ሶፎንያስ 2:1-15

  • የቁጣው ቀን ሳይደርስባችሁ ይሖዋን ፈልጉ (1-3)

    • ጽድቅንና የዋህነትን ፈልጉ (3)

    • ‘ምናልባት ትሰወሩ ይሆናል’ (3)

  • በአጎራባች ብሔራት ላይ የተላለፈ ፍርድ (4-15)

2  እናንተ ኀፍረት የማይሰማችሁ ሕዝቦች ሆይ፣+በአንድነት ተሰብሰቡ፤ አዎ ተሰብሰቡ።+  2  የተላለፈው ውሳኔ ከመፈጸሙ በፊት፣ቀኑ እንደ ገለባ ከማለፉ በፊት፣የሚነደው የይሖዋ ቁጣ ሳይመጣባችሁ፣+የይሖዋ የቁጣ ቀን ሳይደርስባችሁ፣  3  እናንተ የጽድቅ ድንጋጌዎቹን* የምታከብሩ፣በምድር ላይ የምትኖሩ የዋሆች* ሁሉ ይሖዋን ፈልጉ።+ ጽድቅን ፈልጉ፤ የዋህነትን* ፈልጉ። ምናልባት በይሖዋ የቁጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል።+  4  ጋዛ የተተወች ከተማ ትሆናለችና፤አስቀሎንም ባድማ ትሆናለች።+ አሽዶድ በጠራራ ፀሐይ* ትባረራለች፤ኤቅሮንም ከሥሯ ትመነገላለች።+  5  “በባሕሩ ዳርቻ ለሚኖረው ሕዝብ ይኸውም ለከሪታውያን ብሔር ወዮለት!+ የይሖዋ ቃል በአንተ ላይ ነው። የፍልስጤማውያን ምድር የሆንሽው ከነአን ሆይ፣ አጠፋሻለሁ፤አንድም ነዋሪ አይተርፍም።  6  የባሕሩ ዳርቻም መሰማሪያ ይሆናል፤ለእረኞች የውኃ ጉድጓድና ለበጎች ከድንጋይ የተሠራ ጉረኖ ይኖረዋል።  7  ከይሁዳ ቤት ለቀሩት ሰዎች መኖሪያ ስፍራ ይሆናል፤+በዚያም የግጦሽ ቦታ ያገኛሉ። በምሽት በአስቀሎን ቤቶች ውስጥ ይተኛሉ። አምላካቸው ይሖዋ ትኩረቱን በእነሱ ላይ ያደርጋልና፤*የተማረኩባቸውንም ሰዎች መልሶ ይሰበስባል።”+  8  “ሞዓብ የሰነዘረችውን ነቀፋና+ የአሞናውያንን ስድብ ሰምቻለሁ፤+እነሱ በሕዝቤ ላይ ተሳልቀዋል፤ ግዛታቸውንም ለመውሰድ በእብሪት ዝተዋል።+  9  ስለዚህ በሕያውነቴ እምላለሁ” ይላል የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፣“ሞዓብ እንደ ሰዶም፣+አሞናውያንም እንደ ገሞራ ይሆናሉ፤+ሳማ የወረሰው ምድርና የጨው ጉድጓድ ይሆናሉ፤ ለዘለቄታውም ባድማ ሆነው ይቀራሉ።+ የሕዝቤ ቀሪዎች ይዘርፏቸዋል፤ከገዛ ብሔሬ የቀሩት ሰዎችም ይወርሷቸዋል። 10  ከኩራታቸው የተነሳ ይህ ይደርስባቸዋል፤+ምክንያቱም በሠራዊት ጌታ በይሖዋ ሕዝብ ላይ ተሳልቀዋል፤ ራሳቸውንም ከፍ ከፍ አድርገዋል። 11  ይሖዋ በእነሱ ዘንድ የተፈራ* ይሆናል፤በምድር ላይ ያሉትን አማልክት ሁሉ እንዳልነበሩ ያደርጋቸዋልና፤*የብሔራት ደሴቶች ሁሉ በያሉበት ሆነውለእሱ ይሰግዳሉ።*+ 12  እናንተም ኢትዮጵያውያን በሰይፌ ትገደላላችሁ።+ 13  እሱ እጁን ወደ ሰሜን ይዘረጋል፤ አሦርንም ያጠፋል፤ነነዌንም ባድማና እንደ በረሃ ደረቅ ያደርጋታል።+ 14  መንጎች ይኸውም ሁሉም ዓይነት የዱር እንስሳት* በውስጧ ይተኛሉ። ሻላ* እና ጃርት በፈራረሱት ዓምዶቿ መካከል ያድራሉ። የዝማሬ ድምፅ በመስኮት ይሰማል። ደጃፍ ላይ ፍርስራሽ ይኖራል፤የአርዘ ሊባኖስ እንጨቶቹ እንዲጋለጡ ያደርጋልና። 15  በልቧ ‘እኔ ብቻ ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ የለም’ ስትል የነበረችውያለስጋት የተቀመጠችው ኩሩዋ ከተማ ይህች ናት። ምንኛ አስፈሪ ቦታ ሆነች!የዱር እንስሳት የሚተኙባት ስፍራ ሆናለች። በእሷ በኩል የሚያልፍ ሁሉ ያፏጫል፤ ራሱንም ይነቀንቃል።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ፍርዶቹን።”
ወይም “ትሑታን።”
ወይም “ትሕትናን።”
ወይም “በቀትር።”
ወይም “እንክብካቤ ያደርግላቸዋልና።”
ወይም “የሚያሸብር።”
ወይም “ያመነምናቸዋልና።”
ወይም “እሱን ያመልኩታል።”
ቃል በቃል “አንድ ብሔር ያለው እንስሳ ሁሉ።”
ወይም “ገርጌሶ።” ጠፍጠፍ ያለ ረጅም መንቆር ያለው ትልቅ አሞራ።