ነህምያ 9:1-38

  • ሕዝቡ ኃጢአቱን ተናዘዘ (1-38)

    • ይሖዋ ይቅር ባይ አምላክ ነው (17)

9  በዚህ ወር በ24ኛው ቀን እስራኤላውያን ተሰበሰቡ፤ ማቅ ለብሰውና በላያቸው ላይ አቧራ ነስንሰው ጾሙ።+  ከዚያም የእስራኤል ዘሮች ከባዕዳን ሁሉ ራሳቸውን ለዩ፤+ ቆመውም ኃጢአታቸውንና አባቶቻቸው የፈጸሙትን ስህተት ሁሉ ተናዘዙ።+  ከዚያም ባሉበት ስፍራ ቆሙ፤ በቀኑ አንድ አራተኛም* ከአምላካቸው ከይሖዋ የሕግ መጽሐፍ+ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ያነብቡ፣ በቀኑ አንድ አራተኛ ደግሞ ለአምላካቸው ለይሖዋ ይናዘዙና ይሰግዱ ነበር።  የሹዋ፣ ባኒ፣ ቃድሚኤል፣ ሸባንያህ፣ ቡኒ፣ ሸረበያህ፣+ ባኒ እና ኬናኒ ለሌዋውያኑ በተሠራው ከፍ ያለ መድረክ ላይ ቆመው+ ወደ አምላካቸው ወደ ይሖዋ ጮኹ።  እንዲሁም ሌዋውያኑ የሹዋ፣ ቃድሚኤል፣ ባኒ፣ ሃሻበንያህ፣ ሸረበያህ፣ ሆዲያህ፣ ሸባንያህ እና ፐታያህ እንዲህ አሉ፦ “ተነሱ፤ አምላካችሁን ይሖዋን ከዘላለም እስከ ዘላለም አመስግኑ።+ ከምስጋናና ከውዳሴ ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ያለውን ክብራማ ስምህን ያመስግኑ።  “አንተ ብቻ ይሖዋ ነህ፤+ አንተ ሰማያትን፣ አዎ ሰማየ ሰማያትንና ሠራዊታቸውን ሁሉ፣ ምድርንና በላይዋ ያሉትን ሁሉ፣ ባሕርንና በውስጡ ያሉትን ሁሉ ሠርተሃል። ሁሉንም ሕያው አድርገህ ታኖራቸዋለህ፤ የሰማይ ሠራዊትም ለአንተ ይሰግዳል።  አብራምን+ መርጠህ ከከለዳውያን ዑር+ ያወጣኸውና አብርሃም+ ብለህ የጠራኸው እውነተኛው አምላክ ይሖዋ አንተ ነህ።  ልቡ በፊትህ ታማኝ ሆኖ ስላገኘኸው+ የከነአናውያንን፣ የሂታውያንን፣ የአሞራውያንን፣ የፈሪዛውያንን፣ የኢያቡሳውያንንና የገርጌሻውያንን ምድር ለእሱ ይኸውም ለዘሩ ለመስጠት ከእሱ ጋር ቃል ኪዳን ተጋባህ፤+ ጻድቅ ስለሆንክም ቃልህን ጠበቅክ።  “በመሆኑም አባቶቻችን በግብፅ ሳሉ የደረሰባቸውን ሥቃይ አየህ፤+ በቀይ ባሕር ያሰሙትንም ጩኸት ሰማህ። 10  ከዚያም በፈርዖን፣ በአገልጋዮቹ ሁሉና በምድሩ በሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ ፊት ምልክቶችንና ተአምራትን አሳየህ፤+ ይህን ያደረግከው በእነሱ ላይ የእብሪት ድርጊት+ እንደፈጸሙ ስላወቅክ ነው። ለራስህም እስከ ዛሬ ጸንቶ የኖረ ስም አተረፍክ።+ 11  በባሕሩ መሃል በደረቅ ምድር እንዲሻገሩ ባሕሩን በፊታቸው ከፈልክ፤+ አሳዳጆቻቸውንም የሚናወጥ ባሕር ውስጥ እንደተጣለ ድንጋይ ወደ ጥልቁ ወረወርካቸው።+ 12  ቀን በደመና ዓምድ፣ ሌሊት ደግሞ የሚሄዱበት መንገድ ብርሃን እንዲሆንላቸው ለማድረግ ስትል በእሳት ዓምድ መራሃቸው።+ 13  በሲና ተራራ ላይ ወርደህ+ ከሰማይ አነጋገርካቸው፤+ እንዲሁም የጽድቅ ፍርዶችን፣ የእውነት ሕጎችን፣* መልካም ሥርዓቶችንና ትእዛዛትን ሰጠሃቸው።+ 14  ቅዱስ ሰንበትህን አሳወቅካቸው፤+ እንዲሁም በአገልጋይህ በሙሴ አማካኝነት ትእዛዛትህን፣ ሥርዓቶችህንና ሕግህን ሰጠሃቸው። 15  በተራቡ ጊዜ ከሰማይ ምግብ ሰጠሃቸው፤+ በተጠሙም ጊዜ ከዓለቱ ውኃ አፈለቅክላቸው፤+ ልትሰጣቸው የማልክላቸውን* ምድር ገብተው እንዲወርሱም ነገርካቸው። 