ለሮም ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ 5:1-21
5 ስለዚህ አሁን በእምነት አማካኝነት ጻድቃን ናችሁ+ ስለተባልን በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል+ ከአምላክ ጋር ያለንን ሰላም ጠብቀን እንኑር፤*
2 ደግሞም በኢየሱስ አማካኝነት የአምላክን ጸጋ ለማግኘት በእምነት ወደ እሱ መቅረብ የቻልን ሲሆን ይህን ጸጋ አሁን አግኝተናል፤+ የአምላክንም ክብር እንደምናገኝ ተስፋ በማድረግ እጅግ እንደሰት።*
3 በዚህ ብቻ ሳይሆን በመከራ ውስጥ እያለንም እጅግ እንደሰት፤*+ ምክንያቱም መከራ ጽናትን እንደሚያስገኝ እናውቃለን፤+
4 ጽናትም በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንድናገኝ+ ያስችለናል፤ ተቀባይነት ማግኘት ደግሞ ተስፋን+ ያጎናጽፋል፤
5 ተስፋውም ሳይፈጸም ቀርቶ ለሐዘን* አይዳርገንም፤+ ምክንያቱም የአምላክ ፍቅር፣ በተሰጠን መንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በልባችን ውስጥ ፈሷል።+
6 ገና ደካሞች ሳለን+ ክርስቶስ አስቀድሞ የተወሰነው ጊዜ ሲደርስ ለኃጢአተኞች ሞቷልና።
7 ለጻድቅ ሰው የሚሞት ማግኘት በጣም አዳጋች ነው፤ ለጥሩ ሰው ለመሞት የሚደፍር ግን ምናልባት ይገኝ ይሆናል።
8 ሆኖም አምላክ ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ እንዲሞትልን በማድረግ ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር አሳይቷል።+
9 ከእንግዲህ በደሙ ጻድቃን ናችሁ ስለተባልን+ በእሱ አማካኝነት ከአምላክ ቁጣ እንደምንድን ይበልጥ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።+
10 ጠላቶች ሆነን ሳለን በልጁ ሞት አማካኝነት ከአምላክ ጋር ከታረቅን አሁን ታርቀን ሳለንማ+ በእሱ ሕይወት እንደምንድን የተረጋገጠ ነው።
11 ይህም ብቻ ሳይሆን አሁን እርቅ ባገኘንበት+ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት በአምላክ ሐሴት እያደረግን ነው።
12 ስለሆነም በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤+ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ።+
13 ሕጉ ከመሰጠቱ በፊት ኃጢአት በዓለም ላይ ነበርና፤ ሆኖም ሕግ በሌለበት ማንም በኃጢአት አይጠየቅም።+
14 ይሁንና አዳም ትእዛዝ በመተላለፍ የሠራውን ዓይነት ኃጢአት ባልሠሩት ላይም እንኳ ሳይቀር ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ሞት በሁሉ ላይ ነገሠ፤ አዳም በኋላ ለሚመጣው አምሳያ ነበር።+
15 ሆኖም ስጦታው ያስገኘው ነገር በደሉ ካስከተለው ነገር የተለየ ነው። ምክንያቱም በአንድ ሰው በደል ብዙዎች ሞተዋል፤ ይሁንና የአምላክ ጸጋና ነፃ ስጦታው በአንዱ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ+ አማካኝነት ለብዙ ሰዎች ወደር የሌለው* ጥቅም አስገኝቷል!+
16 በተጨማሪም ነፃ ስጦታው ያስገኘው ውጤት የአንዱ ሰው ኃጢአት+ ካመጣው ውጤት የተለየ ነው። ምክንያቱም አንድን በደል ተከትሎ የመጣው ፍርድ ኩነኔን አስከትሏል፤+ ብዙዎች በደል ከፈጸሙ በኋላ ግን አምላክ ጻድቃን እንዲባሉ የሚያስችል ስጦታ ሰጥቷል።+
17 በአንድ ሰው በደል የተነሳ ሞት በዚህ ሰው በኩል ከነገሠ+ የአምላክን የተትረፈረፈ ጸጋና የጽድቅን ነፃ ስጦታ የሚቀበሉትማ+ በአንዱ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት+ ሕይወት አግኝተው ነገሥታት+ ሆነው እንደሚገዙ ይበልጥ የተረጋገጠ ነው!
18 ስለዚህ አንድ በደል ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲኮነኑ እንዳደረገ ሁሉ+ አንድ የጽድቅ ድርጊትም* ሁሉም ዓይነት ሰዎች ጻድቃን ናችሁ ተብለው ለሕይወት እንዲበቁ ያስችላል።+
19 ምክንያቱም በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደሆኑ ሁሉ+ በአንዱ ሰው መታዘዝም ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ።+
20 ሕጉ የመጣው ሰዎች ብዙ በደል እንደሚፈጽሙ ለማሳየት ነው።+ ይሁን እንጂ ሰዎች ብዙ ኃጢአት ሲፈጽሙ አምላክ ታላቅ ጸጋ አሳያቸው።
21 ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ኃጢአት ከሞት ጋር እንደነገሠ+ ሁሉ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የዘላለም ሕይወት ይገኝ ዘንድ ጸጋ በጽድቅ አማካኝነት እንዲነግሥ ነው።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ “ከአምላክ ጋር ሰላም አለን” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ “እጅግ እንደሰታለን” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ “እጅግ እንደሰታለን” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ ወይም “ለኀፍረት።”
^ ወይም “የተትረፈረፈ።”
^ ወይም “ከበደል ነፃ የሚያደርግ አንድ ድርጊትም።” ሰዎች ጻድቃን እንዲባሉ የሚያስችል ድርጊት ማለት ነው።