ለቆላስይስ ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ 1:1-29
1 በአምላክ ፈቃድ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስና ከወንድማችን ከጢሞቴዎስ፣+
2 በቆላስይስ ለሚገኙ ከክርስቶስ ጋር አንድነት ላላቸው ታማኝ የሆኑ ቅዱሳን ወንድሞች፦
አባታችን ከሆነው አምላክ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
3 ስለ እናንተ ስንጸልይ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አባት የሆነውን አምላክ ሁልጊዜ እናመሰግናለን፤
4 ምክንያቱም በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ ስላላችሁ እምነትና ለቅዱሳን ሁሉ ስለምታሳዩት ፍቅር ሰምተናል፤
5 ይህም የሆነው በሰማይ ከሚጠብቃችሁ ተስፋ የተነሳ ነው።+ ይህን ተስፋ በተመለከተ ቀደም ሲል የሰማችሁት፣ በተነገራችሁ የእውነት መልእክት ይኸውም በምሥራቹ አማካኝነት ሲሆን
6 ይህም ምሥራች ወደ እናንተ ደርሷል። ምሥራቹ በመላው ዓለም እየተስፋፋና ፍሬ እያፈራ+ እንደሆነ ሁሉ የአምላክን ጸጋ እውነት ከሰማችሁበትና በትክክል ካወቃችሁበት ቀን አንስቶ በእናንተም መካከል እያደገና ፍሬ እያፈራ ነው።
7 የክርስቶስ ታማኝ አገልጋይ ሆኖ በእኛ ምትክ ከሚሠራውና አብሮን ባሪያ ከሆነው ከተወዳጁ ኤጳፍራ+ የተማራችሁት ይህን ነው።
8 ደግሞም ስለ መንፈሳዊ ፍቅራችሁ ነግሮናል።
9 ከዚህም የተነሳ ይህን ከሰማንበት ቀን አንስቶ ከጥበብና ከመንፈሳዊ ግንዛቤ+ ሁሉ ጋር በፈቃዱ ትክክለኛ እውቀት+ ትሞሉ ዘንድ ስለ እናንተ መጸለያችንንና መለመናችንን አላቋረጥንም፤+
10 ይህም በመልካም ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁና ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት በመቅሰም+ እያደጋችሁ ስትሄዱ ለይሖዋ* በሚገባ ሁኔታ እንድትመላለሱና እሱን ሙሉ በሙሉ እንድታስደስቱ ነው፤
11 በትዕግሥትና በደስታ ሁሉንም ነገር በጽናት እንድትቋቋሙ የአምላክ ታላቅ ኃይል የሚያስፈልጋችሁን ብርታት ሁሉ ይስጣችሁ፤+
12 ደግሞም በብርሃን ውስጥ ያሉት ቅዱሳን ከሚያገኙት ውርሻ+ ለመካፈል ያበቃችሁን አባት አመስግኑ።
13 እሱ ከጨለማው ሥልጣን ታድጎን+ ወደሚወደው ልጁ መንግሥት አሻግሮናል፤
14 ልጁም ቤዛውን በመክፈል ነፃ እንድንወጣ ይኸውም የኃጢአት ይቅርታ እንድናገኝ አድርጎናል።+
15 እሱ የማይታየው አምላክ አምሳልና+ የፍጥረት ሁሉ በኩር ነው፤+
16 ምክንያቱም በሰማያትና በምድር ያሉ ሌሎች ነገሮች በሙሉ፣ የሚታዩትና የማይታዩት ነገሮች፣ ዙፋኖችም ሆኑ ጌትነት፣ መንግሥታትም ሆኑ ሥልጣናት የተፈጠሩት በእሱ አማካኝነት ነው።+ ሌሎች ነገሮች በሙሉ የተፈጠሩት በእሱ በኩልና+ ለእሱ ነው።
