ናሆም 1:1-15
1 በነነዌ ላይ የተላለፈ ፍርድ፦+ የኤልቆሻዊው የናሆም* የራእዩ መጽሐፍ ይህ ነው፦
2 ይሖዋ እሱ ብቻ እንዲመለክ የሚፈልግና+ የሚበቀል አምላክ ነው፤ይሖዋ ይበቀላል፤ ቁጣውንም ለመግለጽ ዝግጁ ነው።+
ይሖዋ ባላጋራዎቹን ይበቀላል፤ለጠላቶቹም ቁጣ ያከማቻል።
3 ይሖዋ ለቁጣ የዘገየ ነው፤+ ኃይሉም ታላቅ ነው፤+ይሁንና ይሖዋ ተገቢውን ቅጣት ከመስጠት ፈጽሞ ወደኋላ አይልም።+
መንገዱ በአደገኛ ነፋስና በወጀብ ውስጥ ነው፤ደመናት ከእግሩ በታች እንዳለ አቧራ ናቸው።+
4 ባሕሩን ይገሥጻል፤+ ያደርቀዋልም፤ወንዞቹንም በሙሉ ያደርቃቸዋል።+
ባሳንና ቀርሜሎስ ይጠወልጋሉ፤+የሊባኖስ አበባዎችም ይጠወልጋሉ።
5 ከእሱ የተነሳ ተራሮች ይንቀጠቀጣሉ፤ኮረብቶችም ይቀልጣሉ።+
ከፊቱም የተነሳ ምድር፣የብስና በላዩ የሚኖሩት ሁሉ ይናወጣሉ።+
6 በቁጣው ፊት ማን ሊቆም ይችላል?+
የንዴቱን ትኩሳት ሊቋቋም የሚችልስ ማን ነው?+
ቁጣው እንደ እሳት ይፈስሳል፤ዓለቶችም ከእሱ የተነሳ ይፈረካከሳሉ።
7 ይሖዋ ጥሩ ነው፤+ በጭንቀትም ቀን መሸሸጊያ ነው።+
እሱን መጠጊያ ማድረግ የሚፈልጉትን ያውቃል።*+
8 ጠራርጎ በሚወስድ ጎርፍ ስፍራዋን* ፈጽሞ ያጠፋል፤ጠላቶቹንም ጨለማ ያሳድዳቸዋል።
9 በይሖዋ ላይ የምታሴሩት ምንድን ነው?
እሱ ፈጽሞ ያጠፋል።
ጭንቀት ዳግመኛ አይመጣም።+
10 እርስ በርሳቸው እንደ እሾህ ተጠላልፈዋልና፤መጠጥ* ጠጥተው እንደሰከሩ ሰዎች ናቸው፤ሆኖም እንደደረቀ ገለባ እሳት ይበላቸዋል።
11 በይሖዋ ላይ ክፉ ነገር የሚያሴር፣ከንቱ ምክርም የሚሰጥ ከመካከልሽ ይወጣል።
12 ይሖዋ እንዲህ ይላል፦
“ምንም እንኳ የተሟላ ኃይል ያላቸውና ብዙዎች ቢሆኑምይቆረጣሉ፤ ደግሞም ይጠፋሉ።*
መከራ አሳይቼሃለሁ፤* ከዚያ በኋላ ግን መከራ አላመጣብህም።
13 አሁንም ቀንበሩን ከአንተ ላይ እሰብራለሁ፤+እስራትህንም እበጥሳለሁ።
14 ይሖዋ አንተን* በተመለከተ እንዲህ ሲል አዟል፦‘ከእንግዲህ ስምህን የሚያስጠራ አይኖርም።
የተቀረጹትን ምስሎችና ከብረት የተሠሩትን ሐውልቶች* ከአማልክትህ ቤት* አስወግዳለሁ።
የተናቅክ ስለሆንክ መቃብር አዘጋጅልሃለሁ።’
15 እነሆ ምሥራች ይዞ የሚመጣ፣ሰላምንም የሚያውጅ ሰው እግር በተራሮች ላይ ነው።+
ይሁዳ ሆይ፣ በዓሎችሽን አክብሪ፤+ ስእለትሽን ፈጽሚ፤ከእንግዲህ ወዲህ የማይረባ ሰው በመካከልሽ አያልፍምና።
እንዲህ ያለው ሰው ሙሉ በሙሉ ይወገዳል።”
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ “አጽናኝ” የሚል ትርጉም አለው።
^ ወይም “ይንከባከባል።”
^ ነነዌን ያመለክታል።
^ ወይም “ከስንዴ የሚዘጋጅ መጠጥ።”
^ “እሱም በመካከላቸው ያልፋል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ ይሁዳን ያመለክታል።
^ አሦርን ያመለክታል።
^ ወይም “ቀልጠው የተሠሩትን ሐውልቶች።”
^ ወይም “ቤተ መቅደስ።”