ለሮም ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ 15:1-33
15 እኛ በእምነት ጠንካሮች የሆን ጠንካሮች ያልሆኑትን ሰዎች ድክመት ልንሸከም ይገባል+ እንጂ ራሳችንን የምናስደስት መሆን የለብንም።+
2 እያንዳንዳችን ባልንጀራችንን* የሚጠቅመውንና የሚያንጸውን ነገር በማድረግ እናስደስተው።+
3 ክርስቶስ እንኳ ራሱን አላስደሰተምና፤+ ይህም “ሰዎች አንተን ይነቅፉበት የነበረው ነቀፋ በእኔ ላይ ደረሰ” ተብሎ እንደተጻፈው ነው።+
4 በምናሳየው ጽናትና+ ከቅዱሳን መጻሕፍት በምናገኘው መጽናኛ ተስፋ ይኖረን ዘንድ+ ቀደም ብሎ የተጻፈው ነገር ሁሉ ለእኛ ትምህርት እንዲሆን ተጽፏልና።+
5 ጽናትንና መጽናኛን የሚሰጠው አምላክ፣ ሁላችሁም ክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ዓይነት አስተሳሰብ እንዲኖራችሁ ያድርግ፤
6 ይኸውም በኅብረትና+ በአንድ ድምፅ* የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክና አባት እንድታከብሩ ነው።
7 ስለዚህ ክርስቶስ እኛን እንደተቀበለን+ ሁሉ አምላክ እንዲከበር እናንተም አንዳችሁ ሌላውን ተቀበሉ።+
8 ክርስቶስ፣ አምላክ እውነተኛ መሆኑን ለማሳየት ሲል ለተገረዙት አገልጋይ እንደሆነ ልነግራችሁ እወዳለሁ፤+ በተጨማሪም አገልጋይ የሆነው፣ አምላክ ለአባቶቻቸው የገባውን ቃል ለማረጋገጥ+
9 እንዲሁም ብሔራት አምላክን ስለ ምሕረቱ ያከብሩት ዘንድ ነው።+ ይህም “ስለዚህ በብሔራት መካከል በይፋ አወድስሃለሁ፤ ለስምህም የውዳሴ መዝሙር እዘምራለሁ” ተብሎ እንደተጻፈው ነው።+
10 ደግሞም “እናንተ ብሔራት፣ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ” ይላል።+
11 እንደገናም “ብሔራት ሁሉ፣ ይሖዋን* አወድሱት፤ ሕዝቦችም ሁሉ ያወድሱት” ይላል።+
12 እንዲሁም ኢሳይያስ “የእሴይ ሥር ይገለጣል፤+ ብሔራትንም የሚገዛው ይነሳል፤+ ብሔራትም ተስፋቸውን በእሱ ላይ ይጥላሉ” ይላል።+
13 በእሱ በመታመናችሁ የተነሳ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተስፋ እንዲትረፈረፍላችሁ* ተስፋ የሚሰጠው አምላክ ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይሙላባችሁ።+
14 ወንድሞቼ ሆይ፣ እናንተ ራሳችሁ በጥሩነት የተሞላችሁ እንደሆናችሁ፣ የተሟላ እውቀት እንዳላችሁና አንዳችሁ ሌላውን መምከር* እንደምትችሉ እኔ ራሴ ስለ እናንተ እርግጠኛ መሆን ችያለሁ።
15 ይሁን እንጂ አንዳንድ ጉዳዮችን ግልጥልጥ አድርጌ የጻፍኩላችሁ ተጨማሪ ማሳሰቢያ ልሰጣችሁ ስለፈለግኩ ነው። ይህን የማደርገው ከአምላክ በተሰጠኝ ጸጋ የተነሳ ነው።
16 ይህ ጸጋ የተሰጠኝም ለአሕዛብ የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋይ እንድሆን ነው።+ የአምላክን ምሥራች በማወጁ ቅዱስ ሥራ+ የምካፈለው እነዚህ አሕዛብ በመንፈስ ቅዱስ የተቀደሰ፣ ተቀባይነት ያለው መባ ሆነው ለአምላክ እንዲቀርቡ ነው።
17 ስለዚህ ለአምላክ ከማቀርበው አገልግሎት ጋር በተያያዘ በክርስቶስ ኢየሱስ ሐሴት የማደርግበት ምክንያት አለኝ።