17 በተጨማሪም እሱ ከሌሎች ነገሮች ሁሉ በፊት ነው፤+ ሌሎች ነገሮች ሁሉ ወደ ሕልውና የመጡትም በእሱ አማካኝነት ነው፤
18 እሱ የአካሉ ማለትም የጉባኤው ራስ ነው።+ በሁሉም ነገር ቀዳሚ መሆን እንዲችልም እሱ የመጀመሪያ፣ ከሙታን መካከልም በኩር ነው፤+
19 ይህም የሆነው እሱ በሁሉም ነገር ሙሉ እንዲሆን አምላክ ስለፈለገ ነው፤+
20 እንዲሁም በመከራው እንጨት* ላይ ባፈሰሰው ደም+ አማካኝነት ሰላም በመፍጠር ሌሎቹን ነገሮች ሁሉ ይኸውም በምድርም ሆነ በሰማያት ያሉትን ነገሮች ሁሉ በእሱ በኩል ከራሱ ጋር ለማስታረቅ ስለወደደ ነው።+
21 በእርግጥ እናንተ በአንድ ወቅት አእምሯችሁ በክፉ ሥራዎች ላይ ያተኮረ ስለነበር ከአምላክ የራቃችሁና ጠላቶች ነበራችሁ፤
22 አሁን ግን እሱ ቅዱሳንና እንከን የሌለባችሁ እንዲሁም ከማንኛውም ክስ ነፃ የሆናችሁ አድርጎ በፊቱ ሊያቀርባችሁ ስለፈለገ+ ራሱን ለሞት አሳልፎ በሰጠው ሰው ሥጋዊ አካል አማካኝነት ከራሱ ጋር አስታርቋችኋል፤
23 በእርግጥ ይህ የሚሆነው በእምነት መሠረት ላይ ታንጻችሁና+ ተደላድላችሁ በመቆም፣+ የሰማችሁት ምሥራች ካስገኘላችሁ ተስፋ ሳትወሰዱ በእምነት ጸንታችሁ ስትኖሩ ነው፤+ ይህም ምሥራች ከሰማይ በታች ላለ ፍጥረት ሁሉ* ተሰብኳል።+ እኔም ጳውሎስ የዚህ ምሥራች አገልጋይ ሆኛለሁ።+
24 ለእናንተ ስል በተቀበልኩት መከራ+ አሁን እየተደሰትኩ ነው፤ በክርስቶስ የተነሳ በአካሌ ላይ የሚደርሰው መከራ በዚህ ብቻ አያበቃም። ይህ መከራ እየደረሰብኝ ያለው ለአካሉ+ ይኸውም ለጉባኤው+ ስል ነው።
25 የአምላክን ቃል በተሟላ ሁኔታ እሰብክ ዘንድ ለእናንተ ጥቅም ሲባል ከአምላክ ከተሰጠኝ የመጋቢነት ሥራ+ ጋር በሚስማማ መንገድ የዚህ ጉባኤ አገልጋይ ሆኛለሁ፤
26 ይህም ቃል ካለፉት ሥርዓቶችና* ካለፉት ትውልዶች አንስቶ ተሰውሮ+ የቆየው ቅዱስ ሚስጥር+ ነው። አሁን ግን ለቅዱሳኑ ተገልጧል።+
27 በተጨማሪም አምላክ በአሕዛብ መካከል የዚህን ቅዱስ ሚስጥር ታላቅ ብልጽግና ለቅዱሳኑ ያሳውቅ ዘንድ ወዷል፤+ ይህ ቅዱስ ሚስጥር የክብሩ ተስፋ+ የሆነውና ከእናንተ ጋር አንድነት ያለው ክርስቶስ ነው።
28 እያንዳንዱን ሰው የጎለመሰ* የክርስቶስ ደቀ መዝሙር አድርገን ለአምላክ ማቅረብ እንድንችል ሰውን ሁሉ እያሳሰብንና በጥበብ ሁሉ እያስተማርን የምናውጀው ስለ እሱ ነው።+
29 ይህን ዳር ለማድረስ፣ በውስጤ እየሠራ ባለው በእሱ ብርቱ ኃይል አማካኝነት አቅሜ በሚፈቅደው ሁሉ በትጋት እየሠራሁ ነው።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ወይም “ከሰማይ በታች ባለ ፍጥረት ሁሉ መካከል።”
^ ወይም “ካለፉት ዘመናትና።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ወይም “ፍጹም።”