16  “ይሁንና እነሱ ማለትም አባቶቻችን የእብሪት ድርጊት ፈጸሙ፤+ ግትሮችም ሆኑ፤*+ ትእዛዛትህንም አልሰሙም። 17  ለመስማትም አሻፈረኝ አሉ፤+ በመካከላቸው የፈጸምካቸውን እጅግ አስደናቂ የሆኑ ነገሮች ረሱ፤ ከዚህ ይልቅ ግትሮች ሆኑ፤* በግብፅ ወደነበሩበት የባርነት ሕይወት ለመመለስም መሪ ሾሙ።+ አንተ ግን ይቅር ለማለት ዝግጁ የሆንክ፣* ሩኅሩኅ፣* መሐሪ፣ ለቁጣ የዘገየህና ታማኝ ፍቅርህ የበዛ* አምላክ ነህ፤+ እነሱንም አልተውካቸውም።+ 18  ሌላው ቀርቶ ለራሳቸው የብረት* ጥጃ ሐውልት ሠርተው ‘ከግብፅ መርቶ ያወጣህ አምላክህ ይህ ነው’+ በማለት ከፍተኛ የንቀት ተግባር በፈጸሙ ጊዜም 19  አንተ ምሕረትህ ታላቅ ስለሆነ በምድረ በዳ አልተውካቸውም።+ ቀን ቀን በመንገዳቸው ይመራቸው የነበረው የደመና ዓምድም ሆነ የሚሄዱበትን መንገድ የሚያበራላቸው ሌሊት ሌሊት ይታይ የነበረው የእሳት ዓምድ ከላያቸው አልተነሳም ነበር።+ 20  ጥልቅ ማስተዋል እንዲያገኙ መልካም መንፈስህን ሰጠሃቸው፤+ መናህንም ከአፋቸው አልከለከልክም፤+ በተጠሙም ጊዜ ውኃ ሰጠሃቸው።+ 21  በምድረ በዳም ለ40 ዓመት መገብካቸው።+ ምንም ያጡት ነገር አልነበረም። ልብሶቻቸው አላለቁም፤+ እግሮቻቸውም አላበጡም። 22  “መንግሥታትንና ሕዝቦችን እየከፋፈልክ ሰጠሃቸው፤+ በመሆኑም የሲሖንን+ ምድር ይኸውም የሃሽቦንን+ ንጉሥ ምድር እንዲሁም የባሳንን ንጉሥ የኦግን+ ምድር ወረሱ። 23  ወንዶች ልጆቻቸውንም በሰማያት ላይ እንዳሉ ከዋክብት አበዛሃቸው።+ ከዚያም ገብተው እንዲወርሷት ለአባቶቻቸው ቃል ወደገባህላቸው ምድር አመጣሃቸው።+ 24  በመሆኑም ወንዶች ልጆቻቸው ገብተው ምድሪቱን ወረሱ፤+ አንተም የምድሪቱ ነዋሪዎች የሆኑትን ከነአናውያን በፊታቸው እንዲንበረከኩ አደረግክ፤+ በነገሥታታቸውና በምድሪቱ ሕዝቦች ላይም ያሻቸውን እንዲያደርጉ በእጃቸው አሳልፈህ ሰጠሃቸው። 25  የተመሸጉ ከተሞችንና+ ለም የሆነውን* መሬት ያዙ፤+ መልካም ነገሮች ሁሉ የሞሉባቸውን ቤቶች፣ የተቆፈሩ የውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓዶችን፣ የወይን እርሻዎችን፣ የወይራ ዛፎችንና+ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን የፍራፍሬ ዛፎች ወረሱ። በመሆኑም እስኪጠግቡ ድረስ በሉ፤ ሰቡም፤ ታላቅ በሆነው ጥሩነትህም ተንደላቀቁ። 26  “ይሁንና ለመታዘዝ እንቢተኞች በመሆን በአንተ ላይ ዓመፁ፤+ ለሕግህም ጀርባቸውን ሰጡ።* ወደ አንተ እንዲመለሱ ሲያስጠነቅቋቸው የነበሩትን ነቢያትህን ገደሉ፤ ከፍተኛ ንቀት የሚንጸባረቅባቸውንም ተግባሮች ፈጸሙ።+ 27  በዚህም የተነሳ መከራ ለሚያሳዩአቸው ጠላቶቻቸው አሳልፈህ ሰጠሃቸው።+ በተጨነቁ ጊዜ ግን ወደ አንተ ጮኹ፤+ አንተም ከሰማያት ሆነህ ሰማሃቸው፤ ከታላቅ ምሕረትህ የተነሳም ከጠላቶቻቸው እጅ የሚታደጓቸውን አዳኞች ሰጠሃቸው።+ 28  “ሆኖም ፋታ ሲያገኙ እንደገና በፊትህ መጥፎ ነገር አደረጉ፤+ አንተም በሚጨቁኗቸው* ጠላቶቻቸው እጅ ጣልካቸው።