አስቴር 5:1-14
5 በሦስተኛው ቀን+ አስቴር ልብሰ መንግሥቷን ለብሳ ከንጉሡ ቤት ፊት ለፊት በሚገኘው በንጉሡ ቤት* ውስጠኛ ግቢ ቆመች፤ ንጉሡም በመግቢያው ፊት ለፊት በሚገኘው በንጉሡ ቤት ውስጥ በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ነበር።
2 ንጉሡ፣ ንግሥት አስቴርን ግቢ ውስጥ ቆማ ሲያያት በፊቱ ሞገስ አገኘች፤ ንጉሡም እጁ ላይ የነበረውን የወርቅ በትረ መንግሥት ለአስቴር ዘረጋላት።+ በዚህ ጊዜ አስቴር ቀርባ የበትሩን ጫፍ ነካች።
3 ንጉሡም “ንግሥት አስቴር ሆይ፣ ምን ችግር አጋጠመሽ? የምትፈልጊው ምንድን ነው? እስከ መንግሥቴ እኩሌታ እንኳ ብትጠይቂ ይሰጥሻል!” አላት።
4 አስቴርም መልሳ “ንጉሡን ደስ የሚያሰኘው ከሆነ ንጉሡ ለእሱ ባዘጋጀሁት ግብዣ ላይ ዛሬ ከሃማ+ ጋር ይገኝልኝ” አለች።
5 በመሆኑም ንጉሡ አገልጋዮቹን “አስቴር ባቀረበችው ጥያቄ መሠረት በአስቸኳይ እንዲመጣ ለሃማ ንገሩት” አለ። ስለዚህ ንጉሡና ሃማ አስቴር ወዳዘጋጀችው ግብዣ መጡ።
6 በወይን ጠጅ ግብዣው ላይ ንጉሡ አስቴርን እንዲህ አላት፦ “የምትጠይቂው ምንድን ነው? የጠየቅሽው ይሰጥሻል! የምትፈልጊውስ ምንድን ነው? እስከ መንግሥቴ እኩሌታ እንኳ ብትጠይቂ ይሰጥሻል!”+
7 አስቴርም እንዲህ ስትል መለሰች፦ “የምጠይቀውም ሆነ የምፈልገው ነገር ይህ ነው፦
8 በንጉሡ ዘንድ ሞገስ ካገኘሁ እንዲሁም ንጉሡ የምጠይቀውን ነገር መስጠትና የምፈልገውን መፈጸም ደስ ካሰኘው ነገ ንጉሡና ሃማ ለእነሱ በማዘጋጅላቸው ግብዣ ላይ ይገኙ፤ እኔም በነገው ዕለት ንጉሡ ያለውን አደርጋለሁ።”
9 በዚያ ቀን ሃማ ተደስቶ ልቡም ሐሴት አድርጎ ወጣ። ሆኖም ሃማ፣ መርዶክዮስን በንጉሡ በር ላይ ሲያየው እንዲሁም እንዳልተነሳለትና በፊቱ እንዳልተንቀጠቀጠ ሲመለከት በመርዶክዮስ ላይ ቁጣው ነደደ።+
10 ይሁንና ሃማ ራሱን ተቆጣጥሮ ወደ ቤቱ ሄደ። ከዚያም ጓደኞቹንና ሚስቱን ዜሬሽን+ አስጠራቸው።
11 ሃማም ስለ ሀብቱ ታላቅነትና ስለ ወንዶች ልጆቹ ብዛት+ እንዲሁም ንጉሡ ላቅ ያለ ሹመት እንደሰጠውና ከመኳንንቱም ሆነ ከንጉሡ አገልጋዮች በላይ ከፍ ከፍ እንዳደረገው+ በጉራ ይነግራቸው ጀመር።
12 ሃማ በመቀጠል እንዲህ አለ፦ “ምን ይሄ ብቻ፣ ንግሥት አስቴር አዘጋጅታ በነበረው ግብዣ+ ላይ ከንጉሡ ጋር እንድገኝ የጋበዘችው እኔን ብቻ ነው። በተጨማሪም ነገ ከንጉሡና ከእሷ ጋር እንድገኝ ጋብዛኛለች።+
13 ይሁን እንጂ አይሁዳዊውን መርዶክዮስን በንጉሡ በር ላይ ተቀምጦ የማየው ከሆነ ይህ ሁሉ ምንም አያስደስተኝም።”
14 በዚህ ጊዜ ሚስቱ ዜሬሽና ጓደኞቹ በሙሉ እንዲህ አሉት፦ “ቁመቱ 50 ክንድ* የሆነ እንጨት አስተክል። ከዚያም ነገ ጠዋት በላዩ ላይ መርዶክዮስ እንዲሰቀል ለንጉሡ ንገረው።+ አንተም ከንጉሡ ጋር በግብዣው ላይ ተገኝተህ ሐሴት አድርግ።” ይህ ሐሳብ ሃማን አስደሰተው፤ እንጨቱንም አስተከለ።