ለቆላስይስ ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ 4:1-18
4 ጌቶች ሆይ፣ እናንተም በሰማይ ጌታ እንዳላችሁ በመገንዘብ ባሪያዎቻችሁን በጽድቅና በፍትሕ አስተዳድሯቸው።+
2 በጸሎት ረገድ ዘወትር ንቁ በመሆንና ምስጋና በማቅረብ+ በጽናት ጸልዩ።+
3 ደግሞም ለእኔ መታሰር ምክንያት የሆነውን ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውን ቅዱስ ሚስጥር ማወጅ እንድንችል+ አምላክ የቃሉን በር እንዲከፍትልን ለእኛም ጸልዩልን፤+
4 ቅዱሱን ሚስጥር የሚገባኝን ያህል በግልጽ እንዳውጅም ጸልዩልኝ።
5 ጊዜያችሁን በተሻለ መንገድ በመጠቀም* በውጭ ካሉት ጋር* ባላችሁ ግንኙነት በጥበብ መመላለሳችሁን ቀጥሉ።+
6 ለእያንዳንዱ ሰው እንዴት መልስ መስጠት እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ምንጊዜም በጨው+ የተቀመመ ያህል ለዛ ያለው ይሁን።+
7 በጌታ ታማኝ አገልጋይና አብሮኝ ባሪያ የሆነው የተወደደው ወንድሜ ቲኪቆስ+ ስለ እኔ ሁሉንም ነገር ይነግራችኋል።
8 እሱን ወደ እናንተ የምልከው ስላለንበት ሁኔታ እንድታውቁና ልባችሁን እንዲያጽናና ነው።
9 እናንተ ጋ ከነበረው ከታማኙና ከተወደደው ወንድሜ ከአናሲሞስ+ ጋር ይመጣል፤ እነሱም እዚህ እየተከናወነ ስላለው ነገር ሁሉ ያሳውቋችኋል።
10 አብሮኝ የታሰረው አርስጥሮኮስ+ ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ የበርናባስ ዘመድ* የሆነው ማርቆስም+ ሰላም ብሏችኋል (እሱን በተመለከተ ወደ እናንተ ከመጣ እንድትቀበሉት+ መመሪያ ደርሷችኋል)፤
11 ኢዮስጦስ ተብሎ የሚጠራው ኢየሱስም ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ እነዚህ ከተገረዙት ወገን ናቸው። ለአምላክ መንግሥት አብረውኝ የሚሠሩት እነዚህ ብቻ ናቸው፤ እነሱም የብርታት ምንጭ ሆነውልኛል።*
12 ከእናንተ ጋር የነበረው የክርስቶስ ኢየሱስ ባሪያ የሆነው ኤጳፍራ+ ሰላምታ ልኮላችኋል። በአምላክ ፈቃድ ሁሉ ፍጹምና* ጽኑ እምነት ያላችሁ ሆናችሁ እስከ መጨረሻው እንድትቆሙ ዘወትር በጸሎቱ ስለ እናንተ እየተጋደለ ነው።
13 ስለ እናንተ እንዲሁም በሎዶቅያና በሂራጶሊስ ስላሉት ብዙ እንደሚደክም እኔ ራሴ እመሠክርለታለሁ።
14 የተወደደው ሐኪም ሉቃስ+ ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ ዴማስም+ ሰላም ብሏችኋል።
15 በሎዶቅያ ላሉት ወንድሞችና ለንምፉን እንዲሁም በቤቷ ላለው ጉባኤ+ ሰላምታዬን አቅርቡልኝ።
16 እንዲሁም ይህ ደብዳቤ እናንተ ጋ ከተነበበ በኋላ በሎዶቅያውያን ጉባኤ እንዲነበብና ከሎዶቅያ የሚደርሳችሁ ደብዳቤ ደግሞ እናንተ ጋ እንዲነበብ ዝግጅት አድርጉ።+
17 በተጨማሪም አርክጳን+ “በጌታ የተቀበልከውን አገልግሎት ከፍጻሜ እንድታደርስ ለአገልግሎቱ ትኩረት ስጥ” በሉት።
18 እኔ ጳውሎስ በገዛ እጄ የጻፍኩላችሁ ሰላምታ ይድረሳችሁ።+ በሰንሰለት ታስሬ+ እንዳለሁ አስታውሱ። የአምላክ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “አመቺ የሆነውን ጊዜ በመግዛት።”
^ ወይም “የክርስቲያን ጉባኤ አባል ካልሆኑ ሰዎች ጋር።”
^ የበርናባስ የአጎቱ ወይም የአክስቱ ልጅ ሊሆን ይችላል።
^ ወይም “በእጅጉ አጽናንተውኛል።”
^ ወይም “ጎልማሳና።”