18 አሕዛብ ታዛዦች እንዲሆኑ ክርስቶስ በእኔ አማካኝነት ስላከናወነው ነገር ካልሆነ በቀር ስለ ሌላ ነገር ለመናገር አልደፍርም። ይህን ያከናወነው እኔ በተናገርኩትና ባደረግኩት ነገር
19 እንዲሁም በተአምራዊ ምልክቶችና ድንቅ ነገሮች+ ደግሞም በአምላክ መንፈስ ኃይል ነው፤ በመሆኑም ከኢየሩሳሌም አንስቶ ዙሪያውን እስከ እልዋሪቆን ድረስ ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውን ምሥራች በተሟላ ሁኔታ ሰብኬአለሁ።+
20 በዚህ መንገድ የክርስቶስ ስም አስቀድሞ በታወቀበት ቦታ ምሥራቹን ላለመስበክ የተቻለኝን ሁሉ ጥረት አድርጌአለሁ፤ ይህን ያደረግኩት ሌላ ሰው በጣለው መሠረት ላይ መገንባት ስላልፈለግኩ ነው፤
21 ይህም “ከዚህ በፊት ስለ እሱ ምንም ያልተነገራቸው ያያሉ፤ ያልሰሙም ያስተውላሉ” ተብሎ እንደተጻፈው ነው።+
22 በተደጋጋሚ ጊዜያት ወደ እናንተ መምጣት ሳልችል የቀረሁትም በዚህ ምክንያት ነው።
23 አሁን ግን በዚህ አካባቢ ባሉት አገሮች ያልሰበክሁበት ክልል የለም፤ ደግሞም ለብዙ ዓመታት* ወደ እናንተ ለመምጣት ስጓጓ ቆይቻለሁ።
24 በመሆኑም ወደ ስፔን በምጓዝበት ጊዜ እንደማገኛችሁና እናንተ ጋ ለተወሰነ ጊዜ ቆይቼ ናፍቆቴን ከተወጣሁ በኋላ ጥቂት መንገድ እንደምትሸኙኝ ተስፋ አደርጋለሁ።
25 አሁን ግን ቅዱሳንን ለማገልገል* ወደ ኢየሩሳሌም ልጓዝ ነው።+
26 በመቄዶንያና በአካይያ ያሉት ወንድሞች በኢየሩሳሌም ባሉት ቅዱሳን መካከል ለሚገኙት ድሆች መዋጮ በመስጠት ያላቸውን ነገር በደስታ አካፍለዋልና።+
27 አዎ፣ ይህን ያደረጉት በፈቃደኝነት ነው፤ ደግሞም የእነሱ ዕዳ ነበረባቸው፤ ምክንያቱም አሕዛብ የእነሱን መንፈሳዊ ነገር ከተካፈሉ እነሱ ደግሞ ለሚያስፈልጓቸው ቁሳዊ ነገሮች የማዋጣት ዕዳ አለባቸው።+
28 ስለሆነም ይህን ሥራ ካከናወንኩና መዋጮውን ካስረከብኳቸው* በኋላ በእናንተ በኩል አድርጌ ወደ ስፔን እሄዳለሁ።
29 ደግሞም ወደ እናንተ በምመጣበት ጊዜ የክርስቶስን የተትረፈረፈ በረከት ይዤላችሁ እንደምመጣ አውቃለሁ።
30 እንግዲህ ወንድሞች፣ ስለ እኔ አምላክን በመለመን ከእኔ ጋር አብራችሁ በጸሎት እንድትተጉ+ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስና ከመንፈስ በሚገኘው ፍቅር አበረታታችኋለሁ፤
31 በይሁዳ ካሉት የማያምኑ ሰዎች እጅ እንድድንና+ በኢየሩሳሌም ለሚገኙት ቅዱሳን+ የማቀርበው አገልግሎት* በእነሱ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ጸልዩልኝ፤
32 ይኸውም አምላክ ከፈቀደ ወደ እናንተ በደስታ እንድመጣና ከእናንተ ጋር በመሆን መንፈሴ እንዲታደስ ነው።
33 ሰላም የሚሰጠው አምላክ ከሁላችሁ ጋር ይሁን።+ አሜን።
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ “ባልንጀራ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል የአንድን ሰው የቅርብ ጓደኛ ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ሰው ሊያመለክት ይችላል።
^ ቃል በቃል “አፍ።”
^ ወይም “እንዲበዛላችሁ።”
^ ወይም “ማስተማር።”
^ “ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ ወይም “ለመርዳት።”
^ ቃል በቃል “ፍሬውን ከሰጠኋቸው።”
^ ወይም “እርዳታ።”