ነህምያ 5:1-19

  • ነህምያ ወንድሞቻቸውን መበዝበዛቸውን እንዲያቆሙ አደረገ (1-13)

  • ነህምያ የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ አሳየ (14-19)

5  ሆኖም ወንዶቹም ሆኑ ሚስቶቻቸው በአይሁዳውያን ወንድሞቻቸው ላይ ታላቅ ጩኸት አሰሙ።+  አንዳንዶቹ “የእኛም ሆነ የወንዶች ልጆቻችንና የሴቶች ልጆቻችን ቁጥር ብዙ ነው። በሕይወት ለመቆየት የምንበላው እህል ማግኘት ይኖርብናል” ይሉ ነበር።  ሌሎቹም “የምግብ እጥረት በተከሰተበት ወቅት እህል ለማግኘት ስንል ማሳችንን፣ የወይን እርሻችንንና ቤታችንን መያዣ አድርገን ሰጥተናል” አሉ።  የተቀሩት ደግሞ እንዲህ ይሉ ነበር፦ “የንጉሡን ግብር ለመክፈል ስንል ማሳችንንና የወይን እርሻችንን አስይዘን ገንዘብ ተበድረናል።+  እንግዲህ ወንድሞቻችን የአጥንታችን ፍላጭ፣ የሥጋችን ቁራጭ ናቸው፤* ልጆቻችንም እንደ ልጆቻቸው ናቸው፤ ሆኖም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችንን ለባርነት አሳልፈን ለመስጠት ተገደናል፤ እንዲያውም ከሴቶች ልጆቻችን መካከል አንዳንዶቹ አሁንም በባርነት ላይ ናቸው።+ ያም ሆኖ ማሳችንና የወይን እርሻችን በሌሎች እጅ ስለሆነ ይህን ለማስቆም የሚያስችል አቅም የለንም።”  እኔም ጩኸታቸውንና ይህን አቤቱታቸውን ስሰማ በጣም ተናደድኩ።  ስለዚህ ነገሩን በልቤ ካጤንኩ በኋላ የተከበሩትን ሰዎችና የበታች ገዢዎቹን “እያንዳንዳችሁ ከገዛ ወንድማችሁ ላይ ወለድ እየተቀበላችሁ* ነው” በማለት ወቀስኳቸው።+ በተጨማሪም በእነሱ የተነሳ ታላቅ ስብሰባ ጠራሁ።  እንዲህም አልኳቸው፦ “ለብሔራት ተሸጠው የነበሩትን አይሁዳውያን ወንድሞቻችንን በተቻለን መጠን መልሰን ገዝተናቸው ነበር፤ ታዲያ እናንተ አሁን የገዛ ወንድሞቻችሁን መልሳችሁ ትሸጣላችሁ?+ ደግሞስ እንደገና ለእኛ መሸጥ ይኖርባቸዋል?” በዚህ ጊዜ የሚመልሱት ስለጠፋቸው ዝም አሉ።  ከዚያም እንዲህ አልኳቸው፦ “የምትሠሩት ሥራ ጥሩ አይደለም። ጠላቶቻችን የሆኑት ብሔራት መሳለቂያ እንዳያደርጉን አምላካችንን በመፍራት መመላለስ አልነበረባችሁም?+ 10  ከዚህም በላይ እኔም ሆንኩ ወንድሞቼና አገልጋዮቼ ገንዘብና እህል አበድረናቸዋል። እባካችሁ ይህን በወለድ ማበደር የሚባል ነገር እንተው።+ 11  ደግሞም እባካችሁ ማሳዎቻቸውን፣ የወይን እርሻዎቻቸውን፣ የወይራ ዛፎቻቸውንና ቤቶቻቸውን እንዲሁም ከገንዘብ፣ ከእህል፣ ከአዲስ የወይን ጠጅና ከዘይት ወለድ አድርጋችሁ የተቀበላችሁትን ከመቶ አንድ እጅ* ዛሬውኑ መልሱላቸው።”+ 12  እነሱም “እነዚህን ነገሮች እንመልስላቸዋለን፤ በምላሹም ምንም ነገር እንዲያደርጉልን አንጠይቅም። ልክ እንዳልከው እናደርጋለን” አሉ። እኔም ካህናቱን ጠርቼ ሰዎቹን ይህን ቃል እንዲጠብቁ አስማልኳቸው። 13  በተጨማሪም የልብሴን እጥፋት* አራግፌ እንዲህ አልኳቸው፦ “ይህን ቃል የማይፈጽመውን ማንኛውንም ሰው እውነተኛው አምላክ ከቤቱና ከንብረቱ እንዲህ አራግፎ ያስወጣው፤ ልክ እንደዚህ ተራግፎም ባዶውን ይቅር።” በዚህ ጊዜ መላው ጉባኤ “አሜን!”* አለ። ይሖዋንም አመሰገኑ፤ ሕዝቡም ቃል እንደገቡት አደረጉ። 14  ከዚህም በላይ ንጉሡ በይሁዳ ምድር ገዢያቸው አድርጎ ከሾመኝ+ ጊዜ አንስቶ ማለትም ንጉሥ አርጤክስስ+ ከነገሠ ከ20ኛው ዓመት+ አንስቶ እስከ 32ኛው ዓመት+ ድረስ ይኸውም ለ12 ዓመት ያህል እኔም ሆንኩ ወንድሞቼ ለገዢው የሚገባውን ቀለብ አልበላንም።+ 15  ከእኔ በፊት የነበሩት የቀድሞዎቹ ገዢዎች ግን በሕዝቡ ላይ ሸክም ጭነውበት የነበረ ከመሆኑም ሌላ ከሕዝቡ ላይ ለምግብና ለወይን ጠጅ በየቀኑ 40 የብር ሰቅል* ይወስዱ ነበር። በተጨማሪም አገልጋዮቻቸው ሕዝቡን ይጨቁኑ ነበር። እኔ ግን አምላክን ስለምፈራ+ እንዲህ አላደረግኩም።+ 16  ከዚህም በላይ ይህን ቅጥር በመገንባቱ ሥራ ተሳትፌያለሁ፤ አገልጋዮቼም በሙሉ ሥራውን ለመሥራት እዚያ ተሰባስበው ነበር፤ የራሳችንም መሬት አልነበረንም።+ 17  በተጨማሪም 150 አይሁዳውያንና የበታች ገዢዎች እንዲሁም ከሌሎች ብሔራት ወደ እኛ የመጡ ሰዎች ከማዕዴ ይበሉ ነበር። 18  በየቀኑ አንድ በሬ፣ ስድስት ምርጥ በጎች እንዲሁም ወፎች ይዘጋጁልኝ* ነበር፤ በየአሥር ቀኑ ደግሞ የተለያየ ዓይነት የወይን ጠጅ በብዛት ይቀርብልን ነበር። እንደዚያም ሆኖ ሕዝቡ የራሱ የአገልግሎት ቀንበር ከብዶት ስለነበር ለገዢው የሚገባው ቀለብ እንዲሰጠኝ ጠይቄ አላውቅም። 19  አምላኬ ሆይ፣ ለዚህ ሕዝብ ስላደረግኩት ነገር ሁሉ በመልካም አስበኝ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ሥጋችን እንደ ወንድሞቻችን ሥጋ ነው።”
ወይም “ለገዛ ወንድማችሁ በአራጣ እያበደራችሁ።”
ወይም በየወሩ “አንድ በመቶ።”
ቃል በቃል “እቅፍ።”
ወይም “ይሁን!”
አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “በራሴ ወጪ ይዘጋጁ።”