ለቆላስይስ ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ 3:1-25
3 ይሁን እንጂ ከክርስቶስ ጋር አብራችሁ ከተነሳችሁ+ ክርስቶስ በአምላክ ቀኝ+ በተቀመጠበት በላይ ያሉትን ነገሮች ፈልጉ።
2 አእምሯችሁ በምድር ባሉት ነገሮች ላይ ሳይሆን+ ምንጊዜም በላይ ባሉት ነገሮች ላይ እንዲያተኩር አድርጉ።+
3 እናንተ ሞታችኋልና፤ ሕይወታችሁም ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ ሁኔታ ከክርስቶስ ጋር ተሰውሯል።
4 ሕይወታችን የሆነው ክርስቶስ+ በሚገለጥበት ጊዜ እናንተም ከእሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ።+
5 ስለዚህ በምድር ያሉትን የአካል ክፍሎቻችሁን ግደሉ፤+ እነሱም የፆታ ብልግና፣* ርኩሰት፣ ልቅ የሆነ የፍትወት ስሜት፣+ መጥፎ ፍላጎትና ጣዖት አምልኮ የሆነው ስግብግብነት ናቸው።
6 በእነዚህ ነገሮች ምክንያት የአምላክ ቁጣ ይመጣል።
7 እናንተም በቀድሞ ሕይወታችሁ በዚህ መንገድ ትኖሩ ነበር።+
8 አሁን ግን ቁጣን፣ ንዴትን፣ ክፋትንና+ ስድብን+ ሁሉ ከእናንተ አስወግዱ፤ ጸያፍ ንግግርም+ ከአፋችሁ አይውጣ።
9 አንዳችሁ ሌላውን አትዋሹ።+ አሮጌውን ስብዕና* ከነልማዶቹ ገፋችሁ ጣሉ፤+
10 እንዲሁም ከፈጣሪው አምሳል ጋር በሚስማማ ሁኔታ+ በትክክለኛ እውቀት አማካኝነት እየታደሰ የሚሄደውን አዲሱን ስብዕና ልበሱ፤+
11 በዚህ ሁኔታ ግሪካዊ ወይም አይሁዳዊ፣ የተገረዘ ወይም ያልተገረዘ፣ የባዕድ አገር ሰው፣ እስኩቴስ፣* ባሪያ ወይም ነፃ ሰው ብሎ ልዩነት የለም፤ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉም ነገር ነው፤ እንዲሁም በሁሉም ነው።+
12 እንግዲህ የአምላክ ምርጦች፣+ ቅዱሳንና የተወደዳችሁ እንደመሆናችሁ መጠን ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄን፣+ ደግነትን፣ ትሕትናን፣+ ገርነትንና+ ትዕግሥትን+ ልበሱ።
13 አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖረው+ እንኳ እርስ በርስ መቻቻላችሁንና በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ።+ ይሖዋ* በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉ።+
14 ይሁንና በእነዚህ ነገሮች ሁሉ ላይ ፍቅርን ልበሱ፤+ ፍቅር ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ ነውና።+
15 በተጨማሪም አምላክ የጠራችሁ አንድ አካል እንድትሆኑና በሰላም እንድትኖሩ ስለሆነ የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ።*+ እንዲሁም አመስጋኝ መሆናችሁን አሳዩ።
16 የክርስቶስ ቃል ከጥበብ ሁሉ ጋር በተትረፈረፈ ሁኔታ በውስጣችሁ ይኑር። በመዝሙራት፣ ለአምላክ በሚቀርብ ውዳሴና በአመስጋኝነት መንፈስ* በሚዘመሩ መንፈሳዊ ዝማሬዎች ትምህርትና ማበረታቻ* መስጠታችሁን ቀጥሉ፤+ በልባችሁም ለይሖዋ* ዘምሩ።+
17 በቃልም ሆነ በተግባር የምታደርጉት ነገር ምንም ሆነ ምን አባት የሆነውን አምላክ በኢየሱስ በኩል እያመሰገናችሁ ሁሉንም ነገር በጌታ ኢየሱስ ስም አድርጉት።+
18 ሚስቶች ሆይ፣ የክርስቶስ ተከታዮች ሊያደርጉት የሚገባ ስለሆነ ለባሎቻችሁ ተገዙ።+
19 ባሎች ሆይ፣ ሚስቶቻችሁን መውደዳችሁን ቀጥሉ፤+ መራራ ቁጣም አትቆጧቸው።*+
20 ልጆች ሆይ፣ በሁሉም ነገር ለወላጆቻችሁ ታዘዙ፤+ እንዲህ ማድረጋችሁ ጌታን ያስደስተዋልና።
21 አባቶች ሆይ፣ ቅስማቸው እንዳይሰበር* ልጆቻችሁን አታበሳጯቸው።+
22 ባሪያዎች ሆይ፣ ሰውን ለማስደሰት ብላችሁ ሰብዓዊ ጌቶቻችሁ በሚያዩአችሁ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በቅን ልብ ተነሳስታችሁ ይሖዋን* በመፍራት ጌቶቻችሁ ለሆኑት በሁሉም ነገር ታዛዥ ሁኑ።+
23 የምታደርጉትን ሁሉ ለሰው ሳይሆን ለይሖዋ* እንደምታደርጉት በማሰብ በሙሉ ነፍሳችሁ* አድርጉት፤+
24 ከይሖዋ* ዘንድ እንደ ሽልማት የምትቀበሉት ውርሻ እንዳለ ታውቃላችሁና።+ ጌታችንን ክርስቶስን እንደ ባሪያ አገልግሉ።
25 መጥፎ ነገር የሚሠራ የእጁን እንደሚያገኝ የተረጋገጠ ነው፤+ ደግሞም አድልዎ የለም።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ቃል በቃል “ሰው።”
^ “እስኩቴስ” የሚለው ቃል ያልሠለጠነ ሕዝብን ያመለክታል።
^ ወይም “ልባችሁን ይቆጣጠር።”
^ ወይም “በጸጋ።”
^ ወይም “ምክር።”
^ ወይም “ኃይለኛም አትሁኑባቸው።”
^ ወይም “ተስፋ እንዳይቆርጡ።”
^ የቃላት መፍቻው ላይ “ነፍስ” የሚለውን ተመልከት።