ለሮም ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ 13:1-14
13 ሰው* ሁሉ ለበላይ ባለሥልጣናት ይገዛ፤+ ሥልጣን ሁሉ የሚገኘው ከአምላክ ነውና፤+ ያሉት ባለሥልጣናት አንጻራዊ ቦታቸውን ያገኙት ከአምላክ ነው።+
2 ስለዚህ ባለሥልጣንን የሚቃወም ሁሉ አምላክ ያደረገውን ዝግጅት ይቃወማል፤ ይህን ዝግጅት የሚቃወሙ በራሳቸው ላይ ፍርድ ያመጣሉ።
3 ገዢዎች የሚያስፈሩት ክፉ ለሚያደርጉ እንጂ መልካም ለሚያደርጉ አይደለምና።+ እንግዲያው ባለሥልጣንን መፍራት የማትፈልግ ከሆነ መልካም ማድረግህን ቀጥል፤+ ከእሱም ምስጋና ታገኛለህ፤
4 ለአንተ ጥቅም ሲባል የተሾመ የአምላክ አገልጋይ ነውና። ክፉ የምታደርግ ከሆነ ግን ልትፈራ ይገባሃል፤ ምክንያቱም ሰይፍ የሚታጠቀው እንዲያው በከንቱ አይደለም። ክፉ የሚሠራን በመቅጣት* የሚበቀል የአምላክ አገልጋይ ነው።
5 ስለዚህ ቁጣውን በመፍራት ብቻ ሳይሆን ስለ ሕሊናችሁ ስትሉም መገዛታችሁ አስፈላጊ ነው።+
6 ቀረጥ የምትከፍሉትም ለዚሁ ነው፤ ምክንያቱም እነሱ ሕዝባዊ አገልግሎት የሚያከናውኑ የአምላክ አገልጋዮች ናቸው፤ የዘወትር ተግባራቸውም ይኸው ነው።
7 ለሁሉም የሚገባውን አስረክቡ፤ ቀረጥ ለሚጠይቅ ቀረጥ፣+ ግብር ለሚጠይቅ ግብር ስጡ፤ መፈራት የሚፈልገውን ፍሩ፤+ መከበር የሚፈልገውን አክብሩ።+
8 እርስ በርስ ከመዋደድ በቀር በማንም ላይ ምንም ዕዳ አይኑርባችሁ፤+ ሰውን የሚወድ ሁሉ ሕጉን ፈጽሟልና።+
9 ምክንያቱም “አታመንዝር፣+ አትግደል፣+ አትስረቅ፣+ አትጎምጅ”+ የሚሉት ሕጎችና ሌሎች ትእዛዛት በሙሉ “ባልንጀራህን* እንደ ራስህ ውደድ”+ በሚለው በዚህ ቃል ተጠቃለዋል።
10 ፍቅር በባልንጀራው ላይ ክፉ አያደርግም፤+ ስለዚህ ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው።+
11 ምን ዓይነት ዘመን ላይ እንደምንገኝ ስለምታውቁም ይህን አድርጉ፤ አማኞች ከሆንበት ጊዜ ይልቅ አሁን መዳናችን ይበልጥ ስለቀረበ ከእንቅልፍ የምትነቁበት ሰዓት አሁን ነው።+
12 ሌሊቱ እየተገባደደ ነው፤ ቀኑም ቀርቧል። ስለዚህ ከጨለማ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን አውልቀን+ የብርሃንን የጦር ዕቃዎች እንልበስ።+
13 መረን በለቀቀ ፈንጠዝያና በስካር፣ ልቅ በሆነ የፆታ ግንኙነትና ማንአለብኝነት በሚንጸባረቅበት ድርጊት*+ እንዲሁም በጠብና በቅናት+ ሳይሆን በቀን ብርሃን እንደምንመላለስ በጨዋነት እንመላለስ።+
14 ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤+ የሥጋ ፍላጎታችሁን ለማርካት ዕቅድ አታውጡ።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “ነፍስ።”
^ ወይም “ክፉ በሚሠራ ላይ የአምላክን ቁጣ በመግለጽ።”
^ “ባልንጀራ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል የአንድን ሰው የቅርብ ጓደኛ ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ሰው ሊያመለክት ይችላል።
^ ወይም “እፍረተ ቢስነት በሚንጸባረቅበት ምግባር።” እዚህ ላይ የገባው አሴልጊያ የሚለው ግሪክኛ ቃል ብዙ ቁጥር ነው። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።