ለሮም ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ 12:1-21
12 እንግዲህ ወንድሞች፣ ሰውነታችሁን ሕያው፣ ቅዱስና+ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት አድርጋችሁ እንድታቀርቡ+ በአምላክ ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፤ ይህም የማሰብ ችሎታችሁን ተጠቅማችሁ የምታቀርቡት ቅዱስ አገልግሎት ነው።+
2 በተጨማሪም ይህ ሥርዓት* እንዲቀርጻችሁ አትፍቀዱ፤ ከዚህ ይልቅ ጥሩ የሆነውን፣ ተቀባይነት ያለውንና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ መርምራችሁ ማረጋገጥ ትችሉ ዘንድ+ አእምሯችሁን በማደስ ተለወጡ።+
3 እያንዳንዱ ሰው ከሚገባው በላይ ስለ ራሱ በማሰብ ራሱን ከፍ አድርጎ አይመልከት፤+ ከዚህ ይልቅ አምላክ ለእያንዳንዱ በሰጠው* እምነት መሠረት ጤናማ አስተሳሰብ እንዳለው በሚያሳይ መንገድ እንዲያስብ፣ በመካከላችሁ ያለውን እያንዳንዱን ሰው በተሰጠኝ ጸጋ እመክራለሁ።+
4 በአንድ አካል ላይ ብዙ የአካል ክፍሎች አሉን፤+ ደግሞም ሁሉም የአካል ክፍሎች አንድ ዓይነት ተግባር አያከናውኑም፤
5 ልክ እንደዚሁ እኛም ብዙ ብንሆንም እንኳ ከክርስቶስ ጋር ባለን አንድነት አንድ አካል ነን፤ ደግሞም አንዳችን የሌላው የአካል ክፍል ነን።+
6 በመሆኑም በተሰጠን ጸጋ መሠረት+ የተለያዩ ስጦታዎች ስላሉን ስጦታችን ትንቢት መናገር ከሆነ በተሰጠን እምነት መሠረት ትንቢት እንናገር፤
7 ማገልገል ከሆነ ማገልገላችንን እንቀጥል፤ የሚያስተምርም ቢሆን ማስተማሩን ይቀጥል፤+
8 የሚያበረታታም* ቢሆን ማበረታቻ መስጠቱን ይቀጥል፤+ የሚሰጥ* በልግስና ይስጥ፤+ የሚያስተዳድር* በትጋት ያስተዳድር፤+ የሚምር በደስታ ይማር።+
9 ፍቅራችሁ ግብዝነት የሌለበት ይሁን።+ ክፉ የሆነውን ተጸየፉ፤+ ጥሩ የሆነውን አጥብቃችሁ ያዙ።
10 በወንድማማች ፍቅር እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ። አንዳችሁ ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ ሁኑ።*+
11 ታታሪዎች* ሁኑ እንጂ አትስነፉ።*+ በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ።+ ይሖዋን* እንደ ባሪያ አገልግሉ።+
12 በተስፋው ደስ ይበላችሁ። መከራን በጽናት ተቋቋሙ።+ ሳትታክቱ ጸልዩ።+
13 ለቅዱሳን እንደየችግራቸው ያላችሁን አካፍሉ።+ የእንግዳ ተቀባይነትን ባሕል አዳብሩ።+
14 ስደት የሚያደርሱባችሁን መርቁ፤+ መርቁ እንጂ አትርገሙ።+
15 ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፤ ከሚያለቅሱ ጋር አልቅሱ።
16 ለራሳችሁ ያላችሁ ዓይነት አመለካከት ለሌሎችም ይኑራችሁ፤ የትዕቢት ዝንባሌ እንዳያድርባችሁ ተጠንቀቁ፤ ትሕትና የሚንጸባረቅበት አስተሳሰብ ይኑራችሁ።+ ጥበበኞች እንደሆናችሁ አድርጋችሁ አታስቡ።+
17 ለማንም በክፉ ፋንታ ክፉ አትመልሱ።+ በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን ነገር ለማድረግ ጥረት አድርጉ።
18 ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ።+
19 የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ራሳችሁ አትበቀሉ፤ ከዚህ ይልቅ “‘በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ’ ይላል ይሖዋ”*+ ተብሎ ስለተጻፈ ለቁጣው* ዕድል ስጡ።+
20 ነገር ግን “ጠላትህ ቢራብ አብላው፤ ቢጠማ አጠጣው፤ ይህን በማድረግ በራሱ ላይ ፍም ትከምራለህ።”*+
21 በክፉ አትሸነፍ፤ ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም ክፉውን በመልካም አሸንፍ።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “ይህ ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ወይም “በመደበው፤ ባከፋፈለው።”
^ ወይም “የሚመክርም።”
^ ወይም “የሚያዋጣ።”
^ ወይም “አመራር የሚሰጥ።”
^ ወይም “ተነሳሽነት ይኑራችሁ።”
^ ወይም “ትጉዎች፤ ቀናተኞች።”
^ ወይም “በሥራችሁ አትለግሙ።”
^ የአምላክን ቁጣ ያመለክታል።
^ የሰውየው ልብ እንዲለሰልስና ቁጣው እንዲበርድ ማድረግን ያመለክታል።