጸሎት እየተሰማ በነበረበት ወቅት በዙፋኑ ፊት ባለው በወርቁ መሠዊያ+ ላይ እንዲያቀርበው ከፍተኛ መጠን ያለው ዕጣን+ ተሰጠው። 4  በመልአኩ እጅ ያለው የዕጣኑ ጭስ እንዲሁም የቅዱሳኑ ጸሎት+ በአምላክ ፊት ወደ ላይ ወጣ። 5  ሆኖም መልአኩ ወዲያውኑ ጥናውን ይዞ ከመሠዊያው ላይ እሳት በመውሰድ ጥናውን ሞላውና እሳቱን ወደ ምድር ወረወረው። ከዚያም ነጎድጓድ፣ ድምፅ፣ የመብረቅ ብልጭታና+ የምድር ነውጥ ተከሰተ። 6  ሰባቱን መለከቶች የያዙት ሰባቱ መላእክትም+ ሊነፉ ተዘጋጁ። 7  የመጀመሪያው መለከቱን ነፋ። ከደም ጋር የተቀላቀለ በረዶና እሳት ታየ፤ ወደ ምድርም ተወረወረ፤+ የምድር አንድ ሦስተኛ ተቃጠለ፤ የዛፎችም አንድ ሦስተኛ ተቃጠለ፤ የለመለሙ ተክሎችም ሁሉ ተቃጠሉ።+ 8  ሁለተኛው መልአክ መለከቱን ነፋ። በእሳት የተቀጣጠለ ትልቅ ተራራ የሚመስል ነገርም ወደ ባሕር ተወረወረ።+ የባሕሩም አንድ ሦስተኛ ደም ሆነ፤+ 9  በባሕር ውስጥ ካሉ ሕያዋን ፍጥረታትም* አንድ ሦስተኛው ሞተ፤+ ከመርከቦችም አንድ ሦስተኛው ወደመ። 10  ሦስተኛው መልአክ መለከቱን ነፋ። እንደ መብራት ቦግ ያለ አንድ ትልቅ ኮከብም ከሰማይ ወደቀ፤ በወንዞች አንድ ሦስተኛና በውኃ ምንጮች ላይ ወደቀ።+ 11  ኮከቡ ጭቁኝ ይባላል። የውኃውም አንድ ሦስተኛ እንደ ጭቁኝ መራራ ሆነ፤ ውኃውም መራራ+ ከመሆኑ የተነሳ ብዙ ሰዎች በውኃው ጠንቅ ሞቱ። 12  አራተኛው መልአክ መለከቱን ነፋ። የፀሐይ አንድ ሦስተኛ፣+ የጨረቃ አንድ ሦስተኛና የከዋክብት አንድ ሦስተኛ ተመታ፤ ይህም የሆነው የእነዚህ አካላት አንድ ሦስተኛው እንዲጨልም+ እንዲሁም የቀኑ አንድ ሦስተኛና የሌሊቱ አንድ ሦስተኛ ብርሃን እንዳያገኝ ነው። 13  እኔም አየሁ፤ አንድ ንስር በሰማይ መካከል እየበረረ በታላቅ ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማሁ፦ “መለከቶቻቸውን ሊነፉ የተዘጋጁት ሦስቱ መላእክት+ በሚያሰሟቸው በቀሩት ኃይለኛ የመለከት ድምፆች የተነሳ በምድር ላይ ለሚኖሩት ወዮላቸው! ወዮላቸው! ወዮላቸው!”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ዕጣን ማጨሻ።”
ወይም “ነፍስ ያላቸው ፍጥረታትም።”