+ ከዚያም ተመልሰው ለእርዳታ ወደ አንተ ጮኹ፤+ አንተም በሰማያት ሆነህ ሰማሃቸው፤ ከታላቅ ምሕረትህም የተነሳ በተደጋጋሚ አዳንካቸው።+ 29  ወደ ሕግህ እንዲመለሱ ለማድረግ ብታስጠነቅቃቸውም እነሱ ግን እብሪተኞች በመሆን ትእዛዛትህን ለመስማት አሻፈረኝ አሉ፤+ ለሚጠብቃቸው ሰው ሁሉ ሕይወት በሚያስገኙት ድንጋጌዎችህ ላይ ኃጢአት ሠሩ።+ ደግሞም በግትርነት ጀርባቸውን ሰጡ፤ አንገታቸውን አደነደኑ፤ ለመስማትም አሻፈረኝ አሉ። 30  አንተ ግን ለብዙ ዓመታት ታገሥካቸው፤+ በነቢያትህም አማካኝነት በመንፈስህ አስጠነቀቅካቸው፤ እነሱ ግን ለመስማት አሻፈረኝ አሉ። በመጨረሻም በምድሪቱ ለሚኖሩት ሕዝቦች አሳልፈህ ሰጠሃቸው።+ 31  ከታላቅ ምሕረትህ የተነሳ ፈጽመህ አላጠፋሃቸውም+ ወይም አልተውካቸውም፤ ምክንያቱም አንተ ሩኅሩኅና* መሐሪ አምላክ ነህ።+ 32  “አምላካችን ሆይ፣ አንተ ታላቅ፣ ኃያል፣ የተፈራህ፣ ቃል ኪዳንህን የምትጠብቅና ታማኝ ፍቅር የምታሳይ አምላክ ነህ፤+ ከአሦር ነገሥታት+ ዘመን አንስቶ እስካሁን ድረስ በእኛ፣ በነገሥታታችን፣ በመኳንንታችን፣+ በካህናታችን፣+ በነቢያታችን፣+ በአባቶቻችንና በመላው ሕዝብህ ላይ እየደረሰ ያለውን ይህን ሁሉ መከራ አቅልለህ አትመልከተው። 33  በእኛ ላይ በደረሰው ነገር ሁሉ አንተ ጻድቅ ነህ፤ ምክንያቱም አንተ ማንኛውንም ነገር ያደረግከው በታማኝነት ነው፤ ክፉ ነገር የፈጸምነው እኛ ነን።+ 34  ነገሥታታችን፣ መኳንንታችን፣ ካህናታችንም ሆኑ አባቶቻችን ሕግህን አልጠበቁም፤ ደግሞም እነሱን ለማስጠንቀቅ ብለህ ለሰጠሃቸው ትእዛዛትም ሆነ ማሳሰቢያዎች ትኩረት አልሰጡም።* 35  ሌላው ቀርቶ በራሳቸው መንግሥት ሥር በሚተዳደሩበት፣ አትረፍርፈህ በሰጠሃቸው መልካም ነገሮች በሚደሰቱበት እንዲሁም ባዘጋጀህላቸው ሰፊና ለም* ምድር በሚኖሩበት ጊዜም እንኳ አንተን አላገለገሉም፤+ ከመጥፎ ተግባራቸውም አልተቆጠቡም። 36  በመሆኑም ይኸው ዛሬ እኛ ባሪያዎች ሆነናል፤+ አዎ፣ አባቶቻችን ፍሬዋንና በረከቷን እንዲበሉ በሰጠሃቸው ምድር ላይ ባሪያዎች ሆነናል። 37  በምድሪቱ የተትረፈረፈ ምርት እየተጠቀሙ ያሉት በኃጢአታችን የተነሳ በላያችን እንዲነግሡ ያደረግካቸው ነገሥታት ናቸው።+ እነሱም በሰውነታችንና በቤት እንስሶቻችን ላይ እንዳሻቸው እየገዙ ነው፤ እኛም በከባድ መከራ ውስጥ እንገኛለን። 38  “በዚህም ሁሉ የተነሳ በጽሑፍ የሰፈረ ጽኑ ስምምነት እናደርጋለን፤+ ስምምነቱም በመኳንንታችን፣ በሌዋውያናችንና በካህናታችን ማኅተም የጸደቀ ይሆናል።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ለሦስት ሰዓትም።”
ወይም “አስተማማኝ ሕጎችን።”
ቃል በቃል “እጅህን ያነሳህላቸውን።”
ቃል በቃል “አንገታቸውንም አደነደኑ።”
ወይም “ፍቅራዊ ደግነትህ የበዛ።”
ወይም “ቸር።”
ወይም “ይቅር ባይ የሆንክ።”
ቃል በቃል “አንገታቸውን አደነደኑ።”
ወይም “ቀልጦ የተሠራ።”
ወይም “የበለጸገውን።”
ቃል በቃል “ሕግህንም ወደኋላቸው አሽቀንጥረው ጣሉ።”
ወይም “በሚያደቋቸው።”
ወይም “ቸርና።”
ወይም “ማስጠንቀቂያዎች ትኩረት አልሰጡም።”
ወይም “የበለጸገ።”