ነህምያ 1:1-11

  • ነህምያ ስለ ኢየሩሳሌም የሰማው ወሬ (1-3)

  • ነህምያ ያቀረበው ጸሎት (4-11)

1  የሃካልያህ ልጅ የነህምያ*+ ቃል ይህ ነው፦ በ20ኛው ዓመት በኪስሌው* ወር በሹሻን*+ ግንብ* ነበርኩ።  በዚህ ጊዜ ከወንድሞቼ አንዱ የሆነው ሃናኒ+ በይሁዳ ከነበሩ ሌሎች ሰዎች ጋር መጣ፤ እኔም ከምርኮ ስለተረፉት አይሁዳውያን ቀሪዎችና+ ስለ ኢየሩሳሌም ጠየቅኳቸው።  እነሱም እንዲህ አሉኝ፦ “ከምርኮ ተመልሰው በአውራጃው ውስጥ የሚገኙት ቀሪዎች በጣም አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ፤ መሳለቂያም ሆነዋል።+ የኢየሩሳሌም ቅጥሮች ፈራርሰዋል፤+ በሮቿም በእሳት ተቃጥለዋል።”+  እኔም ይህን ስሰማ ቁጭ ብዬ ማልቀስ ጀመርኩ፤ ለቀናትም በሰማይ አምላክ ፊት ሳዝን፣ ስጾምና+ ስጸልይ ቆየሁ።  ከዚያም እንዲህ አልኩ፦ “የሰማይ አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ለሚወዱህ፣ ትእዛዛትህንም ለሚያከብሩ ቃል ኪዳንህን የምትጠብቅና ታማኝ ፍቅር የምታሳይ ታላቅና የምትፈራ አምላክ ነህ፤+  እባክህ ዛሬ ወደ አንተ የማቀርበውን የአገልጋይህን ጸሎት ለመስማት ጆሮህ ወደ እኔ ያዘንብል፤ ዓይኖችህም ይከፈቱ፤ እኛ እስራኤላውያን በአንተ ላይ የፈጸምነውን ኃጢአት እየተናዘዝኩ ስለ አገልጋዮችህ ስለ እስራኤላውያን ቀን ከሌት እየጸለይኩ ነው።+ እኔም ሆንኩ የአባቴ ቤት ኃጢአት ሠርተናል።+  ለአገልጋይህ ለሙሴ የሰጠሃቸውን ትእዛዛት፣ ሥርዓቶችና ድንጋጌዎች ባለማክበር+ በአንተ ላይ መጥፎ ድርጊት እንደፈጸምን ምንም ጥርጥር የለውም።+  “እባክህ አገልጋይህን ሙሴን እንዲህ በማለት ያዘዝከውን ቃል* አስታውስ፦ ‘ታማኝነት የጎደለው ድርጊት የምትፈጽሙ ከሆነ በሕዝቦች መካከል እበትናችኋለሁ።+  ወደ እኔ ተመልሳችሁ ትእዛዛቴን ብትጠብቁና ብትፈጽሙ ግን ሕዝቦቻችሁ እስከ ሰማይ ዳርቻ ድረስ ቢበተኑ እንኳ ከዚያ እሰበስባቸዋለሁ፤+ እንዲሁም ስሜ እንዲኖርበት ወደመረጥኩት ስፍራ አመጣቸዋለሁ።’+ 10  እነሱ በታላቅ ኃይልህና በብርቱ እጅህ የዋጀሃቸው አገልጋዮችህና ሕዝቦችህ ናቸው።+ 11  ይሖዋ ሆይ፣ እባክህ የአገልጋይህን ጸሎትና ስምህን በመፍራት ደስ የሚሰኙ አገልጋዮችህን ጸሎት ለመስማት ጆሮህን አዘንብል፤ እባክህ ዛሬ አገልጋይህ እንዲሳካለት አድርግ፤ ይህም ሰው ይራራልኝ።”+ እኔም የንጉሡ መጠጥ አሳላፊ ነበርኩ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

“ያህ ያጽናናል” የሚል ትርጉም አለው።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።
ወይም “በሱሳ።”
ወይም “ቤተ መንግሥት፤ ምሽግ።”
ወይም “ለአገልጋይህ ለሙሴ የሰጠኸውን ማስጠንቀቂያ።”